ዘዳግም 2:1-7

ዘዳግም 2:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እን​ዳ​ለኝ ተመ​ል​ሰን በኤ​ር​ትራ ባሕር መን​ገድ ወደ ምድረ በዳ ሄድን፤ የሴ​ይ​ር​ንም ተራራ ብዙ ቀን ዞርን። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እን​ዲህ ብሎ ተና​ገ​ረኝ፦ ‘ይህን ተራራ መዞር ይበ​ቃ​ች​ኋል፤ ተመ​ል​ሳ​ችሁ ወደ መስዕ ሂዱ።’ ሕዝ​ቡ​ንም እን​ዲህ ብለህ እዘ​ዛ​ቸው፦ በሴ​ይር ላይ በተ​ቀ​መ​ጡት በወ​ን​ድ​ሞ​ቻ​ችሁ በዔ​ሳው ልጆች ሀገር ታል​ፋ​ላ​ችሁ፤ እነ​ርሱ ይፈ​ሩ​አ​ች​ኋል፤ እን​ግ​ዲህ እጅግ ተጠ​ን​ቀቁ። የሴ​ይ​ርን ተራራ ለዔ​ሳው ልጆች ርስት አድ​ርጌ ስለ ሰጠሁ እኔ ከም​ድ​ራ​ቸው የጫማ መር​ገጫ ታህል እን​ኳን አል​ሰ​ጣ​ች​ሁ​ምና አት​ጣ​ሉ​አ​ቸው። ከእ​ነ​ርሱ በገ​ን​ዘብ ምግብ ገዝ​ታ​ችሁ ትበ​ላ​ላ​ችሁ፤ ውኃም ደግሞ በገ​ን​ዘብ በመ​ለ​ኪያ ገዝ​ታ​ችሁ ትጠ​ጣ​ላ​ችሁ። አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የእ​ጅ​ህን ሥራ ሁሉ ባር​ኮ​ል​ሃ​ልና፤ ይህን ታላ​ቅና የሚ​ያ​ስ​ፈራ ምድረ በዳ እን​ዴት እንደ ዞር​ኸው ዕወቅ፤ በዚህ አርባ ዓመት ውስጥ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከአ​ንተ ጋር ነበረ፤ ከተ​ና​ገ​ር​ኸው ሁሉ አን​ዳ​ችም አላ​ሳ​ጣ​ህም።

ዘዳግም 2:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት ተመለስን፤ ቀይ ባሕርን ይዘን ወደ ምድረ በዳው ተጓዝን፤ በሴይር ኰረብታማ አገር ዙሪያ ለረዥም ጊዜ ተንከራተትን። ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “በዚህ በኰረብታማ አገር ዙሪያ እስኪበቃችሁ ተንከራታችኋል፤ አሁን ግን ወደ ሰሜን ተመለሱ። ለሕዝቡም እነዚህን ትእዛዞች ስጣቸው፤ ‘ሴይር በሚኖሩት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ዘሮች ግዛት ዐልፋችሁ ትሄዳላችሁ፤ እነርሱ ይፈሯችኋል፤ ቢሆንም ከፍ ያለ ጥንቃቄ አድርጉ። ከየትኛውም ምድራቸው ላይ ለጫማችሁ መርገጫ ታኽል እንኳ መሬት ስለማልሰጣችሁ፣ ለጦርነት አታነሣሧቸው። ኰረብታማውን የሴይርን አገር ርስት አድርጌ ለዔሳው ሰጥቼዋለሁ። ከዚያ ለምትበሉት ምግብም ሆነ ለምትጠጡት ውሃ በጥሬ ብር ትከፍሏቸዋላችሁ።’ ” አምላካችሁ እግዚአብሔር በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኳችኋል፤ በዚህ ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ጕዞ ጠብቋችኋል። በእነዚህ አርባ ዓመታት አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም።

ዘዳግም 2:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“እግዚአብሔር በነገረኝ መሠረት ወደ ምድረ በዳ ተመልሰን ወደ ቀይ ባሕር በሚወስደው አቅጣጫ በመጓዝ የኤዶምን ኮረብታማ ቦታ ለብዙ ቀን ዞርን። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ነገረኝ፦ ‘በእነዚህ ኮረብታማ አገሮች የተንከራተታችሁበት ጊዜው ረጅም ነው፤ አሁን ግን ወደ ሰሜን አቅጣጫ ሂዱ፤ ሕዝቡንም እንዲህ ብለህ እዘዝ፤ ዘመዶቻችሁ የዔሳው ዘሮች በሚኖሩበት በኮረብታማው በኤዶም አገር በኩል ታልፋላችሁ፤ እነርሱ እናንተን ይፈሩአችኋል፤ ነገር ግን ተጠንቀቁ፤ የኤዶምን ኮረብታማ አገር ለዔሳው ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ ከምድራቸው የጫማ መርገጫ ታኽል እንኳ አልሰጣችሁምና በእነርሱ ላይ ጦርነት አታንሡ። የሚያስፈልጋችሁን ምግብና ውሃ በገንዘብ ግዙ።’ “በእርግጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሠራችሁት ሥራ ሁሉ ብዙ በረከት ሰጥቶአችኋል፤ በዚህ በሰፊው በረሓ በሄዳችሁበት ሁሉ ተንከባክቦአችኋል፤ በእነዚህ በአርባ ዓመቶች እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ስለ ነበረ ምንም የጐደለባችሁ ነገር አልነበረም።