ሰባቱ ቀንም ይፈጸም ዘንድ ሲቀርብ ከእስያ የመጡ አይሁድ በመቅደስ አይተውት ሕዝብን ሁሉ አወኩና፦ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ እርዱን ሕዝብን ሕግንም ይህንም ስፍራ ሲቃወም ሰውን ሁሉ በየስፍራው የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ጨምሮም የግሪክን ሰዎች ደግሞ ወደ መቅደስ አግብቶ ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል ብለው እየጮኹ እጃቸውን ጫኑበት። በፊት የኤፌሶኑን ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና ጳውሎስም ወደ መቅደስ ያገባው መስሎአቸው ነው። ከተማውም ሁሉ ታወከ ሕዝቡም ሁሉ ተሰበሰቡ ጳውሎስንም ይዘው ከመቅደስ ውጭ ጎተቱት፥ ወዲያውም ደጆች ተዘጉ። ሊገድሉትም ሲፈልጉ፦ ኢየሩሳሌም ፈጽማ ታወከች የሚል ወሬ ወደ ጭፍራው ሻለቃ ወጣ፤ እርሱም ያን ጊዜ ወታደሮችን ከመቶ አለቆች ጋር ይዞ እየሮጠ ወረደባቸው፤ እነርሱም የሻለቃውንና ወታደሮችን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታት ተዉ። በዚያን ጊዜም የሻለቃው ቀርቦ ያዘውና በሁለት ሰንሰለት ይታሰር ዘንድ አዞ ማን እንደ ሆነና ምን እንዳደረገ ጠየቀ። ሕዝቡም እኵሌቶቹ እንዲህ እኵሌቶቹም እንዲያ እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ስለ ጫጫታውም እርግጡን ማወቅ ባልተቻለ ጊዜ፥ ወደ ወታደሮች ሰፈር ይወስዱት ዘንድ አዘዘ። ወደ ደረጃውም በደረሰ ጊዜ ስለ ሕዝቡ ግፊያ ወታደሮች እንዲሸከሙት ሆነ፤ ብዙ ሕዝብ፦ አስወግደው እያሉና እየጮኹ ይከተሉ ነበርና። ወደ ሰፈርም ሊያገቡት በቀረቡ ጊዜ፥ ጳውሎስ የሻለቃውን፦ አንድ ነገር ብነግርህ ትፈቅዳለህን? አለው። እርሱም፦ የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን? አንተ ከዚህ ዘመን አስቀድሞ ከነፍሰ ገዳዮቹ አራቱን ሺህ ሰዎች አሸፍተህ ወደ ምድረ በዳ ያወጣህ የግብፅ ሰው አይደለህምን? አለ። ጳውሎስ ግን፦ እኔስ አይሁዳዊ በኪልቅያ ያለው የጠርሴስ ሰው ሆኜ ስመ ጥር በሆነ ከተማ የምኖር ነኝ፤ ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ አለ። በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ በእጁ ወደ ሕዝቡ ጠቀሰ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እየተናገረ እንዲህ አለ።
የሐዋርያት ሥራ 21 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 21:27-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos