ሐዋርያት ሥራ 16:16-24
ሐዋርያት ሥራ 16:16-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ቀን ወደ ጸሎት ስፍራ ስንሄድ፣ በጥንቈላ መንፈስ ትንቢት የምትናገር አንዲት የቤት አገልጋይ አገኘችን፤ እርሷም በዚህ የጥንቈላ ሥራዋ ለአሳዳሪዎቿ ብዙ ገንዘብ ታስገኝላቸው ነበር። ይህችው አገልጋይ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፣ “እነዚህ ሰዎች የመዳንን መንገድ የሚነግሯችሁ፣ የልዑል እግዚአብሔር ባሮች ናቸው!” በማለት ትጮኽ ነበር፤ ይህንም ብዙ ቀን ደጋገመችው፤ ጳውሎስ ግን በዚህ እጅግ በመታወኩ ዘወር ብሎ ያን መንፈስ፣ “ከርሷ እንድትወጣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዝሃለሁ” አለው፤ መንፈሱም በዚያው ቅጽበት ወጣላት። አሳዳሪዎቿም የገንዘብ ማግኛ ተስፋቸው ወጥቶ መሄዱን በተረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጐተቱ ባለሥልጣኖች ወዳሉበት ወደ ገበያ ቦታ አመጧቸው። ገዦቹም ፊት አቅርበዋቸው እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ሳሉ፣ ከተማችንን አውከዋል፤ ደግሞም እኛ ሮማውያን መቀበል ወይም መፈጸም ያልተፈቀደልንን ልማድ በሕዝቡ መካከል ይነዛሉ።” ሕዝቡም ተባብረው በጳውሎስና በሲላስ ላይ ተነሡባቸው፤ ገዦቹም ልብሳቸው ተገፍፎ በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ። ክፉኛ ከተደበደቡ በኋላም ወደ ወህኒ ቤት አስገቧቸው፤ የወህኒ ቤት ጠባቂውም ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም ይህን የመሰለ ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፣ ወደ ወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገብቶ እግራቸውን ከግንድ ጋራ አጣብቆ አሰራቸው።
ሐዋርያት ሥራ 16:16-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ለጸሎት ስንሄድም የምዋርተኛነት መንፈስ ያደረባት አንዲት ልጅ አገኘችን፤ በጥንቈላም የምታገኘውን ብዙ እጅ መንሻ ለጌቶችዋ ታገባ ነበር። ከዚህም በኋላ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፥ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው፤ የሕይወትንም መንገድ ያስተምሩአችኋል” እያለች ትጮኽ ነበር። ብዙ ቀንም እንዲሁ ታደርግ ነበር፤ ጳውሎስንም አሳዘነችው፤ መለስ ብሎም፥ “መንፈስ ርኩስ፥ ከእርስዋ እንድትወጣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዤሃለሁ” አለው፤ ወዲያውኑም ተዋት። ጌቶችዋም የምታገባላቸው የጥቅማቸው ተስፋ እንደ ቀረ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው በገበያ እየጐተቱ ወደ ገዢዎች ወሰዱአቸው። ወደ ገዢዎችም አቅርበው፥ “እነዚህ ሰዎች ከተማችንን ያሸብሩብናል፤ እነርሱም አይሁድ ናቸው። እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆንም ልናደርገው የማይገባንን ሕግ ይናገራሉ” አሉ። ሕዝቡም ተነሡባቸው፤ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፍፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ። በብዙም ደብድበው አሰሩአቸው፤ የወህኒ ቤቱን ዘበኛም አጽንቶ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም ትእዛዙን ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ቤት አስገባቸው፤ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው።
ሐዋርያት ሥራ 16:16-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ “የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው” ብላ ትጮኽ ነበር። ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ “ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ” አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ። ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤ ወደ ገዢዎም አቅርበው፦ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ” አሉ። ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፥ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸ።
ሐዋርያት ሥራ 16:16-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ቀን ወደ ጸሎት ቦታ ስንሄድ ወደፊት የሚሆነውን ነገር በጥንቈላ የሚያናግር ርኩስ መንፈስ ያደረባት አንዲት አገልጋይ ልጃገረድ በመንገድ አገኘችን፤ ይህች ልጃገረድ በጥንቈላዋ ለአሳዳሪዎችዋ ብዙ ትርፍ ታስገኝላቸው ነበር። እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፥ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው! እነርሱ የመዳንን መንገድ ያበሥሩአችኋል!” በማለት ትጮኽ ነበር። ይህንንም ብዙ ቀን እየደጋገመች ታደርግ ነበር፤ ጳውሎስ ግን ተበሳጨና ዞር ብሎ ርኩሱን መንፈስ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከእርስዋ እንድትወጣ አዝሃለሁ!” አለው። ርኩሱም መንፈስ ወዲያውኑ ወጣ። አሳዳሪዎችዋ ጥቅም የሚያገኙበት ተስፋ እንደ ተቋረጠባቸው ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ያዙአቸው፤ እየጐተቱም ወደ አደባባይ ወሰዱአቸውና በሹሞች ፊት አቀረቡአቸው። ወደ ሮማውያን ባለሥልጣኖችም አመጡአቸውና እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች የአይሁድ ወገኖች ናቸው፤ በከተማችንም ሁከት ያስነሣሉ፤ እኛ የሮም ዜጋዎች ልንቀበለው ወይም ልናደርገው ያልተፈቀደልንን ሥርዓት ያስተምራሉ።” ሕዝቡም ሁሉ ተባብሮ በእነርሱ ላይ ተነሣ። ባለሥልጣኖችም የጳውሎስንና የሲላስን ልብስ ገፈፉና በዱላ እንዲደበደቡ አዘዙ። ብዙ ከተደበደቡም በኋላ ወደ ወህኒ ቤት አገቡአቸው፤ የወህኒ ቤቱም ጠባቂ በጥብቅ እንዲጠብቃቸው ታዘዘ። ጠባቂው ይህን ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፥ በወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገባቸው፤ እግሮቻቸውንም በግንድና ግንድ መካከል አጣብቆ አሰራቸው።
ሐዋርያት ሥራ 16:16-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቆለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። እርሷ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች “የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባርያዎች ናቸው፤” ብላ ትጮኽ ነበር። ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን “ከእርሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ፤” አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ። ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤ ወደ ገዢዎም አቅርበው “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ፤” አሉ። ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፤ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፤ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፤ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸ።