አሞጽ 9:1-15
አሞጽ 9:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “መድረኮቹ እንዲናወጡ፣ ጕልላቶቹን ምታ፤ በሕዝቡም ሁሉ ራስ ላይ ሰባብራቸው፤ የቀሩትን በሰይፍ እገድላቸዋለሁ፤ ከእነርሱ አንድም ሰው አይሸሽም፤ ቢሸሽም የሚያመልጥ የለም። መቃብር በጥልቀት ቈፍረው ቢወርዱም፣ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይ ቢወጡም፣ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ። በቀርሜሎስ ጫፍ ላይ ቢሸሸጉም፣ ዐድኜ፣ ፈልጌ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤ እይዛቸዋለሁም። በጥልቅ ባሕር ውስጥ ከእኔ ቢሸሸጉም፣ በዚያ እባቡ እንዲነድፋቸው አዝዘዋለሁ። በጠላቶቻቸው ተነድተው ለምርኮ ቢወሰዱም፣ በዚያ እንዲገድላቸው ሰይፍን አዝዛለሁ። “ለመልካም ሳይሆን ለክፉ፣ ዐይኔን በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ።” ጌታ እግዚአብሔር፣ የሰራዊት ጌታ፣ ምድርን ይዳስሳል፤ እርሷም ትቀልጣለች፤ በውስጧ የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የምድር ሁለመና እንደ አባይ ወንዝ ይነሣል፤ እንደ ግብጽ ወንዝም ይወርዳል። መኖሪያውን በሰማይ የሚሠራ፣ መሠረቱንም በምድር የሚያደርግ፣ የባሕርን ውሃ የሚጠራ፣ በምድርም ገጽ ላይ የሚያፈስስ፣ እርሱ ስሙ እግዚአብሔር ነው። “እናንተ እስራኤላውያን፣ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁምን?” ይላል እግዚአብሔር “እስራኤልን ከግብጽ፣ ፍልስጥኤማውያንን ከቀፍቶር፣ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን? “እነሆ፤ የጌታ እግዚአብሔር ዐይኖች፣ በኀጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፤ ከምድር ገጽ፣ ፈጽሜ አጠፋዋለሁ፤ የያዕቆብን ቤት ግን፣ ሙሉ በሙሉ አልደመስስም፤” ይላል እግዚአብሔር። “እነሆ፤ ትእዛዝ እሰጣለሁ፤ እህል በወንፊት እንደሚነፋ፣ የእስራኤልን ቤት፣ በሕዝብ ሁሉ መካከል እንዲሁ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም። በሕዝቤ መካከል ያሉ፣ ‘ክፉ ነገር አያገኘንም ወይም አይደርስብንም’ የሚሉ፣ ኀጢአተኞች ሁሉ፣ በሰይፍ ይሞታሉ። “በዚያ ቀን፣ “የወደቀውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፤ የተሰበረውን እጠግናለሁ፤ ፍርስራሹን ዐድሳለሁ፤ ቀድሞ እንደ ነበረም አድርጌ እሠራዋለሁ፤ ስለዚህ የኤዶምን ትሩፍ፣ በስሜ የተጠሩትንም ሕዝቦች ሁሉ ይወርሳሉ፤” ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ዐጫጁ ዐጭዶ ሳይጨርስ፣ ዐራሹ በላዩ የሚደርስበት፣ ችግኝ ተካዩም ገና ተክሎ ሳይጨርስ፣ ወይን ጨማቂው የሚደርስበት ጊዜ ይመጣል፤ አዲስ የወይን ጠጅ ከተራሮች ይንጠባጠባል፤ ከኰረብቶችም ሁሉ ይፈስሳል። የተሰደደውን ሕዝቤን እስራኤልን እመልሳለሁ። “እነርሱም የፈራረሱትን ከተሞች መልሰው ሠርተው በውስጣቸው ይኖራሉ። የወይን ተክል ተክለው፣ ጠጁን ይጠጣሉ፤ አትክልት ተክለው ፍሬውን ይበላሉ። እስራኤልን በገዛ ምድራቸው እተክላቸዋለሁ፤ ከሰጠኋቸውም ምድር፣ ዳግመኛ አይነቀሉም፤” ይላል አምላክህ እግዚአብሔር።
አሞጽ 9:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርን በመሠውያው ላይ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “አበቦች የተሳሉባቸውን ምሰሶዎችን ምታ፤ መድረኮቹም ይናወጣሉ፤ ራሳቸውንም ቍረጥ፤ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፤ ከሚሸሹትም የሚያመልጥ የለም፤ ከሚያመልጡትም የሚድን የለም። ወደ ሲኦል ቢወርዱ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይም ቢወጡ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤ በቀርሜሎስ ራስ ውስጥ ቢሸሸጉ ፈልጌ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ በባሕሩም ጥልቅ ውስጥ ከዐይኔ ቢደበቁ በዚያ እባቡን አዝዛለሁ፤ እርሱም ይነድፋቸዋል፤ በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ በዚያ ሰይፍን አዝዛታለሁ፤ እርስዋም ትገድላቸዋለች፤ ዐይኔንም ለመልካም ሳይሆን ለክፋት በእነርሱ ላይ እጥላለሁ።” ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር ምድርን ሁሉ ይዳስሳል፤ ያነዋውጣታልም፤ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ግድያ እንደ ወንዝ ይፈስሳል፤ ደግሞም እንደ ግብፅ ወንዝ ይወርዳል። አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ትእዛዙንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት የሚያፈስሰው እርሱ ነው፤ ስሙም ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ነው። “የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር። እስራኤልን ከግብፅ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከቀጰዶቅያ፥ ሶርያውያንንም ከጕድጓድ ያወጣሁ አይደለምን? እነሆ የጌታ የእግዚአብሔር ዐይኖች በኀጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፤ ከምድርም ፊት አጠፋታለሁ፤ ነገር ግን የያዕቆብን ቤት ፈጽሜ አላጠፋም፤ ይላል እግዚአብሔር። እነሆ አዝዛለሁ፤ እህልም በመንሽ እንደሚዘራ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እዘራለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም። ክፉው ነገር አይደርስብንም፤ አያገኘንምም የሚሉ የሕዝቤ ኀጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ። “በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ቤት አነሣለሁ፤ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፤ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤ ይኸውም የቀሩ ሰዎችንና ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ ይፈልጉ ዘንድ ነው” ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር። “እነሆ፥ እንዲህ ያለ ወራት ይመጣልን? ይላል እግዚአብሔር፤ እርሻ ከአጨዳ ጋር፥ ዘርም ከእሸት ጋር አንድ ይሆናል፤ ከተራሮችም ማር ይፈስሳል፤ ኮረብታውም ይለመልማል። የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፤ የፈረሱትንም ከተሞች ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ የወይን ጠጃቸውንም ይጠጣሉ፤ ተክልን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። በምድራቸውም እተክላቸዋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም” ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር አምላክ።
አሞጽ 9:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፥ እርሱም እንዲህ አለ፦ መድረኮቹ ይናወጡ ዘንድ ጕልላቶቹን ምታ፥ በራሳቸውም ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፥ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፥ የሚሸሽ አያመልጥም፥ የሚያመልጥም አይድንም። ወደ ሲኦል ቢወርዱ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፥ ወደ ሰማይም ቢወጡ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፥ በቀርሜሎስም ራስ ውስጥ ቢሸሸጉ ፈልጌ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፥ በጥልቅ ባሕርም ውስጥ ከዓይኔ ቢደበቁ ከዚያ እባቡን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይነድፋቸዋል፥ በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ ከዚያ ሰይፍን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይገድላቸዋል፥ ዓይኔንም በእነርሱ ላይ ለክፋት እንጂ ለመልካም አላደርግም። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድርን ይዳስሳል እርስዋም ትቀልጣለች፥ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፥ ሙላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ ትነሣለች፥ ደግሞም እንደ ግብጽ ወንዝ ትወርዳለች። አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው። የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር። እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን? እነሆ፥ የጌታ የእግዚአብሔር ዓይኖች በኃጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፥ ከምድርም ፊት አጠፋታለሁ፥ ነገር ግን የያዕቆብን ቤት ፈጽሜ አላጠፋም፥ ይላል እግዚአብሔር። እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ እህልም በወንፊት እንዲነፋ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እነፋለሁ፥ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም። ክፉው ነገር አይደርስብንም፥ አያገኘንምም የሚሉ የሕዝቤ ኃጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ። በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፥ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፥ ይኸውም የኤዶምያስን ቅሬታ፥ ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ ይወርሱ ዘንድ ነው፥ ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር። እነሆ፥ አራሹ አጫጁን፥ ወይን ጠማቂውም ዘሪውን የሚያገኝበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ተራሮችም በተሀውን የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ይቀልጣሉ። የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፥ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ፥ አታክልትንም ያባጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ። በምድራቸውም እተክላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም፥ ይላል አምላክህ እግዚአብሔር።
አሞጽ 9:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ ሲል አዘዘ፦ “መድረኮቹ እስኪናወጡ ድረስ የቤተ መቅደሱን ጒልላት ምታ፤ ሰባብረህም በሰዎቹ አናት ላይ እንዲደረመስ አድርግ፤ ከዚያ የተረፉትንም እኔ በሰይፍ እጨርሳቸዋለሁ፤ ማንም መሸሽ አይችልም፤ ማንም ሊያመልጥ አይችልም። ምድርን ቆፍረው ወደ ሙታን ዓለም ቢወርዱ እንኳ እኔ ከዚያ መንጥቄ አወጣቸዋለሁ፤ ወደ ሰማይም መጥቀው ቢወጡ እንኳ እኔ መልሼ አወርዳቸዋለሁ፤ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ወጥተው ቢሸሸጉም ተከታትዬ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ ወደ ጥልቅ ባሕር ገብተው ከእኔ ለመሰወር ቢሞክሩም እንዲነድፋቸው የባሕሩን ዘንዶ አዛለሁ። በጠላቶቻቸው እጅ ተማርከው ቢወሰዱም እዚያ እንዲገደሉ አደርጋለሁ፤ በዚህ ዐይነት እኔ በእነርሱ ላይ የማደርገው ትኲረት ይጐዳቸዋል እንጂ አይጠቅማቸውም።” መላዋ ምድር እንደ ግብጹ የዐባይ ወንዝ ከፍና ዝቅ በማለት ትናወጣለች፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድሪቱን ሲነካ ትቀልጣለች፤ በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ። መኖሪያውን በሰማያት ያደረገ፥ ጠፈርን ከምድር በላይ ያጸና፥ የባሕሩን ውሃ አዞ በምድር ላይ እንዲፈስ የሚያደርግ፥ ስሙ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በእኔ ዘንድ ኢትዮጵያውያን ከእናንተ አያንሱም፤ እናንተን ከግብጽ እንዳወጣሁ እንደዚሁም ፍልስጥኤማውያንን ከቀርጤስ፥ ሶርያውያንን ከቂር አላወጣሁምን? አውጥቻለሁ። እኔ ጌታ እግዚአብሔር ወደ ኃጢአተኛው የእስራኤል መንግሥት እመለከታለሁ፤ እርስዋንም ከምድር ገጽ አጠፋለሁ፤ ሆኖም የያዕቆብን ዘር ሙሉ በሙሉ አልደመስስም። ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። “የእስራኤል ሕዝብ በሕዝቦች መካከል እንዲበተኑ አዛለሁ፤ የሚበተኑትም እህል በወንፊት እንደሚነፋ ዐይነት ነው፤ ነገር ግን ወንፊቱ ሲነቃነቅ ገለባው እንጂ አንድም ቅንጣት አይበተንም። ‘ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም ወይም አያገኘንም’ የሚሉ በሕዝቤ መካከል የሚገኙ ኃጢአተኞች ሁሉ በጦርነት ይሞታሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ፈራርሶ እንደ ወደቀ ቤት የነበረውን የዳዊትን ሥርወ መንግሥት መልሼ የማቋቊምበት ጊዜ ይመጣል፤ ቅጽሩን እጠግናለሁ፤ ፍርስራሹንም አድሳለሁ፤ በቀድሞ ዘመን እንደ ነበረውም አድርጌ እሠራዋለሁ፤ በዚህም ዐይነት ከኤዶም ምድር የተረፉትንና ሌሎችንም በስሜ የተጠሩትን ሕዝብ ሁሉ ይወርሳሉ፤” ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእህል ሰብል አጫጆች አጭደው ሳይጨርሱ፥ አራሾች የሚደርሱባቸውና ወይን ጨማቂዎችም የወይን ፍሬ ጨምቀው ሳይጨርሱ፥ የወይን ተካዮች የሚደርሱባቸው ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ተራራዎች ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያፈልቃሉ፤ ኰረብቶችም በወይን ጠጅ ይጥለቀለቃሉ። ሕዝቤን እስራኤልን ወደ አገራቸው መልሼ አመጣለሁ፤ የፈረሱትን ከተሞች እንደገና ሠርተው በዚያ ይኖራሉ፤ ወይን ተክለው የወይን ጠጅ ይጠጣሉ፤ ልዩ ልዩ ተክሎችን ተክለው ፍሬውን ይመገባሉ። ሕዝቤን እስራኤልን በሰጠኋቸው ምድር ላይ እተክላቸዋለሁ፤ ዳግመኛም ከዚያ ተነቅለው አይወጡም፤” ይህን የሚናገር እግዚአብሔር አምላካችሁ ነው።
አሞጽ 9:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ፦ መድረኮቹ እስኪናወጡ ድረስ ጉልላቶቹን ምታ፥ በሰዎቹም ራስ ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፤ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፤ የሚሸሽ አያመልጥም፥ የሚያመልጥም አይድንም። “ወደ ሲኦል ቢወርዱ እንኳ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይም ቢወጡ እንኳ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤ በቀርሜሎስም ራስ ላይ ቢሸሸጉ እንኳ አድኜ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ በጥልቅ ባሕርም ውስጥ ከዓይኔ ቢደበቁ እንኳ ከዚያ እባቡን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይነድፋቸዋል፤ በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ እንኳ ከዚያ ሰይፍን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይገድላቸዋል፤ ዓይኔንም በእነርሱ ላይ ለክፋት እንጂ ለመልካም አላደርግም።” ጌታ የሠራዊት አምላክ ምድርን ይዳስሳል እርሷም ትቀልጣለች፥ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ሞላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ ትነሣለች፥ ዳግመኛም እንደ ግብጽ ወንዝ ትወርዳለች። አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው፤ ስሙም ጌታ ነው። “የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?” ይላል ጌታ። “እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን? እነሆ፥ የጌታ የእግዚአብሔር ዐይኖች በኃጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፥ ከምድርም ፊት አጠፋዋለሁ፤ ነገር ግን የያዕቆብን ቤት ፈጽሜ አላጠፋም፥” ይላል ጌታ። “እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ እህልም በወንፊት እንደሚነፋ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እንዲሁ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም። ‘ክፉው ነገር አይደርስብንም፥ አያገኘንምም’ የሚሉ የሕዝቤ ኃጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ። “በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤ ይኸውም የኤዶምያስን ትሩፍ፥ ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ እንዲወርሱ ነው፥” ይላል ይህን የሚያደርግ ጌታ። “እነሆ፥ አራሹ አጫጁን፥ ወይን ጠማቂውም ዘሪውን የሚቀድምበት ወራት ይመጣል፥” ይላል ጌታ፤ “ተራሮችም ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ይቀልጣሉ። የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ዳግም ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ፤ የአትክልት ስፍራዎችንም ያበጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ። በምድራቸውም ላይ እተክላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም፥” ይላል ጌታ አምላክህ።