ኤፌሶን 6:16-20
ኤፌሶን 6:16-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከእነዚህም ሁሉ ጋር፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንን ራስ ቍር አድርጉ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ፤ ይህንም በማሰብ ንቁ፤ ስለ ቅዱሳንም ሁሉ በትጋት ልመና አቅርቡ። የወንጌልን ምስጢር ለመግለጥ አፌን በምከፍትበት ጊዜ ሁሉ በድፍረት እንድናገር ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ጸልዩልኝ። በሰንሰለት የታሰረ መልእክተኛ የሆንሁት ለዚሁ ነውና። ስለዚህ መናገር የሚገባኝን ያለ ፍርሀት እንድናገር ጸልዩልኝ።
ኤፌሶን 6:16-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም ሁሉ ጋር የሚንበለበሉ የክፉን ፍላፃዎች ሁሉ ማጥፋት እንድትችሉ የእምነትን ጋሻ አንሡ። የመዳንንም የራስ ቍር በራሳችሁ ላይ ጫኑ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ሰይፍ ያዙ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በጸሎትና በምልጃ ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ ከዚህም ጋር ስለ ቅዱሳን ሁሉ ለመጸለይ ሁልጊዜ ትጉ፤ ለእኔም፦ ቃልን እንዲሰጠኝ፥ አፌንም ከፍቼ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንድናገር ጸልዩልኝ። ስለ ወንጌልም በእስራት መልእክተኛ የሆንሁ፦ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ጸልዩ።
ኤፌሶን 6:16-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤ ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤ ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ።
ኤፌሶን 6:16-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህም ሁሉ በላይ እንደ እሳት የሚንበለበሉትን የዲያብሎስን ፍላጻዎች ሁሉ ማጥፋት የምትችሉበትን እምነት እንደ ጋሻ አንግቡ። መዳንን እንደ ራስ ቊር በራሳችሁ ላይ ድፉ፤ እንዲሁም ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን ሰይፍ ይኸውም የእግዚአብሔርን ቃል ያዙ። ዘወትር በመንፈስ ቅዱስ እየተመራችሁ ጸሎትንና ልመናን አቅርቡ። በዚህም መሠረት እግዚአብሔር ለቀደሳቸው ሰዎች ነቅታችሁና ተግታችሁ ጸልዩ። የወንጌልን ምሥጢር ያለ ፍርሀት እንድገልጥ በምናገርበት ጊዜ አስፈላጊውን ቃል እንዲሰጠኝ ለእኔም ጸልዩልኝ። አሁንም በሰንሰለት ታስሬ የዚሁ ወንጌል መልእክተኛ ነኝ፤ ስለዚህ እንደሚገባኝ ያለ ፍርሀት እንድናገር ጸልዩልኝ።
ኤፌሶን 6:16-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የመዳንንም ራስ ቁር፥ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ። በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ እስከ መጨረሻው በጽናት ትጉ። ቃል እንዲሰጠኝና አፌን በመክፈት የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ፥ ስለ እኔም ለምኑ። ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንኩ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጽ እድናገር ለምኑ።