የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ አሞጽ 9

9
1ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፥ እርሱም እንዲህ አለ፦ መድረኮቹ ይናወጡ ዘንድ ጕልላቶቹን ምታ፥ በራሳቸውም ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፥ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፥ የሚሸሽ አያመልጥም፥ የሚያመልጥም አይድንም። 2ወደ ሲኦል ቢወርዱ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፥ ወደ ሰማይም ቢወጡ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፥ 3በቀርሜሎስም ራስ ውስጥ ቢሸሸጉ ፈልጌ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፥ በጥልቅ ባሕርም ውስጥ ከዓይኔ ቢደበቁ ከዚያ እባቡን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይነድፋቸዋል፥ 4በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ ከዚያ ሰይፍን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይገድላቸዋል፥ ዓይኔንም በእነርሱ ላይ ለክፋት እንጂ ለመልካም አላደርግም።
5የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድርን ይዳስሳል እርስዋም ትቀልጣለች፥ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፥ ሙላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ ትነሣለች፥ ደግሞም እንደ ግብጽ ወንዝ ትወርዳለች። 6አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው።
7የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር። እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን? 8እነሆ፥ የጌታ የእግዚአብሔር ዓይኖች በኃጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፥ ከምድርም ፊት አጠፋታለሁ፥ ነገር ግን የያዕቆብን ቤት ፈጽሜ አላጠፋም፥ ይላል እግዚአብሔር። 9እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ እህልም በወንፊት እንዲነፋ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እነፋለሁ፥ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም። 10ክፉው ነገር አይደርስብንም፥ አያገኘንምም የሚሉ የሕዝቤ ኃጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ።
11በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፥ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፥ 12ይኸውም የኤዶምያስን ቅሬታ፥ ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ ይወርሱ ዘንድ ነው፥ ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር።
13እነሆ፥ አራሹ አጫጁን፥ ወይን ጠማቂውም ዘሪውን የሚያገኝበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ተራሮችም በተሀውን የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ይቀልጣሉ። 14የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፥ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ፥ አታክልትንም ያባጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ። 15በምድራቸውም እተክላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም፥ ይላል አምላክህ እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ