ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ፦ መድረኮቹ እስኪናወጡ ድረስ ጉልላቶቹን ምታ፥ በሰዎቹም ራስ ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፤ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፤ የሚሸሽ አያመልጥም፥ የሚያመልጥም አይድንም። “ወደ ሲኦል ቢወርዱ እንኳ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይም ቢወጡ እንኳ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤ በቀርሜሎስም ራስ ላይ ቢሸሸጉ እንኳ አድኜ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ በጥልቅ ባሕርም ውስጥ ከዓይኔ ቢደበቁ እንኳ ከዚያ እባቡን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይነድፋቸዋል፤ በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ እንኳ ከዚያ ሰይፍን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይገድላቸዋል፤ ዓይኔንም በእነርሱ ላይ ለክፋት እንጂ ለመልካም አላደርግም።” ጌታ የሠራዊት አምላክ ምድርን ይዳስሳል እርሷም ትቀልጣለች፥ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ሞላዋም እንደ ግብጽ ወንዝ ትነሣለች፥ ዳግመኛም እንደ ግብጽ ወንዝ ትወርዳለች። አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው፤ ስሙም ጌታ ነው። “የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?” ይላል ጌታ። “እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን? እነሆ፥ የጌታ የእግዚአብሔር ዐይኖች በኃጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፥ ከምድርም ፊት አጠፋዋለሁ፤ ነገር ግን የያዕቆብን ቤት ፈጽሜ አላጠፋም፥” ይላል ጌታ። “እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ እህልም በወንፊት እንደሚነፋ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እንዲሁ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም። ‘ክፉው ነገር አይደርስብንም፥ አያገኘንምም’ የሚሉ የሕዝቤ ኃጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ። “በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤ ይኸውም የኤዶምያስን ትሩፍ፥ ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ እንዲወርሱ ነው፥” ይላል ይህን የሚያደርግ ጌታ። “እነሆ፥ አራሹ አጫጁን፥ ወይን ጠማቂውም ዘሪውን የሚቀድምበት ወራት ይመጣል፥” ይላል ጌታ፤ “ተራሮችም ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፥ ኮረብቶችም ሁሉ ይቀልጣሉ። የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ዳግም ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ፤ የአትክልት ስፍራዎችንም ያበጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ። በምድራቸውም ላይ እተክላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም፥” ይላል ጌታ አምላክህ።
ትንቢተ አሞጽ 9 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ አሞጽ 9:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos