ከኤሊምም ተነሱ፥ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከግብጽ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር፥ በዓሥራ አምስተኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ። የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ። የእስራኤልም ልጆች እንዲህ አሉአቸው፦ “በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን ሳለን፥ ምግብ ተትረፍርፎ ስንበላ ሳለን፥ በግብጽ ምድር ሳለን በጌታ እጅ ምነው በሞትን! ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ ወደዚህ ምድረ በዳ አወጣችሁን።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ ከሰማይ እንጀራን ላዘንብላችሁ ነው፤ ሕዝቡም ወጥተው ለቀኑ የሚበቃቸውን በቀኑ ይልቀሙ በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እፈትናቸዋለሁ። እንዲህም ይሆናል በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ በየቀኑ ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን።” ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ አሉ፦ “ጌታ ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፥ በጥዋትም የጌታን ክብር ታያላችሁ፤ ምክንያቱም በጌታ ላይ ያጉረመረማችሁትን ሰምቶአልና፥ በእኛም ላይ የምታጉረመርሙ እኛ ምንድን ነን?” ሙሴም፦ “ጌታ በማታ የምትበሉትን ሥጋና በማለዳ ደግሞ የሚያጠግባችሁን ምግብ ሲሰጣችሁ ጌታ ያጉረመረማችሁበትን ማጉረምረም ሰምቶ ነው፤ እኛ ምንድን ነን? ማጉረምረማችሁ በጌታ ላይ ነው እንጂ በእኛ ላይ አይደለም” አለ። ሙሴም አሮንን፦ “ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ‘ማጉረምረማችሁን ሰምቶአልና ወደ ጌታ ፊት ቅረቡ በላቸው’” አለው። እንዲህም ሆነ አሮን ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አዞሩ፤ እነሆም የጌታ ክብር በደመናው ታየ። ጌታም ሙሴን አለው፦ የእስራኤልን ልጆች ማጉረምረማቸውን ሰማሁ፦ እንዲህ በላቸው “ወደ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፥ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።” እንዲህም ሆነ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፥ ሰፈሩንም ሸፈኑት ማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ነበር። ጤዛውም ከተነነ በኋላ፥ በመሬት ላይ ስስ የሆነ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ መሬት ላይ ታየ። የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደሆነ አላወቁምና ሁሉም ሰው ወንድሙን፦ “ይህ ምንድነው?” በማለት ተጠያየቁ። ሙሴም፦ “እንድትበሉት ጌታ የሰጣችሁ ምግብ ነው።” ጌታ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ “እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳኑ ባሉት ነፍሶች ቍጥር ለአንድ ሰው አንድ ዖሜር ይውሰድ።” የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዳንዶቹ ብዙ አንዳንዶቹ ጥቂት ሰበሰቡ። በዖሜርም በሰፈሩት ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም ጥቂት የሰበሰበውም አላነሰውም፤ የሰበሰቡት እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ነው።
ኦሪት ዘፀአት 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 16:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች