አስቴር 9:20-32

አስቴር 9:20-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

መርዶክዮስ የተፈጸሙትን እነዚህን ድርጊቶች ጻፈ፤ ደብዳቤ አዘጋጅቶም በመላው የንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃ በቅርብና በሩቅ ለሚገኙት አይሁድ ሁሉ ላከ፤ የላከውም የአዳርን ወር ዐሥራ አራተኛና ዐሥራ ዐምስተኛ ቀን በየዓመቱ እንዲያከብሩ ነው፤ የሚያከብሩበትም ምክንያት አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍት ያገኙበት፣ ሐዘናቸው ወደ ደስታ፣ ልቅሷቸውም ወደ ክብረ በዓል የተለወጠበት ቀን ስለ ሆነ ነው። ቀኖቹንም የተድላና የደስታ ቀኖች አድርገው፣ እርስ በርሳቸውም የምግብ ስጦታ እየተለዋወጡና ለድኾችም ስጦታ እየሰጡ እንዲያከብሩ ጻፈላቸው። ስለዚህ አይሁድ መርዶክዮስ የጻፈላቸውን ለመፈጸምና የጀመሩትን በዓል ለማክበር ተስማሙ፤ ምክንያቱም የአይሁድ ሁሉ ጠላት የሆነው የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ አይሁድን ለማጥፋት አሢሮ ነበር፤ ሊፈጃቸውና ሊያጠፋቸውም ፉር የተባለ ዕጣ ጥሎ ነበር። ሤራው በንጉሡ ዘንድ እንደ ታወቀ ሐማ በአይሁድ ላይ የሸረበው ሤራ በገዛ ራሱ ላይ እንዲጠመጠም፣ እርሱና ወንዶች ልጆቹም በዕንጨት ላይ እንዲሰቀሉ የጽሑፍ ትእዛዝ አስተላለፈ። ስለዚህ እነዚህ ቀኖች ፉር ከሚለው ቃል “ፉሪም” ለመባል በቁ። በዚህ ደብዳቤ ስለ ተጻፈው ሁሉ፣ ስላዩትና ስለ ደረሰባቸውም ነገር ሁሉ፣ አይሁድ በታዘዘውና በተወሰነው ጊዜ እነርሱና ዘሮቻቸው፣ እነርሱን የተጠጓቸውም ሁሉ እነዚህን ሁለት ቀኖች በየዓመቱ ባለማቋረጥ እንዲያከብሩ ሥርዐት አድርገው ራሳቸው ወሰኑ። እነዚህም ቀኖች በእያንዳንዱ ትውልድ፣ በእያንዳንዱ ቤተ ሰብ፣ በእያንዳንዱ አውራጃና በእያንዳንዱ ከተማ መታሰብና መከበር ይኖርባቸዋል፤ ይኸውም እነዚህ የፉሪም ቀኖች በአይሁድ ዘንድ ሳይከበሩ እንዳይቀሩ፤ መታሰቢያቸውም ከዘሮቻቸው መካከል እንዳይደመሰስ ነው። ስለዚህ የአቢካኢል ልጅ ንግሥት አስቴር ከአይሁዳዊው ከመርዶክዮስ ጋራ በመሆን፣ ፉሪምን አስመልክተው ይህችን ሁለተኛዪቱን ደብዳቤ ለማጽናት በሙሉ ሥልጣን ጻፉ። መርዶክዮስም የመልካም ምኞት መግለጫና ማረጋገጫ የሆነውን ደብዳቤ በጠረክሲስ ግዛት ውስጥ በሚገኙት አንድ መቶ ሃያ ሰባት አውራጃዎች ለሚኖሩት አይሁድ ሁሉ ላከ፤ የላከውም አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥት አስቴር ባወጁላቸውና እንደዚሁም የጾሙንና የሰቈቃውን ጊዜ በሚመለከት ለራሳቸውና ለዘራቸው ባጸኑት ውሳኔ መሠረት እነዚህ የፉሪም ቀኖች በተወሰነላቸው ጊዜ እንዲከበሩ ነው። የአስቴር ዐዋጅ ስለ ፉሪም የወጣውን ሥርዐት አጸና፤ ይህም በመዝገብ ተጻፈ።

አስቴር 9:20-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

መርዶክዮስም ይህን ነገር ጻፈ፥ በንጉሡም በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በቅርብና በሩቅ ወዳሉት አይሁድ ሁሉ ደብዳቤዎችን ላከ። በየዓመቱም አዳር በሚባለው ወር አሥራ አራተኛውና አሥራ አምስተኛው ቀን፥ አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍትን ያገኙበት ቀን፥ ወሩም ከኀዘን ወደ ደስታ ከልቅሶም ወደ መልካም ቀን የተለወጠበት ወር ሆኖ ይጠብቁት ዘንድ፥ የግብዣና የደስታም ቀን፥ እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበትና ለድሆች ስጦታ የሚሰጡበት ቀን ያደርጉት ዘንድ አዘዛቸው። አይሁድም ለመሥራት የጀመሩትን፥ መርዶክዮስም የጻፈላቸውን ያደርጉ ዘንድ ተቀበሉት፥ አጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ የአይሁድ ሁሉ ጠላት ሐማ አይሁድን ያጠፋ ዘንድ ተተንኵሎ ነበር፥ ሊደመስሳቸውና ሊያጠፋቸውም ፉር የሚባል ዕጣ ጥሎ ነበር። አስቴርም ወደ ንጉሡ ፊት በገባች ጊዜ በአይሁድ ላይ የተተነኰለው ክፉ ተንኰል በራሱ ላይ እንዲመለስ፥ እርሱና ልጆቹም በግንድ ላይ እንዲሰቀሉ በደብዳቤው አዘዘ። ስለዚህም እነዚህ ቀኖች እንደ ፉርስም ፉሪም ተባሉ። በዚህም ደብዳቤ ስለ ተጻፈው ቃል ሁሉ፥ ስላዩትና ስላገኙአቸውም ነገር ሁሉ፥ አይሁድ እነዚህን ሁሉ ቀኖች እንደ ጽሕፈቱና እንደ ጊዜው በየዓመቱ ይጠብቁ ዘንድ፥ እነዚህም ቀኖች በየትውልዳቸውና በየወገናቸው በየአገራቸውም በየከተማቸውም የታሰቡና የተከበሩ ይሆኑ ዘንድ፥ እነዚህም የፉሪም ቀኖች በአይሁድ ዘንድ እንዳይሻሩ፥ መታሰባቸውም ከዘራቸው እንዳይቈረጥ፥ በራሳቸውና በዘራቸው ወደ እነርሱም በተጠጉት ሁሉ ላይ እንዳይቀር ሥርዓት አድርገው ተቀበሉ። የአቢካኢልም ልጅ ንግሥቲቱ አስቴርና አይሁዳዊው መርዶክዮስ ይህችን ስለ ፉሪም የምትናገረውን ሁለተኛይቱን ደብዳቤ በሥልጣናቸው ሁሉ ያጸኑአት ዘንድ ጻፉ። ደብዳቤዎቹንም በአርጤክስስ መንግሥት በመቶ ሀያ ሰባቱ አገሮች ወዳሉ አይሁድ ሁሉ በሰላምና በእውነት ቃል ላኩ። እነዚህንም የፉሪም ቀኖች፥ አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥቲቱ አስቴር እንዳዘዙ፥ ለራሳቸውና ለዘራቸውም የጾማቸውንና የልቅሶአቸውን ነገር ለማክበር እንደ ተቀበሉ፥ በየጊዜያቸው ያጸኑ ዘንድ ጻፉ። የአስቴርም ትእዛዝ ይህን የፉሪምን ነገር አጸና፥ በመጽሐፍም ተጻፈ።

አስቴር 9:20-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

መርዶክዮስም የዚህን ሁሉ ድርጊት ታሪክ ጽፎ በመላው የፋርስ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ውስጥ በቅርብም በሩቅም ወደሚኖሩት አይሁድ ሁሉ በደብዳቤ ላከው። በየዓመቱ የአዳርን ወር ዐሥራ አራተኛና ዐሥራ አምስተኛ ቀን በዓል አድርገው በማክበር እንዲጠብቁት ነገራቸው። እነዚህም ዕለቶች አይሁድ ራሳቸውን ከጠላቶቻቸው እጅ በማዳን ዕረፍት ያገኙባቸው ቀኖች ናቸው፤ ከሐዘንና ከተስፋ መቊረጥ ወደ ደስታና ወደ ሐሴት የተላለፉት በዚህ ወር ነበር፤ በእነዚህ ዕለቶች በዓል አድርገው በመብላትና በመጠጣት እየተደሰቱ፥ እርስ በርሳቸው አንዳቸው ለሌላው የምግብ ስጦታ እየተለዋወጡና ለድኾችም ስጦታ እየሰጡ እንዲጠብቁአቸው ተነገራቸው። ስለዚህም አይሁድ የመርዶክዮስን መመሪያ በመቀበል በዚህ ሁኔታ የተጀመረው በዓል በየዓመቱ እንዲከበር ለማድረግ ተስማሙ። የአይሁድ ጠላት የነበረው የአጋግ ዘር የሆነው የሃመዳታ ልጅ ሃማን፥ ፑሪም ተብለው የሚጠሩትን ዕጣዎች በመጣል አይሁድ በሙሉ ከምድረ ገጽ ጠራርጎ ለማጥፋት የሚችልበትን ዕለት ለማወቅ ዐቅዶ ነበር። ነገር ግን አስቴር ወደ ንጉሡ ቀረበች፤ ንጉሡም ትእዛዙን በጽሑፍ እንዲተላለፍ አደረገ፤ ያም ትእዛዝ ባስገኘው ውጤት ሃማን አይሁድን ለመደምሰስ ዐቅዶት የነበረው ሤራ በራሱ ላይ እንዲመለስበት ሆነ፤ እርሱና ዐሥር ልጆቹ በእንጨት ላይ ተሰቀሉ። እነዚህ የበዓላት ቀኖች “ፑሪም” ተብለው የሚጠሩትም በዚሁ ምክንያት ነው፤ መርዶክዮስ የላከውን ደብዳቤ መሠረት በማድረግና በዐይናቸው ያዩትንና የደረሰባቸውንም ነገር ሁሉ በማስታውስ፥ አይሁድ ለራሳቸው፥ ለዘሮቻቸው አይሁዳዊ መሆን ለሚፈልግ ሁሉ ቋሚ ደንብ አደረጉ፤ ይኸውም በየዓመቱ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ መርዶክዮስ በሰጠው መመሪያ መሠረት እነዚህ ሁለት ቀኖች ባለማቋረጥ ይከበራሉ። እነዚህ የፑሪም ቀኖች በየትውልዱ፥ በየቤተሰቡ፥ በየሀገሩና በየከተማው መከበር እንዳለባቸው ተወሰነ፤ እነዚህም ቀኞች ሳይከበሩ መቅረት የለባቸውም፤ ከትውልዱም መካከል መታሰቢያነታቸው መቋረጥ የለበትም። ከዚህም ሁሉ በኋላ የአቢኀይል ልጅ ንግሥት አስቴር ከመርዶክዮስ ጋር በመተባበር ስለ ፑሪም፥ መርዶክዮስ ቀደም ሲል የላከውን ደብዳቤ በማጠናከር ያላትን ሥልጣን የሚገልጥ ትእዛዝ ያለበት ደብዳቤ ጽፋ ላከች። ደብዳቤውም በአይሁድ አድራሻ የተጻፈ ሲሆን ቅጂው ግን በፋርስ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ውስጥ ላሉት ለመቶ ኻያ ሰባት አገሮች ሁሉ ተልኮ ነበር፤ የደብዳቤውም መልእክት ለአይሁድ ሰላምንና በደኅንነት የመኖርን መልካም ምኞት የሚገልጥ ነበር። ከዚህም ጋር ከአሁን በፊት ለጾምና ለሐዘን ደንብ አውጥተው በነበረው ዐይነት እነዚህን የፑሪም ዕለቶች እነርሱ ራሳቸውም ሆኑ ወደፊት የሚነሡት ዘሮቻቸው በየዓመቱ በማክበር ይጠብቁአቸው ዘንድ ይጠይቃል፤ ይህም ንግሥት አስቴርና መርዶክዮስ በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ሁለቱም ያስተላለፉት ትእዛዝ ነበር። ስለ ፑሪም ሕግና ሥርዓት የተነገረውን ለማጠናከር ንግሥት አስቴር የላከችው የደብዳቤ ትእዛዝ በልዩ የብራና ጥቅል እንዲጻፍ ተደረገ።