መጽሐፈ መክብብ 1
1
ሁሉ ነገር ከንቱ ስለ መሆኑ
1በኢየሩሳሌም ነግሦ የነበረ ጥበበኛው የዳዊት ልጅ የተናገረው የጥበብ ቃል ይህ ነው፤ 2ጥበበኛው እንዲህ አለ፦ ሁሉ ነገር ከንቱ፥ እንዲያውም የከንቱ ከንቱ ነው፤ ሁሉም ነገር በፍጹም ከንቱ ነው። 3ሰው በሚኖርበት ዓለም በሥራ የሚደክምበት ነገር ሁሉ ትርፉ ምንድን ነው? 4ትውልድ አልፎ ትውልድ ይተካል፤ ምድር ግን ሳትለወጥ ለዘለዓለሙ ጸንታ ትኖራለች። 5ፀሐይ ወጥታ ትጠልቃለች፤ እንደገናም ወደምትወጣበት ስፍራ ለመድረስ ትጣደፋለች። 6ነፋስ ወደ ደቡብም፥ ወደ ሰሜንም ይነፍሳል፤ ዞሮ ዞሮም እንደገና ይመለሳል። 7የወንዝ ውሃ ሁሉ ወደ ባሕር ይፈስሳል፤ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ውሃ ተመልሶ እንደገና ወደሚፈልቅበት ወደ ወንዞቹ መነሻ ይሄዳል። 8ሁሉ ነገር አሰልቺ ነው፤ አሰልቺነቱንም ሰው በቃል ገልጦ ሊናገረው እንኳ አይችልም፤ ዐይን አይቶ አይጠግብም፤ ጆሮም ሰምቶ በቃኝ አይልም። 9ቀድሞ የሆነው ነገር እንደገና ይሆናል፤ አሁንም የሚደረገው ነገር ሁሉ ያው ቀድሞ የተደረገው ነው፤ ስለዚህ በመላው ዓለም አዲስ ተብሎ የሚጠራ ምንም ነገር የለም። 10ማንም ሰው “እነሆ ይህ አዲስ ነገር ነው!” ቢል ያ ነገር እኛ ከመወለዳችን አስቀድሞ የነበረ ሆኖ ይገኛል። 11ባለፉት ዘመናት ተደርገው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ የሚያስታውስ የለም፤ ከእነርሱም በኋላ ተከታትለው የሚመጡትም ነገሮች ቢሆኑ በተተኪው ትውልድ ዘንድ መታሰቢያ አይኖራቸውም።
ጥበበኛው ከኑሮ ልምድ የቀሰመው ዕውቀት
12እኔ ተናጋሪው በኢየሩሳሌም የእስራኤል ንጉሥ ነበርኩ፤ 13ታዲያ፥ በዚህ ዓለም የተደረጉትን ነገሮች ሁሉ በጥበብ መርምሬ ለማጥናት ወሰንኩ፤ ይህችን ከባድ ጭነት የሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ እግዚአብሔር ሰጥቶአቸዋል። 14እነሆ በዚህ ዓለም ላይ የተደረገውን ነገር ሁሉ ተመለከትኩ፤ ይሁን እንጂ ሁሉ ነገር ከንቱ ሆኖ አገኘሁት፤ ሁሉም ነገር ነፋስን እንደ መጨበጥ ሆኖ ይቈጠራል። 15ጠማማው ሊቀና አይችልም፤ የሌለ ነገር ሊቈጠር አይቻልም።
16እኔማ በልቤ “ከእኔ በፊት ኢየሩሳሌምን ከገዙት ሁሉ ይበልጥ ታላቅና የጥበብ ሰው ሆኛለሁ፤ የጥበብንና የዕውቀትን ምንነት መርምሬ አጥንቻለሁ” ብዬ ነበር፤ #1ነገ. 4፥29-31። 17ስለዚህ ጥበብንና ዕውቀትን፥ እብደትንና ሞኝነትን ዐውቅ ዘንድ ኅሊናዬን አተጋለሁ፤ ይህም ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ሆኖ አገኘሁት። 18ጥበብ በበዛ መጠን ትካዜ ይበዛል፤ ዕውቀትም በበዛ መጠን ጭንቀትን ያስከትላል።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997