የሐዋርያት ሥራ 21:27-40

የሐዋርያት ሥራ 21:27-40 አማ05

ሰባቱ ቀን ሊፈጸም ሲቃረብ ከእስያ የመጡ አይሁድ ጳውሎስን በቤተ መቅደስ በማየታቸው ሕዝቡን ሁሉ አሳድመው ያዙት፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! እርዱን! ሕዝባችንንና ሕጋችንን፥ ይህንንም ስፍራ እየተሳደበ በየአገሩ ያለውን ሕዝብ ሁሉ የሚያስተምር ይህ ሰው ነው፤ ይህም አልበቃ ብሎት አሕዛብን ወደ ቤተ መቅደስ በማስገባት ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል!” እያሉ ጮኹ። ይህንንም ያሉበት ምክንያት ከዚህ ቀደም የኤፌሶኑን ተወላጅ ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ስለ ነበር እርሱን ጳውሎስ ወደ ቤተ መቅደስ ይዞት የገባ መስሎአቸው ነበር። ከተማዋ በሙሉ ታወከች፤ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ በአንድነት መጡና ጳውሎስን ይዘው እየጐተቱ ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ የቤተ መቅደሱ በሮችም ወዲያውኑ ተዘጉ። ሰዎቹ ጳውሎስን ሊገድሉት በፈለጉ ጊዜ “የኢየሩሳሌም ከተማ በሙሉ ታውካለች” የሚል መልእክት ለሮማውያኑ ጦር አዛዥ ደረሰ። ስለዚህ እርሱ ወታደሮችንና የመቶ አለቆችን አስከትሎ በፍጥነት እየሮጠ ወደ ሰዎቹ ሄደ። ሰዎቹም አዛዡንና ወታደሮቹን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መደብደብ ተዉ። አዛዡም ቀርቦ ጳውሎስን ያዘውና በሁለት ሰንሰለት እንዲታሰር አዘዘ፤ ከዚህ በኋላ ማን መሆኑንና ምን እንዳደረገ ለማወቅ ፈልጎ ጠየቀ። ሕዝቡም አንዳንዶቹ አንድ ነገር ሲሉ፥ ሌሎች ሌላ ነገር ይሉ ነበር፤ አዛዡ ከሕዝቡ ጩኸት የተነሣ እርግጠኛውን ነገር ለማወቅ ስላልቻለ ጳውሎስን ወደ ወታደሮቹ ሰፈር እንዲወስዱት አዘዘ። ጳውሎስ ወደ ደረጃው በደረሰ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ በብርቱ ቊጣ ተነሣሥቶ አደጋ ሊያደርስበት በመፈለጉ ወታደሮቹ ተሸክመውት ሄዱ። ሕዝቡም “ይገደል!” እያሉ በመጮኽ ይከተሉት ነበር። ወታደሮች ወደ ጦር ሰፈራቸው ሊያስገቡት በቀረቡ ጊዜ ጳውሎስ የጦር አዛዡን “አንድ ነገር እንድነግርህ ትፈቅድልኛለህን?” አለው። አዛዡም “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን? ታዲያ፥ አሁን በቅርቡ ብጥብጥ አስነሥቶና አራት ሺህ ነፍሰ ገዳዮች ይዞ ወደ በረሓ የሸሸው ግብጻዊው አንተ አይደለህምን?” አለ። ጳውሎስም “እኔ በኪልቅያ በምትገኘውና ዝነኛ በሆነችው በጠርሴስ ከተማ የተወለድኩ አይሁዳዊ ነኝ፤ እባክህ ለሕዝቡ እንድናገር ፍቀድልኝ” አለው። እንዲናገር በፈቀደለት ጊዜ ጳውሎስ በደረጃ ላይ ቆሞ ሕዝቡ ዝም እንዲል በእጁ ጠቀሰ፤ ሕዝቡ ጸጥ ባለ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤