የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 16

16
1ከኤሊምም ተጓዙ፥ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከግብፅ አገር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ። 2የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አንጎራጎሩ። 3የእስራኤልም ልጆች፦ ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ እኛን ወደዚች ምድረ በዳ አውጥታችኋል፤ በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እንጀራ ስንበላ ስንጠግብ ሳለን በግብፅ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን! አሉአቸው። 4እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይልቀሙ። 5እንዲህም ይሆናል፤ በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ ዕለት ዕለትም ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን አለው። 6ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ፦ እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር እንዳወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፥ 7የእግዚአብሔርንም ክብር ጥዋት ታያላችሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ያንጎራጎራችሁትን ሰምቶአልና በእኛም ላይ የምታንጎራጕሩ እኛ ምንድር ነን? አሉ። 8ሙሴም፦ እግዚአብሔር ያንጎራጎራችሁበትን ማንጎራጎራችሁን ሰምቶአልና በመሸ ጊዜ ትበሉ ዘንድ ሥጋን፥ ማልዶም ትጠግቡ ዘንድ እንጀራን እግዚአብሔር ይሰጣችኋል፤ እኛም ምንድር ነን? ማንጎራጎራችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በእኛ አይደለም አለ። 9ሙሴም አሮንን፦ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ፦ ማንጎራጎራችሁን ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ በል አለው። 10እንዲህም ሆነ፤ አሮን ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አቀኑ፤ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ታየ። 11-12እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ የእስራኤልን ልጆች ማንጎራጎር ሰማሁ፦ ወደ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፥ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው። 13እንዲህም ሆነ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፥ ሰፈሩንም ከደኑት ማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጠል ወድቆ ነበር። 14የወደቀውም ጠል ባለፈ ጊዜ፥ እነሆ በመሬት ላይ እንደ ደቃቅ ውርጭ ሆኖ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ ታየ። 15የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደ ሆነ አላወቁምና እርስ በእርሳቸው፦ ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። ሙሴም፦ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው። 16እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይልቀም በድኳኑ ባሉት ነፍሶች ቁጥር ለአንድ ሰው አንድ ጎሞር ውሰዱ አላቸው። 17የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዱ አብዝቶ አንዱም እሳንሶ ለቀመ። 18በጎሞርም በሰፈሩት ጊዜ እጅግ ለለቀመ አልተረፈውም ጥቂትም ለለቀመ አልጎደለበትም፤ ሁሉ እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ለቀመ። 19ሙሴም፦ ማንም ከእርሱ አንዳች ለነገ አያስቀር አላቸው። 20ነገር ግን ሙሴን አልሰሙትም፤ አንዳንድ ሰዎችም ከእርሱ ለነገ አስቀሩ፥ እርሱም ተላ ሸተተም፤ ሙሴም ተቆጣቸው። 21ሰውም ሁሉ ዕለት ዕለት የሚበላውን ያህል በጥዋት ለቀመ፤ ፀሐይም በተኮሰ ጊዜ ቀለጠ። 22እንዲህም ሆነ፤ በስድስተኛው ቀን ሁለት እጥፍ አድርገው እያንዳንዳቸው ሁለት ጎሞር እንጀራ ለቀሙ፤ የማኀበሩም አለቆች ሁሉ መጥተው ለሙሴ ነገሩት። 23እርሱም፦ እግዚአብሔር የተናገረው ይህ ነው፦ ነገ ዕረፍት፥ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ሰንበት ነው፤ የምትጋግሩትን ጋግሩ፥ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፥ የተረፈውን ሁሉ ለነገ እንዲጠበቅ አኑሩት አላቸው። 24ሙሴም እንዳዘዘ ለነገ አኖሩት፤ አልሸተተም፥ ትልም አልሆነበትም። 25ሙሴም፦ የእግዚአብሔር ሰንበት ዛሬ ነውና ብሉት፤ ዛሬ በሜዳ አታገኙትም። 26ስድስት ቀን ልቀሙት ሰባተኛው ቀን ግን ሰንበት ነው፤ በእርሱ አይገኝም አለ። 27በሰባተኛውም ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሕዝቡ አንዳንድ ሰዎች ሊለቅሙ ወጡ፥ ምንም አላገኙም። 28እግዚአብሔርም ሙሴን፦ ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ለመጠበቅ እስከ መቼ እንቢ ትላላችሁ? 29እግዚአብሔር ሰንበትን እንደ ሰጣችሁ እዩ፤ ስለዚህ በስድስተኛው ቀን የሁለት ቀን እንጀራ ሰጣችሁ፤ ሰው ሁሉ በስፍራው ይቀመጥ፥ በሰባተኛው ቀን ማንም ከስፍራው አይሂድ አለው። ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፈ። 30የእስራኤልም ወገን ስሙን መና ብለው ጠሩት፤ 31እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ ነው፤ ጣዕሙም እንደ ማር ቂጣ ነው። 32ሙሴም፦ እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ ከግብፅ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ ያበላኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ ከእርሱ አንድ ጎሞር ሙሉ ለልጅ ልጆቻችሁ ይጠበቅ አለ። 33ሙሴም እሮንን፦ አንድ ማድጋ ወስደህ ጎሞር ሙሉ መና አግባበት፥ ለልጅ ልጃችሁም ይጠበቅ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት አኑረው አለው። 34እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ይጠበቅ ዘንድ አሮን በምስክሩ ፊት አኖረው። 35የእስራኤልም ልጆች ወደሚኖሩባት ምድር እስኪመጡ ድረስ አርባ ዓመት መና በሉ፤ ወደ ከነዓን ምድር ድንበር እስኪመጡ ድረስ መና በሉ። 36ጎሞርም የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ