ሐዋርያት ሥራ 21:27-40
ሐዋርያት ሥራ 21:27-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሰባተኛውም ቀን ከእስያ የመጡ አይሁድ ጳውሎስን በመቅደስ አዩት፤ ሕዝቡንም ሁሉ በእርሱ ላይ አነሳሥተው ያዙት። እየጮሁም እንዲህ አሉ፥ “እናንተ የእስራኤል ወገኖች ሆይ፥ ርዱን፤ በየስፍራው ሕዝባችንን፥ ኦሪትንም፥ ይህንም ስፍራ የሚቃወም ትምህርት ለሰው ሁሉ የሚያስተምር እነሆ፥ ይህ ሰው ነው፤ አሁንም አረማውያንን ወደ መቅደስ አስገባ፤ ቤተ መቅደስንም አረከሰ። የኤፌሶን ሀገር ሰው የሆነ ጥሮፊሞስን ከጳውሎስ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና፤ ጳውሎስም ወደ ቤተ መቅደስ ያስገባው መስሎአቸው ነበርና። ከተማውም ሁሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ ሄደው ጳውሎስን ጐትተው ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ በሩንም ሁሉ ዘጉ። ሊገድሉትም ፈልገው ብዙ ደበደቡት፤ ወዲያውም ኢየሩሳሌም በመላዋ እንደ ታወከች የሚገልጥ መልእክት ወደ ሻለቃው ደረሰለት። በዚያ ጊዜም ጭፍሮቹን ከአለቆቻቸው ጋር ይዞ ወደ እነርሱ ሄደ፤ እነርሱም የሻለቃውን ጭፍሮች ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታታቸውን ተዉ። የሻለቃውም ቀረብ ብሎ ያዘው፤ በሁለት ሰንሰለትም እንዲታሰር አዘዘ፤ “ምንድነው? ምንስ አደረገ?” ብሎም ጠየቀ። ሕዝቡም እኩሌቶቹ እንዲህ ነው፤ እኩሌቶቹም እንዲህ አይደለም እያሉ ይጮሁ ነበር፤ ሻለቃውም ሕዝቡ የሚታወክበትን ርግጡን ማወቅ ተሣነው፤ ወደ ወታደሮቹም ሰፈር እንዲወስዱት አዘዘ። ደረጃውንም በሚወጣበት ጊዜ ወታደሮች ተሸክመው አወጡት፤ ሰው ይጋፋ ነበርና። ብዙዎችም ይከተሉት ነበር፤ ሕዝቡም፥ “አስወግዱት” እያሉ ይጮሁ ነበር። ወደ ሰፈርም በደረሰ ጊዜ ጳውሎስ ሻለቃውን፥ “ላነጋግርህ ትፈቅድልኛለህን?” አለው፤ ሻለቃውም፥ “የጽርዕ ቋንቋ ታውቃለህን?” አለው። “ምናልባት ከዚህ በፊት ወንጀል የሠራህና ከነፍሰ ገዳዮች አራት ሺህ ሰዎችን ይዘህ ወደ ምድረ በዳ የወጣህ ያ ግብፃዊ አንተ አይደለህምን?” አለው። ጳውሎስም፥ “እኔስ አይሁዳዊ ሰው ነኝ፤ የተወለድሁባትም ሀገር ጠርሴስ የታወቀች የቂልቅያ ከተማ ናት፤ ለሕዝቡም እንድነግራቸው ትፈቅድልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ” አለው። በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ እጁን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ፤ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ ጳውሎስ በዕብራይስጥ ቋንቋ ተናገረ፤ እንዲህም አለ።
ሐዋርያት ሥራ 21:27-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሰባቱ ቀንም ሊፈጸም ሲቃረብ፣ ከእስያ አውራጃ የመጡት አይሁድ ጳውሎስን በቤተ መቅደስ ባዩት ጊዜ፣ ሕዝቡን ሁሉ አነሣሥተው ያዙት፤ እንዲህም እያሉ ጮኹ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ርዱን! ሕዝባችንንና ሕጋችንን እንዲሁም ይህን ስፍራ በማጥላላት በደረሰበት ስፍራ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ከዚህም በላይ ግሪኮችን ወደ ቤተ መቅደስ እያስገባ ይህን የተቀደሰ ስፍራ የሚያረክሰው እርሱ ነው።” ይህንም ያሉት ቀደም ሲል፣ የኤፌሶኑን ሰው ጥሮፊሞስን ከጳውሎስ ጋራ በከተማው ውስጥ ስላዩት፣ ጳውሎስ እርሱንም ወደ ቤተ መቅደስ ይዞ የገባ ስለ መሰላቸው ነበር። ከተማው በሙሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ከየአቅጣጫው እየተሯሯጡ መጡ፤ ጳውሎስንም ይዘው እየጐተቱት ከቤተ መቅደሱ ግቢ አወጡት፤ በሮቹም ወዲያውኑ ተዘጉ። ሊገድሉት ሲፈልጉም የኢየሩሳሌም ከተማ ፍጹም ታወከች፤ ወሬውም ለሮማ ጦር አዛዥ ደረሰው። እርሱም ወዲያው አንዳንድ የጦር መኰንኖችንና ወታደሮችን ይዞ እየሮጠ ወደ እነርሱ ወረደ፤ እነርሱም መኰንኖቹንና ወታደሮቹን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መደብደብ ተዉ። የጦር አዛዡም ቀርቦ ያዘው፤ በሁለት ሰንሰለትም እንዲታሰር ትእዛዝ ሰጠ፤ ከዚያም ማን መሆኑንና ምን እንዳደረገ ጠየቀ። ሕዝቡም ከፊሉ አንድ ነገር ሲናገር፣ ከፊሉ ደግሞ ሌላ ይናገር ነበር፤ ከጫጫታው የተነሣም አዛዡ ምንም ነገር ሊሰማ አልቻለም፤ ስለዚህ ጳውሎስ ወደ ጦር ሰፈር እንዲወሰድ አዘዘ። ከሕዝቡ ሁካታ የተነሣ፣ ጳውሎስ ወደ መውጫው ደረጃ ሲደርስ ወታደሮቹ ይሸከሙት ዘንድ ግድ ሆነባቸው። ከኋላ የተከተለውም ሕዝብ፣ “አስወግደው!” እያለ ይጮኽ ነበር። ወታደሮቹ ወደ ጦር ሰፈር ይዘውት ሊሄዱ ሲሉ፣ ጳውሎስ ጦር አዛዡን፣ “አንድ ነገር እንድነግርህ ፍቀድልኝ?” አለው። አዛዡም እንዲህ አለው፤ “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህ? አንተ ከዚህ ቀደም ዐመፅ አስነሥተህ፣ አራት ሺሕ ነፍሰ ገዳዮችን ወደ በረሓ ያሸፈትኸው ግብጻዊ አይደለህምን?” ጳውሎስም፣ “እኔስ በኪልቅያ ያለችው የታዋቂዋ የጠርሴስ ከተማ ነዋሪ የሆንሁ አይሁዳዊ ነኝ፤ ለሕዝቡ ንግግር እንዳደርግ ፍቀድልኝ” አለው። ጳውሎስም የጦር አዛዡን ካስፈቀደ በኋላ፣ በደረጃው ላይ ቆሞ ሕዝቡን በእጁ ጠቀሰ፤ ሁሉም ጸጥ ባሉ ጊዜ፣ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ አለ፤
ሐዋርያት ሥራ 21:27-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሰባቱ ቀንም ይፈጸም ዘንድ ሲቀርብ ከእስያ የመጡ አይሁድ በመቅደስ አይተውት ሕዝብን ሁሉ አወኩና፦ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ እርዱን ሕዝብን ሕግንም ይህንም ስፍራ ሲቃወም ሰውን ሁሉ በየስፍራው የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ጨምሮም የግሪክን ሰዎች ደግሞ ወደ መቅደስ አግብቶ ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል ብለው እየጮኹ እጃቸውን ጫኑበት። በፊት የኤፌሶኑን ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና ጳውሎስም ወደ መቅደስ ያገባው መስሎአቸው ነው። ከተማውም ሁሉ ታወከ ሕዝቡም ሁሉ ተሰበሰቡ ጳውሎስንም ይዘው ከመቅደስ ውጭ ጎተቱት፥ ወዲያውም ደጆች ተዘጉ። ሊገድሉትም ሲፈልጉ፦ ኢየሩሳሌም ፈጽማ ታወከች የሚል ወሬ ወደ ጭፍራው ሻለቃ ወጣ፤ እርሱም ያን ጊዜ ወታደሮችን ከመቶ አለቆች ጋር ይዞ እየሮጠ ወረደባቸው፤ እነርሱም የሻለቃውንና ወታደሮችን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታት ተዉ። በዚያን ጊዜም የሻለቃው ቀርቦ ያዘውና በሁለት ሰንሰለት ይታሰር ዘንድ አዞ ማን እንደ ሆነና ምን እንዳደረገ ጠየቀ። ሕዝቡም እኵሌቶቹ እንዲህ እኵሌቶቹም እንዲያ እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ስለ ጫጫታውም እርግጡን ማወቅ ባልተቻለ ጊዜ፥ ወደ ወታደሮች ሰፈር ይወስዱት ዘንድ አዘዘ። ወደ ደረጃውም በደረሰ ጊዜ ስለ ሕዝቡ ግፊያ ወታደሮች እንዲሸከሙት ሆነ፤ ብዙ ሕዝብ፦ አስወግደው እያሉና እየጮኹ ይከተሉ ነበርና። ወደ ሰፈርም ሊያገቡት በቀረቡ ጊዜ፥ ጳውሎስ የሻለቃውን፦ አንድ ነገር ብነግርህ ትፈቅዳለህን? አለው። እርሱም፦ የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን? አንተ ከዚህ ዘመን አስቀድሞ ከነፍሰ ገዳዮቹ አራቱን ሺህ ሰዎች አሸፍተህ ወደ ምድረ በዳ ያወጣህ የግብፅ ሰው አይደለህምን? አለ። ጳውሎስ ግን፦ እኔስ አይሁዳዊ በኪልቅያ ያለው የጠርሴስ ሰው ሆኜ ስመ ጥር በሆነ ከተማ የምኖር ነኝ፤ ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ አለ። በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ በእጁ ወደ ሕዝቡ ጠቀሰ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እየተናገረ እንዲህ አለ።
ሐዋርያት ሥራ 21:27-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሰባቱ ቀን ሊፈጸም ሲቃረብ ከእስያ የመጡ አይሁድ ጳውሎስን በቤተ መቅደስ በማየታቸው ሕዝቡን ሁሉ አሳድመው ያዙት፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! እርዱን! ሕዝባችንንና ሕጋችንን፥ ይህንንም ስፍራ እየተሳደበ በየአገሩ ያለውን ሕዝብ ሁሉ የሚያስተምር ይህ ሰው ነው፤ ይህም አልበቃ ብሎት አሕዛብን ወደ ቤተ መቅደስ በማስገባት ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል!” እያሉ ጮኹ። ይህንንም ያሉበት ምክንያት ከዚህ ቀደም የኤፌሶኑን ተወላጅ ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ስለ ነበር እርሱን ጳውሎስ ወደ ቤተ መቅደስ ይዞት የገባ መስሎአቸው ነበር። ከተማዋ በሙሉ ታወከች፤ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ በአንድነት መጡና ጳውሎስን ይዘው እየጐተቱ ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ የቤተ መቅደሱ በሮችም ወዲያውኑ ተዘጉ። ሰዎቹ ጳውሎስን ሊገድሉት በፈለጉ ጊዜ “የኢየሩሳሌም ከተማ በሙሉ ታውካለች” የሚል መልእክት ለሮማውያኑ ጦር አዛዥ ደረሰ። ስለዚህ እርሱ ወታደሮችንና የመቶ አለቆችን አስከትሎ በፍጥነት እየሮጠ ወደ ሰዎቹ ሄደ። ሰዎቹም አዛዡንና ወታደሮቹን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መደብደብ ተዉ። አዛዡም ቀርቦ ጳውሎስን ያዘውና በሁለት ሰንሰለት እንዲታሰር አዘዘ፤ ከዚህ በኋላ ማን መሆኑንና ምን እንዳደረገ ለማወቅ ፈልጎ ጠየቀ። ሕዝቡም አንዳንዶቹ አንድ ነገር ሲሉ፥ ሌሎች ሌላ ነገር ይሉ ነበር፤ አዛዡ ከሕዝቡ ጩኸት የተነሣ እርግጠኛውን ነገር ለማወቅ ስላልቻለ ጳውሎስን ወደ ወታደሮቹ ሰፈር እንዲወስዱት አዘዘ። ጳውሎስ ወደ ደረጃው በደረሰ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ በብርቱ ቊጣ ተነሣሥቶ አደጋ ሊያደርስበት በመፈለጉ ወታደሮቹ ተሸክመውት ሄዱ። ሕዝቡም “ይገደል!” እያሉ በመጮኽ ይከተሉት ነበር። ወታደሮች ወደ ጦር ሰፈራቸው ሊያስገቡት በቀረቡ ጊዜ ጳውሎስ የጦር አዛዡን “አንድ ነገር እንድነግርህ ትፈቅድልኛለህን?” አለው። አዛዡም “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን? ታዲያ፥ አሁን በቅርቡ ብጥብጥ አስነሥቶና አራት ሺህ ነፍሰ ገዳዮች ይዞ ወደ በረሓ የሸሸው ግብጻዊው አንተ አይደለህምን?” አለ። ጳውሎስም “እኔ በኪልቅያ በምትገኘውና ዝነኛ በሆነችው በጠርሴስ ከተማ የተወለድኩ አይሁዳዊ ነኝ፤ እባክህ ለሕዝቡ እንድናገር ፍቀድልኝ” አለው። እንዲናገር በፈቀደለት ጊዜ ጳውሎስ በደረጃ ላይ ቆሞ ሕዝቡ ዝም እንዲል በእጁ ጠቀሰ፤ ሕዝቡ ጸጥ ባለ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤
ሐዋርያት ሥራ 21:27-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሰባቱ ቀንም ይፈጸም ዘንድ ሲቀርብ ከእስያ የመጡ አይሁድ በመቅደስ አይተውት ሕዝብን ሁሉ አወኩና “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! እርዱን፤ ሕዝብን ሕግንም ይህንም ስፍራ ሲቃወም ሰውን ሁሉ በየስፍራው የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ጨምሮም የግሪክን ሰዎች ደግሞ ወደ መቅደስ አግብቶ ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል፤” ብለው እየጮኹ እጃቸውን ጫኑበት። በፊት የኤፌሶኑን ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና ጳውሎስም ወደ መቅደስ ያገባው መስሎአቸው ነው። ከተማውም ሁሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሰበሰቡ ጳውሎስንም ይዘው ከመቅደስ ውጭ ጎተቱት፤ ወዲያውም ደጆች ተዘጉ። ሊገድሉትም ሲፈልጉ “ኢየሩሳሌም ፈጽማ ታወከች፤” የሚል ወሬ ወደ ጭፍራው ሻለቃ ወጣ፤ እርሱም ያንጊዜ ወታደሮችን ከመቶ አለቆች ጋር ይዞ እየሮጠ ወደ እነርሱ ወረደ፤ እነርሱም የሻለቃውንና ወታደሮችን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታት ተዉ። በዚያን ጊዜም የሻለቃው ቀርቦ ያዘውና በሁለት ሰንሰለት ይታሰር ዘንድ አዞ ማን እንደ ሆነና ምን እንዳደረገ ጠየቀ። ሕዝቡም እኩሌቶቹ እንዲህ እኩሌቶቹም እንዲያ እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ስለ ጫጫታውም እርግጡን ማወቅ ባልተቻለ ጊዜ፥ ወደ ወታደሮች ሰፈር ይወስዱት ዘንድ አዘዘ። ወደ ደረጃውም በደረሰ ጊዜ ስለ ሕዝቡ ግፊያ ወታደሮች እንዲሸከሙት ሆነ፤ ብዙ ሕዝብ “አስወግደው!” እያሉና እየጮኹ ይከተሉ ነበርና። ወደ ሰፈርም ሊያገቡት በቀረቡ ጊዜ፥ ጳውሎስ የሻለቃውን “አንድ ነገር ብነግርህ ትፈቅዳለህን?” አለው። እርሱም “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን? አንተ ከዚህ ዘመን አስቀድሞ ከነፍሰ ገዳዮቹ አራቱን ሺህ ሰዎች አሸፍተህ ወደ ምድረ በዳ ያወጣህ የግብጽ ሰው አይደለህምን?” አለ። ጳውሎስ ግን “እኔስ አይሁዳዊ በኪልቅያ ያለው የጠርሴስ ሰው ሆኜ ስመ ጥር በሆነ ከተማ የምኖር ነኝ፤ ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ፤” አለ። በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ በእጁ ወደ ሕዝቡ ጠቀሰ፤ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እየተናገረ እንዲህ አለ።