የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6

6
ስለ ልጆችና ስለ ወላጆች
1 # ቈላ. 3፥20። ልጆች ሆይ! ተገቢ ነውና ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ። 2#ዘፀ. 20፥12፤ ዘዳ. 5፥16። “አባትህንና እናትህን አክብር፤” ከተስፋ ቃል ጋር የተሰጠ የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው፤ 3“መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” 4#ቈላ. 3፥21።እናንተም አባቶች ሆይ! ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው።
ስለ አገልጋዮችና ስለ ጌቶች
5 # ቈላ. 3፥22-25። አገልጋዮች ሆይ! ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ፥ በልባችሁ ቅንነት በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ 6የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባርያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። 7ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታገለግሉ በጽኑ ፍላጎት ተገዙ፤ 8ባርያም ሆነ ነጻ ሰው፥ እያንዳንዱ ለሚያደርገው መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ ብድራቱን እንደሚቀበል ታውቃላችሁ። 9#ቈላ. 4፥1፤ ዘዳ. 10፥17፤ ቈላ. 3፥25።እናንተም ጌቶች ሆይ! ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንደማያዳላ ታውቃላችሁ።
የእግዚአብሔር የጦር መሣሪያ
10በተረፈ በጌታ በኃይሉ ብርታትም ጠንክሩ። 11#ጥበ. 5፥17።የዲያብሎስን ሽንገላ ለመቃወም እንድትችሉ፥ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ። 12ተጋድሏችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም፤ ነገር ግን ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር፥ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር፥ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው። 13ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን የጦር ትጥቅ አንሡ። 14#ጥበ. 5፥18-23።#ኢሳ. 11፥5፤ ኢሳ. 59፥17።#ኢሳ. 52፥7።እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ 15የሰላም ወንጌል ለማወጅ በዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤ 16በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ 17#ኢሳ. 59፥17።የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የመዳንንም ራስ ቁር፥ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ። 18በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ እስከ መጨረሻው በጽናት ትጉ። 19ቃል እንዲሰጠኝና አፌን በመክፈት የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ፥ ስለ እኔም ለምኑ። 20ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንኩ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጽ እድናገር ለምኑ።
የመጨረሻ ሰላምታ
21 # የሐዋ. 20፥4፤ 2ጢሞ. 4፥12። # ቈላ. 4፥7-8። እናንተ ደግሞ በምን ሁኔታ እንዳለሁና እንዴት እንደምኖር እንድታውቁት የተወደደ ወንድምና በጌታ የታመነ አገልጋይ ቲኪቆስ ሁሉን ይነግራችኋል፤ 22ስለ እኛ ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ወደ እናንተ የምልከው በዚህ ምክንያት ነው።
23ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን። 24ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ