መክብብ 1:1-18

መክብብ 1:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ለእ​ስ​ራ​ኤል የነ​ገሠ የዳ​ዊት ልጅ የሰ​ባ​ኪው የሰ​ሎ​ሞን ቃል። ሰባ​ኪው፥ “ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከ​ንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው” ይላል። ከፀ​ሐይ በታች በሚ​ደ​ክ​ም​በት ድካም ሁሉ የሰው ትርፉ ምን​ድን ነው? ትው​ልድ ያል​ፋል፥ ትው​ል​ድም ይመ​ጣል፤ ምድር ግን ለዘ​ለ​ዓ​ለም ጸንታ ትኖ​ራ​ለች። ፀሐይ ይወ​ጣል፥ ፀሐ​ይም ይገ​ባል፥ ወደ​ሚ​ወ​ጣ​በ​ትም ስፍራ ይመ​ለ​ሳል፤ ወደ ቀኝ ይመ​ለ​ሳል፥ ወደ ሰሜ​ንም ይዞ​ራል፤ ነፋስ ዙሪ​ያ​ዉን ዙሮ ይሄ​ዳል፥ ነፋ​ስም በዙ​ረቱ ይመ​ለ​ሳል። ፈሳ​ሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄ​ዳሉ፥ ባሕሩ ግን አይ​ሞ​ላም፤ ፈሳ​ሾች ወደ​ሚ​ሄ​ዱ​በት ስፍራ እንደ ገና ወደ​ዚያ ይመ​ለ​ሳሉ። ነገር ሁሉ ያደ​ክ​ማል፤ ሰውም ይና​ገ​ረው ዘንድ አይ​ች​ልም፥ ዐይን በማ​የት አይ​ጠ​ግ​ብም፥ ጆሮም በመ​ስ​ማት አይ​ሞ​ላም። የሆ​ነው ነገር እርሱ የሚ​ሆን ነው፥ የተ​ደ​ረ​ገ​ውም ነገር እርሱ የሚ​ደ​ረግ ነው፥ ከፀ​ሐ​ይም በታች ከተ​ደ​ረ​ገው ሁሉ አዲስ ነገር የለም። እነሆ፥ “ይህ ነገር አዲስ ነው” ብሎ የሚ​ና​ገር ማን ነው? እርሱ ከእኛ በፊት በነ​በ​ሩት ዘመ​ናት ተደ​ር​ጓል። ለፊ​ተ​ኞቹ ነገ​ሮች መታ​ሰ​ቢያ የላ​ቸ​ውም፤ ለኋ​ለ​ኞ​ቹም ነገ​ሮች ከእ​ነ​ርሱ በኋላ በሚ​ነ​ሡት ሰዎች ዘንድ መታ​ሰ​ቢያ አይ​ገ​ኝ​ላ​ቸ​ውም። እኔ ሰባ​ኪው በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ንጉሥ ነበ​ርሁ። ከሰ​ማ​ይም በታች ስለ​ተ​ደ​ረ​ገው ሁሉ በጥ​በብ ለመ​መ​ር​መ​ርና ለመ​ፈ​ተን ልቤን አተ​ጋሁ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይደ​ክ​ሙ​በት ዘንድ ክፉ ድካ​ምን ለሰው ልጆች ሰጥ​ት​ዋ​ልና። ከፀ​ሐይ በታች የተ​ሠ​ራ​ውን ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እነ​ሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋ​ስ​ንም እንደ መከ​ተል ነው። ጠማማ ይቀና ዘንድ አይ​ች​ልም፤ ጐደ​ሎም ይቈ​ጠር ዘን​ድ​አ​ይ​ች​ልም። እኔ በልቤ፥ “እነሆ፥ ከእኔ አስ​ቀ​ድ​መው በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ላይ ከነ​በ​ሩት ሁሉ ይልቅ ጥበ​ብን አበ​ዛሁ፤ ልቤ​ንም ለጥ​በ​ብና ለዕ​ው​ቀት ሰጠሁ፥” በማ​ለት ተና​ገ​ርሁ። ልቤም ብዙ ጥበ​ብ​ንና አእ​ም​ሮን፥ ምሳ​ሌ​ንና ማስ​ተ​ዋ​ልን ተመ​ለ​ከ​ተች። ይህም ነፋ​ስን መከ​ተል እንደ ሆነ አስ​ተ​ዋ​ልሁ። በጥ​በብ መብ​ዛት ትካዜ ይበ​ዛ​ልና፤ ዕው​ቀ​ት​ንም የሚ​ያ​በዛ መከ​ራን ያበ​ዛ​ልና።

መክብብ 1:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በኢየሩሳሌም የነገሠው፣ የዳዊት ልጅ፣ የሰባኪው ቃል፤ “የከንቱ ከንቱ፤” ይላል ሰባኪው፤ “ሁሉም ነገር ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ነው።” ከፀሓይ በታች ከሚለፋበት ተግባር ሁሉ፣ ሰው ምን ትርፍ ያገኛል? ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች። ፀሓይ ትወጣለች፤ ትጠልቃለችም፤ ወደምትወጣበትም ለመመለስ ትጣደፋለች። ነፋስ ወደ ደቡብ ይነፍሳል፤ ወደ ሰሜንም ይመለሳል፤ ዞሮ ዞሮ ይሄዳል፤ ዘወትርም ወደ ዑደቱ ይመለሳል። ወንዞች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈስሳሉ፤ ባሕሩ ግን ፈጽሞ አይሞላም፤ ወንዞች ወደ መጡበት ስፍራ፣ ወደዚያ እንደ ገና ይመለሳሉ። ሰው መናገር ከሚችለው በላይ፣ ነገሮች ሁሉ አድካሚ ናቸው፤ ዐይን ከማየት አይጠግብም፤ ጆሮም በመስማት አይሞላም። የነበረው ነገር እንደ ገና ይሆናል፤ የተደረገውም ተመልሶ ይደረጋል፤ ከፀሓይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም። ማንም፣ “እነሆ፤ ይህ አዲስ ነገር ነው!” ሊል የሚችለው አንዳች ነገር አለን? ቀድሞውኑ በዚሁ የነበረ ነው፤ ከእኛ በፊት የሆነ ነው። የቀድሞ ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፤ ወደ ፊት የሚመጡትም ቢሆኑ፣ ከእነርሱ በኋላ በሚተኩት አይታወሱም። እኔ ሰባኪው፣ በኢየሩሳሌም የእስራኤል ንጉሥ ነበርሁ። ከሰማይ በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ ለማጥናትና ለመመርመር ራሴን አተጋሁ፤ አምላክ በሰዎች ላይ የጫነው እንዴት ያለ ከባድ ሸክም ነው! ከፀሓይ በታች የተደረገውን ነገር ሁሉ አየሁ፤ ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። የተጣመመው ሊቃና አይችልም፤ የሌለም ነገር ሊቈጠር አይችልም። እኔም በልቤ፣ “እነሆ፤ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከገዙት ከማንኛቸውም ይልቅ ታላቅ ሆኛለሁ፤ ጥበብም በዝቶልኛል፤ በብዙ ጥበብና ዕውቀት ተመክሮም ዐልፌአለሁ” አልሁ። ከዚያም የጥበብንና የእብደትን፣ የሞኝነትንም ነገር ለመገንዘብ ራሴን አተጋሁ፤ ይህም ነፋስን እንደ መከተል መሆኑን ተረዳሁ። ጥበብ ሲበዛ፣ ትካዜ ይበዛልና፤ ዕውቀት ሲጨምርም ሐዘን ይበዛል።

መክብብ 1:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በኢየሩሳሌም የነገሠ የሰባኪው የዳዊት ልጅ ቃል። ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፥ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። ከፀሐይ በታች በሚደክምበት ድካም ሁሉ የሰው ትርፉ ምንድር ነው? ትውልድ ይሄዳል፥ ትውልድም ይመጣል፥ ምድር ግን ለዘላለም ነው። ፀሐይ ትወጣለች፥ ፀሐይም ትገባለች፥ ወደምትወጣበትም ስፍራ ትቸኵላለች። ነፋስ ወደ ደቡብ ይሄዳል፥ ወደ ሰሜንም ይዞራል፥ ዘወትር በዙረቱ ይዞራል፥ ነፋስም በዙረቱ ደግሞ ይመለሳል። ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፥ ባሕሩ ግን አይሞላም፥ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደ ገና ወደዚያ ይመለሳሉ። ነገር ሁሉ ያደክማል፥ ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፥ ዓይን ከማየት አይጠግብም፥ ጆሮም ከመስማት አይሞላም። የሆነው ነገር እርሱ የሚሆን ነው፥ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፥ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም። ማንም፦ እነሆ፥ ይህ ነገር አዲስ ነው ይል ዘንድ ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተደርጎአል። ለፊተኞቹም ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፥ ለኋለኖቹም ነገሮች ከእነርሱ በኋላ በሚነሡት ሰዎች ዘንድ መታሰቢያ አይገኝላቸውም። እኔ ሰባኪው በእስራኤል ላይ በኢየሩሳሌም ንጉሥ ነበርሁ። ከሰማይም በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ እፈልግና እመረምር ዘንድ ልቤን አተጋሁ፥ እግዚአብሔር ይደክሙባት ዘንድ ይህችን ለሰው ልጆች የሰጠ ክፉ ጥረት ናት። ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፥ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ጠማማ ይቀና ዘንድ አይችልም፥ ጐደሎም ይቈጠር ዘንድ አይችልም። እኔ በልቤ፦ እነሆ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ላይ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ጥበብን አብዝቼ ጨመርሁ፥ ልቤም ብዙ ጥበብንና እውቀትን ተመለከተ ብዬ ተናገርሁ። ጥበብንና ዕብደትን ሞኝነትንም አውቅ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፥ ይህም ደግሞ ነፋስን እንደ መከተል እንደ ሆነ አስተዋልሁ። በጥበብ መብዛት ትካዜ ይበዛልና፥ እውቀትንም የሚጨምር ኀዘንን ይጨምራልና።

መክብብ 1:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በኢየሩሳሌም ነግሦ የነበረ ጥበበኛው የዳዊት ልጅ የተናገረው የጥበብ ቃል ይህ ነው፤ ጥበበኛው እንዲህ አለ፦ ሁሉ ነገር ከንቱ፥ እንዲያውም የከንቱ ከንቱ ነው፤ ሁሉም ነገር በፍጹም ከንቱ ነው። ሰው በሚኖርበት ዓለም በሥራ የሚደክምበት ነገር ሁሉ ትርፉ ምንድን ነው? ትውልድ አልፎ ትውልድ ይተካል፤ ምድር ግን ሳትለወጥ ለዘለዓለሙ ጸንታ ትኖራለች። ፀሐይ ወጥታ ትጠልቃለች፤ እንደገናም ወደምትወጣበት ስፍራ ለመድረስ ትጣደፋለች። ነፋስ ወደ ደቡብም፥ ወደ ሰሜንም ይነፍሳል፤ ዞሮ ዞሮም እንደገና ይመለሳል። የወንዝ ውሃ ሁሉ ወደ ባሕር ይፈስሳል፤ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ውሃ ተመልሶ እንደገና ወደሚፈልቅበት ወደ ወንዞቹ መነሻ ይሄዳል። ሁሉ ነገር አሰልቺ ነው፤ አሰልቺነቱንም ሰው በቃል ገልጦ ሊናገረው እንኳ አይችልም፤ ዐይን አይቶ አይጠግብም፤ ጆሮም ሰምቶ በቃኝ አይልም። ቀድሞ የሆነው ነገር እንደገና ይሆናል፤ አሁንም የሚደረገው ነገር ሁሉ ያው ቀድሞ የተደረገው ነው፤ ስለዚህ በመላው ዓለም አዲስ ተብሎ የሚጠራ ምንም ነገር የለም። ማንም ሰው “እነሆ ይህ አዲስ ነገር ነው!” ቢል ያ ነገር እኛ ከመወለዳችን አስቀድሞ የነበረ ሆኖ ይገኛል። ባለፉት ዘመናት ተደርገው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ የሚያስታውስ የለም፤ ከእነርሱም በኋላ ተከታትለው የሚመጡትም ነገሮች ቢሆኑ በተተኪው ትውልድ ዘንድ መታሰቢያ አይኖራቸውም። እኔ ተናጋሪው በኢየሩሳሌም የእስራኤል ንጉሥ ነበርኩ፤ ታዲያ፥ በዚህ ዓለም የተደረጉትን ነገሮች ሁሉ በጥበብ መርምሬ ለማጥናት ወሰንኩ፤ ይህችን ከባድ ጭነት የሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ እግዚአብሔር ሰጥቶአቸዋል። እነሆ በዚህ ዓለም ላይ የተደረገውን ነገር ሁሉ ተመለከትኩ፤ ይሁን እንጂ ሁሉ ነገር ከንቱ ሆኖ አገኘሁት፤ ሁሉም ነገር ነፋስን እንደ መጨበጥ ሆኖ ይቈጠራል። ጠማማው ሊቀና አይችልም፤ የሌለ ነገር ሊቈጠር አይቻልም። እኔማ በልቤ “ከእኔ በፊት ኢየሩሳሌምን ከገዙት ሁሉ ይበልጥ ታላቅና የጥበብ ሰው ሆኛለሁ፤ የጥበብንና የዕውቀትን ምንነት መርምሬ አጥንቻለሁ” ብዬ ነበር፤ ስለዚህ ጥበብንና ዕውቀትን፥ እብደትንና ሞኝነትን ዐውቅ ዘንድ ኅሊናዬን አተጋለሁ፤ ይህም ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ሆኖ አገኘሁት። ጥበብ በበዛ መጠን ትካዜ ይበዛል፤ ዕውቀትም በበዛ መጠን ጭንቀትን ያስከትላል።

መክብብ 1:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በኢየሩሳሌም የነገሠ የሰባኪው የዳዊት ልጅ ቃል። ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፥ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። ከፀሐይ በታች በሚደክምበት ድካም ሁሉ የሰው ትርፉ ምንድነው? ትውልድ ይሄዳል፥ ትውልድም ይመጣል፥ ምድር ግን ለዘለዓለም ናት። ፀሐይ ትወጣለች፥ ፀሐይም ትገባለች፥ ወደምትወጣበትም ስፍራ ትቸኩላለች። ነፋስ ወደ ደቡብ ይሄዳል፥ ወደ ሰሜንም ይዞራል፥ ዘወትር በዙረቱ ይዞራል፥ ነፋስም በዙረቱ ደግሞ ይመለሳል። ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፥ ባሕሩ ግን አይሞላም፥ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደገና ወደዚያ ይመለሳሉ። ነገር ሁሉ ያደክማል፥ ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፥ ዐይን ከማየት አይጠግብም፥ ጆሮም ከመስማት አይሞላም። የሆነው ነገር ወደፊትም የሚሆነው ነው፥ የተደረገውም ነገር ወደ ፊት የሚደረገው ነው፥ ከፀሐይም በታች ምንም አዲስ ነገር የለም። ማንም፦ እነሆ፥ ይህ ነገር አዲስ ነው ማለት ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተደርጎአል። ለፊተኞቹም ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፥ ለኋለኞቹም ነገሮች ከእነርሱ በኋላ በሚነሡት ሰዎች ዘንድ መታሰቢያ አይገኝላቸውም። እኔ ሰባኪው በእስራኤል ላይ በኢየሩሳሌም ንጉሥ ነበርሁ። ከሰማይም በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ እፈልግና እመረምር ዘንድ ልቤን አተጋሁ፥ ይደክሙባት ዘንድ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጣት ከባድ ጥረት ናት። ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፥ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም መከተል ነው። ጠማማ ሊቀና አይችልም፥ የጐደለም ሊቈጠር ዘንድ አይችልም። እኔ በልቤ፦ እነሆ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ላይ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ጥበብን አብዝቼ ጨመርሁ፥ ልቤም ብዙ ጥበብንና እውቀትን ተመለከተ ብዬ ተናገርሁ። ጥበብንና ዕብደትን ሞኝነትንም አውቅ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፥ ይህም ደግሞ ነፋስን መከተል እንደሆነ አስተዋልሁ። በጥበብ መብዛት ትካዜ ይበዛልና፥ እውቀትንም የሚጨምር ኀዘንን ይጨምራልና።