የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 16:16-24

የሐዋርያት ሥራ 16:16-24 አማ05

አንድ ቀን ወደ ጸሎት ቦታ ስንሄድ ወደፊት የሚሆነውን ነገር በጥንቈላ የሚያናግር ርኩስ መንፈስ ያደረባት አንዲት አገልጋይ ልጃገረድ በመንገድ አገኘችን፤ ይህች ልጃገረድ በጥንቈላዋ ለአሳዳሪዎችዋ ብዙ ትርፍ ታስገኝላቸው ነበር። እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፥ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው! እነርሱ የመዳንን መንገድ ያበሥሩአችኋል!” በማለት ትጮኽ ነበር። ይህንንም ብዙ ቀን እየደጋገመች ታደርግ ነበር፤ ጳውሎስ ግን ተበሳጨና ዞር ብሎ ርኩሱን መንፈስ “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከእርስዋ እንድትወጣ አዝሃለሁ!” አለው። ርኩሱም መንፈስ ወዲያውኑ ወጣ። አሳዳሪዎችዋ ጥቅም የሚያገኙበት ተስፋ እንደ ተቋረጠባቸው ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ያዙአቸው፤ እየጐተቱም ወደ አደባባይ ወሰዱአቸውና በሹሞች ፊት አቀረቡአቸው። ወደ ሮማውያን ባለሥልጣኖችም አመጡአቸውና እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች የአይሁድ ወገኖች ናቸው፤ በከተማችንም ሁከት ያስነሣሉ፤ እኛ የሮም ዜጋዎች ልንቀበለው ወይም ልናደርገው ያልተፈቀደልንን ሥርዓት ያስተምራሉ።” ሕዝቡም ሁሉ ተባብሮ በእነርሱ ላይ ተነሣ። ባለሥልጣኖችም የጳውሎስንና የሲላስን ልብስ ገፈፉና በዱላ እንዲደበደቡ አዘዙ። ብዙ ከተደበደቡም በኋላ ወደ ወህኒ ቤት አገቡአቸው፤ የወህኒ ቤቱም ጠባቂ በጥብቅ እንዲጠብቃቸው ታዘዘ። ጠባቂው ይህን ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፥ በወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገባቸው፤ እግሮቻቸውንም በግንድና ግንድ መካከል አጣብቆ አሰራቸው።