ዘፀአት 16:1-18
ዘፀአት 16:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
መላው የእስራኤል ማኅበር ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ወር በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ከኤሊም ተነሥተው በኤሊምና በሲና መካከል ወደምትገኘው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። በምድረ በዳውም መላው የእስራኤል ልጆች ማኅበር በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ። እስራኤላውያንም እነርሱን እንዲህ አሏቸው፣ “በሥጋ መቀቀያው ምንቸት ዙሪያ ተቀምጠን የፈለግነውን ያህል ምግብ መመገብ በምንችልበት በግብጽ ሳለን፣ ምነው በእግዚአብሔር እጅ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! እናንተ ግን ይህ ሁሉ ጉባኤ በራብ እንዲያልቅ ወደዚህ ምድረ በዳ አመጣችሁን” አሏቸው። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ከሰማይ እንጀራ አዘንብላችኋለሁ። ሕዝቡም በየቀኑ እየወጡ ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰብስቡ፤ በዚህም ትእዛዞቼን ይጠብቁ እንደ ሆነ እፈትናቸዋለሁ። በስድስተኛው ቀን በሌሎቹ ዕለታት ከሚሰበስቡት ዕጥፍ ሰብስበው ያዘጋጁ።” ስለዚህ ሙሴና አሮን ለእስራኤላውያን ሁሉ፣ እንዲህ አሉ፤ “ከግብጽ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር መሆኑን በዛሬዪቱ ምሽት ታውቃላችሁ። በርሱ ላይ ያሰማችሁትን ማጕረምረም ሰምቷልና በማለዳ የእግዚአብሔርን ክብር ታያላችሁ፤ ለመሆኑ በእኛስ ላይ የምታጕረመርሙት እኛ ምንድን ነንና ነው?” አሏቸው። ሙሴም ንግግሩን በመቀጠል፣ “በርሱ ላይ ማጕረምረማችሁን ሰምቷልና በምሽት የምትበሉትን ሥጋ፣ በማለዳም የምትፈልጉትን ያህል እንጀራ በሚሰጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር መሆኑን ታውቃላችሁ፤ እኛ ማን ነን? በእኛ ላይ አይደለም ያጕረመረማችሁት፤ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ” አላቸው። ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ ‘ማጕረምረማችሁን እርሱ ሰምቷልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ’ ብለህ ለመላው የእስራኤል ማኅበር ተናገር” አለው። አሮንም ለመላው የእስራኤል ማኅበር ሲናገር ሳለ ወደ ምድረ በዳው ተመለከቱ፤ በዚያም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ላይ ተገልጦ ይታይ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤላውያንን ማጕረምረም ሰምቻለሁ፤ ይህን ንገራቸው፤ ‘ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት ሥጋ ትበላላችሁ፤ ሲነጋም እንጀራ ትበላላችሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ” በዚያች ምሽት ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤ በነጋውም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ተኝቶበት ነበር። ጤዛው ከረገፈ በኋላ በሜዳው ላይ ስስ የሆነ ዐመዳይ የሚመስል የተጋገረ ነገር በምድረ በዳው ላይ ታየ። እስራኤላውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ምን እንደ ሆነ ባለማወቃቸው እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ። ሙሴም፣ “ይህ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው አላቸው። እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳናችሁ ባለው ሰው ልክ ለእያንዳንዱ አንድ ጎሞር ውሰዱ’ ” ብሎ እግዚአብሔር አዝዟል። እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ አንዳንዶች አብዝተው፣ አንዳንዶች ደግሞ አሳንሰው ሰበሰቡ። የሰበሰቡትን በጎሞር በሰፈሩ ጊዜ፣ ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አልጐደለበትም፤ እያንዳንዱ የሰበሰበው የሚያስፈልገውን ያህል ሆነ።
ዘፀአት 16:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከኤሎም ተጓዙ፤ ከግብፅ ሀገር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር ከወሩም በዐሥራ አምስተኛው ቀን በኤሎምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ። የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አንጐራጐሩ። የእስራኤልም ልጆች አሉአቸው፥ “በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እስክንጠግብ ድረስ እንጀራና ሥጋ በምንበላበት ጊዜ በግብፅ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን! ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ እኛን ወደዚች ምድረ በዳ አምጥታችኋልና።” እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደ ሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ፥ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰብስቡ። እንዲህም ይሆናል፤ በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፤ ዕለት ዕለትም ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን” አለው። ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ፥ “እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር እንደ አወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ጥዋት ታያላችሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ያንጐራጐራችሁትን ሰምቶአልና፤ በእኛም ላይ የምታንጐራጕሩ እኛ ምንድን ነን?” አሉ። ሙሴም፥ “እግዚአብሔር ያንጐራጐራችሁበትን ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና በመሸ ጊዜ ትበሉ ዘንድ ሥጋን፥ በማለዳም ትጠግቡ ዘንድ እንጀራን እግዚአብሔር ይሰጣችኋል፤ እኛም ምንድን ነን? ማንጐራጐራችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በእኛ ላይ አይደለም” አለ። ሙሴም አሮንን፥ “ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ፦ ‘ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ’ በል” አለው። አሮንም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አቀኑ፤ እነሆም፥ የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ታየ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “የእስራኤልን ልጆች ማንጐራጐር ሰማሁ፦ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፤ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው።” እንዲህም ሆነ፤ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፤ ሰፈሩንም ሸፈኑት፤ በማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጠል ወድቆ ነበር። የወደቀው ጠል በአለፈ ጊዜ፥ እነሆ፥ በመሬት ላይ እንደ ውርጭ ነጭ ሆኖ ድንብላል የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ ታየ። የእስራኤልም ልጆች በአዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው፥ “ይህ ምንድን ነው?” ተባባሉ። ያ ምን እንደሆነ አላወቁምና። ሙሴም አላቸው፥ “ትበሉ ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ይህ ነው። ታደርጉት ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ እያንዳንዱ ሰው ለቤተ ሰቡ ለእያንዳንዱ አንድ ጎሞር ይሰብስብ፤ እንደ ቤተ ሰቡ ቍጥር ለእያንዳንዱ በድንኳኑ አብረውት ከሚኖሩት ጋር ይሰብስብ።” የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዱ አብዝቶ፥ አንዱም አሳንሶ ሰበሰበ። በጎሞርም በሰፈሩት ጊዜ እጅግ ለሰበሰበ አልተረፈውም፤ ጥቂትም ለሰበሰበ አልጐደለበትም፤ ሁሉም እያንዳንዱ ሰው ለየቤቱ ሰበሰበ።
ዘፀአት 16:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
መላው የእስራኤል ማኅበር ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ወር በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ከኤሊም ተነሥተው በኤሊምና በሲና መካከል ወደምትገኘው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። በምድረ በዳውም መላው የእስራኤል ልጆች ማኅበር በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ። እስራኤላውያንም እነርሱን እንዲህ አሏቸው፣ “በሥጋ መቀቀያው ምንቸት ዙሪያ ተቀምጠን የፈለግነውን ያህል ምግብ መመገብ በምንችልበት በግብጽ ሳለን፣ ምነው በእግዚአብሔር እጅ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! እናንተ ግን ይህ ሁሉ ጉባኤ በራብ እንዲያልቅ ወደዚህ ምድረ በዳ አመጣችሁን” አሏቸው። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ከሰማይ እንጀራ አዘንብላችኋለሁ። ሕዝቡም በየቀኑ እየወጡ ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰብስቡ፤ በዚህም ትእዛዞቼን ይጠብቁ እንደ ሆነ እፈትናቸዋለሁ። በስድስተኛው ቀን በሌሎቹ ዕለታት ከሚሰበስቡት ዕጥፍ ሰብስበው ያዘጋጁ።” ስለዚህ ሙሴና አሮን ለእስራኤላውያን ሁሉ፣ እንዲህ አሉ፤ “ከግብጽ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር መሆኑን በዛሬዪቱ ምሽት ታውቃላችሁ። በርሱ ላይ ያሰማችሁትን ማጕረምረም ሰምቷልና በማለዳ የእግዚአብሔርን ክብር ታያላችሁ፤ ለመሆኑ በእኛስ ላይ የምታጕረመርሙት እኛ ምንድን ነንና ነው?” አሏቸው። ሙሴም ንግግሩን በመቀጠል፣ “በርሱ ላይ ማጕረምረማችሁን ሰምቷልና በምሽት የምትበሉትን ሥጋ፣ በማለዳም የምትፈልጉትን ያህል እንጀራ በሚሰጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር መሆኑን ታውቃላችሁ፤ እኛ ማን ነን? በእኛ ላይ አይደለም ያጕረመረማችሁት፤ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ” አላቸው። ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ ‘ማጕረምረማችሁን እርሱ ሰምቷልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ’ ብለህ ለመላው የእስራኤል ማኅበር ተናገር” አለው። አሮንም ለመላው የእስራኤል ማኅበር ሲናገር ሳለ ወደ ምድረ በዳው ተመለከቱ፤ በዚያም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ላይ ተገልጦ ይታይ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤላውያንን ማጕረምረም ሰምቻለሁ፤ ይህን ንገራቸው፤ ‘ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት ሥጋ ትበላላችሁ፤ ሲነጋም እንጀራ ትበላላችሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ” በዚያች ምሽት ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤ በነጋውም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ተኝቶበት ነበር። ጤዛው ከረገፈ በኋላ በሜዳው ላይ ስስ የሆነ ዐመዳይ የሚመስል የተጋገረ ነገር በምድረ በዳው ላይ ታየ። እስራኤላውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ምን እንደ ሆነ ባለማወቃቸው እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ። ሙሴም፣ “ይህ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው አላቸው። እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳናችሁ ባለው ሰው ልክ ለእያንዳንዱ አንድ ጎሞር ውሰዱ’ ” ብሎ እግዚአብሔር አዝዟል። እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ አንዳንዶች አብዝተው፣ አንዳንዶች ደግሞ አሳንሰው ሰበሰቡ። የሰበሰቡትን በጎሞር በሰፈሩ ጊዜ፣ ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አልጐደለበትም፤ እያንዳንዱ የሰበሰበው የሚያስፈልገውን ያህል ሆነ።
ዘፀአት 16:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከኤሊምም ተጓዙ፥ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከግብፅ አገር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ። የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አንጎራጎሩ። የእስራኤልም ልጆች፦ ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ እኛን ወደዚች ምድረ በዳ አውጥታችኋል፤ በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እንጀራ ስንበላ ስንጠግብ ሳለን በግብፅ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን! አሉአቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይልቀሙ። እንዲህም ይሆናል፤ በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ ዕለት ዕለትም ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን አለው። ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ፦ እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር እንዳወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፥ የእግዚአብሔርንም ክብር ጥዋት ታያላችሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ያንጎራጎራችሁትን ሰምቶአልና በእኛም ላይ የምታንጎራጕሩ እኛ ምንድር ነን? አሉ። ሙሴም፦ እግዚአብሔር ያንጎራጎራችሁበትን ማንጎራጎራችሁን ሰምቶአልና በመሸ ጊዜ ትበሉ ዘንድ ሥጋን፥ ማልዶም ትጠግቡ ዘንድ እንጀራን እግዚአብሔር ይሰጣችኋል፤ እኛም ምንድር ነን? ማንጎራጎራችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በእኛ አይደለም አለ። ሙሴም አሮንን፦ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ፦ ማንጎራጎራችሁን ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ በል አለው። እንዲህም ሆነ፤ አሮን ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አቀኑ፤ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ታየ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ የእስራኤልን ልጆች ማንጎራጎር ሰማሁ፦ ወደ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፥ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው። እንዲህም ሆነ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፥ ሰፈሩንም ከደኑት ማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጠል ወድቆ ነበር። የወደቀውም ጠል ባለፈ ጊዜ፥ እነሆ በመሬት ላይ እንደ ደቃቅ ውርጭ ሆኖ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ ታየ። የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደ ሆነ አላወቁምና እርስ በእርሳቸው፦ ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። ሙሴም፦ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው። እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይልቀም በድኳኑ ባሉት ነፍሶች ቁጥር ለአንድ ሰው አንድ ጎሞር ውሰዱ አላቸው። የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዱ አብዝቶ አንዱም እሳንሶ ለቀመ። በጎሞርም በሰፈሩት ጊዜ እጅግ ለለቀመ አልተረፈውም ጥቂትም ለለቀመ አልጎደለበትም፤ ሁሉ እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ለቀመ።
ዘፀአት 16:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
መላው የእስራኤል ማኅበር ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ወር፥ በዐሥራ አምስተኛው ቀን፥ ከኤሊም ተነሥተው በሲና እና በኤሊም መካከል ወዳለው “ሲን” ተብሎ ወደሚጠራው ምድረ በዳ መጡ። በዚያም ምድረ በዳ ሁሉም ተባብረው በሙሴና በአሮን ላይ በማጒረምረም እንዲህ አሉ፦ “ምነው በግብጽ ሳለን እግዚአብሔር በገደለን ኖሮ፥ በዚያ ሌላው ቢቀር ሥጋም ሆነ ሌላ ምግብ የፈለግነውን ያኽል መመገብ እንችል ነበረ፤ እናንተ ግን ሁላችንም በራብ እንድናልቅ ወደዚህ በረሓ አወጣችሁን።” እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ እኔ ለሁላችሁም የሚበቃ ምግብ ከሰማይ ላዘንብላችሁ ነው፤ ሕዝቡ በየዕለቱ ወጥተው ለዚያው ቀን የሚበቃቸውን ምግብ ይሰብስቡ፤ በዚህ ዐይነት እኔ የምሰጣቸውን መመሪያ ይጠብቁ እንደ ሆነ እፈትናቸዋለሁ። በስድስተኛው ቀን ግን፥ ከሌሎቹ ዕለቶች በአንዱ ቀን የሚሰበስቡትን እጥፍ ሰብስበው ያዘጋጁ።” ስለዚህ ሙሴና አሮን ለመላው የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አሉ፦ “ከግብጽ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር መሆኑን በዛሬይቱ ምሽት ታውቃላችሁ፤ በማለዳ የእግዚአብሔርን ክብር ታያላችሁ፤ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ሰምቶአል፤ በእኛ ላይ የምታጒረመርሙት እኛ ማን ነን?” ከዚህም በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፦ “በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ስለ ሰማ በማታ የምትበሉትን ሥጋና በማለዳ ደግሞ የፈለጋችሁትን ያኽል እንጀራ የሚሰጣችሁ እግዚአብሔር ነው፤ እኛ ምንድን ነን? በእኛ ላይ ስታጒረመርሙ በእግዚአብሔር ላይ ማጒረምረማችሁ ነው።” ሙሴ አሮንን፦ “እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ስለ ሰማ፥ መላው የእስራኤል ማኅበር መጥታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቁሙ ብለህ ንገራቸው” አለው። አሮንም ለመላው ማኅበር በተናገረ ጊዜ ፊታቸውን ወደ በረሓው አዞሩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር በደመና ተገለጠ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያን በእኔ ላይ ማጒረምረማቸውን ሰምቼአለሁ፤ ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በዛሬው ምሽት ፀሐይ ከመጥለቅዋ በፊት ምግብ የሚሆናችሁን ሥጋ ታገኛላችሁ፤ በማለዳም የምትፈልጉትን ያኽል እንጀራ ታገኛላችሁ፤ በዚያን ጊዜም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ።’ ” በምሽትም ብዙ ድርጭቶች እየበረሩ መጥተው ሰፈሩን ሸፈኑት፤ በማለዳ ደግሞ በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ነበረ፤ ጤዛውም ከተነነ በኋላ ደቃቅና ስስ የሆነ ነገር በበረሓማው ምድር ላይ ታየ፤ እርሱም በምድር ላይ ያረፈ ዐመዳይ ይመስል ነበር። እስራኤላውያን ባዩት ጊዜ ምን እንደ ሆነ ባለማወቃቸው “ይህ ነገር ምንድን ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ሙሴም እንዲህ አላቸው፦ “ይህ እንድትበሉት እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው፤ ከእናንተ እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያኽል ብቻ እንዲሰበስብ እግዚአብሔር አዞአል፤ ስለዚህ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አንድ ኪሎ ተኩል ይውሰድ።” እስራኤላውያንም እንደዚሁ አደረጉ፤ አንዳንዶቹ ብዙ አንዳንዶቹ ጥቂት ሰበሰቡ፤ በሰፈሩትም ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አላነሰበትም፤ እያንዳንዱ የሰበሰበው ልክ የሚበቃውን ያኽል ነበር።
ዘፀአት 16:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከኤሊምም ተነሱ፥ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከግብጽ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር፥ በዓሥራ አምስተኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ። የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ። የእስራኤልም ልጆች እንዲህ አሉአቸው፦ “በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን ሳለን፥ ምግብ ተትረፍርፎ ስንበላ ሳለን፥ በግብጽ ምድር ሳለን በጌታ እጅ ምነው በሞትን! ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ ወደዚህ ምድረ በዳ አወጣችሁን።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ ከሰማይ እንጀራን ላዘንብላችሁ ነው፤ ሕዝቡም ወጥተው ለቀኑ የሚበቃቸውን በቀኑ ይልቀሙ በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እፈትናቸዋለሁ። እንዲህም ይሆናል በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ በየቀኑ ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን።” ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ አሉ፦ “ጌታ ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፥ በጥዋትም የጌታን ክብር ታያላችሁ፤ ምክንያቱም በጌታ ላይ ያጉረመረማችሁትን ሰምቶአልና፥ በእኛም ላይ የምታጉረመርሙ እኛ ምንድን ነን?” ሙሴም፦ “ጌታ በማታ የምትበሉትን ሥጋና በማለዳ ደግሞ የሚያጠግባችሁን ምግብ ሲሰጣችሁ ጌታ ያጉረመረማችሁበትን ማጉረምረም ሰምቶ ነው፤ እኛ ምንድን ነን? ማጉረምረማችሁ በጌታ ላይ ነው እንጂ በእኛ ላይ አይደለም” አለ። ሙሴም አሮንን፦ “ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ‘ማጉረምረማችሁን ሰምቶአልና ወደ ጌታ ፊት ቅረቡ በላቸው’” አለው። እንዲህም ሆነ አሮን ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አዞሩ፤ እነሆም የጌታ ክብር በደመናው ታየ። ጌታም ሙሴን አለው፦ የእስራኤልን ልጆች ማጉረምረማቸውን ሰማሁ፦ እንዲህ በላቸው “ወደ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፥ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።” እንዲህም ሆነ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፥ ሰፈሩንም ሸፈኑት ማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ነበር። ጤዛውም ከተነነ በኋላ፥ በመሬት ላይ ስስ የሆነ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ መሬት ላይ ታየ። የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደሆነ አላወቁምና ሁሉም ሰው ወንድሙን፦ “ይህ ምንድነው?” በማለት ተጠያየቁ። ሙሴም፦ “እንድትበሉት ጌታ የሰጣችሁ ምግብ ነው።” ጌታ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ “እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳኑ ባሉት ነፍሶች ቍጥር ለአንድ ሰው አንድ ዖሜር ይውሰድ።” የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዳንዶቹ ብዙ አንዳንዶቹ ጥቂት ሰበሰቡ። በዖሜርም በሰፈሩት ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም ጥቂት የሰበሰበውም አላነሰውም፤ የሰበሰቡት እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ነው።