የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐዋርያት ሥራ 16:16-24

ሐዋርያት ሥራ 16:16-24 NASV

አንድ ቀን ወደ ጸሎት ስፍራ ስንሄድ፣ በጥንቈላ መንፈስ ትንቢት የምትናገር አንዲት የቤት አገልጋይ አገኘችን፤ እርሷም በዚህ የጥንቈላ ሥራዋ ለአሳዳሪዎቿ ብዙ ገንዘብ ታስገኝላቸው ነበር። ይህችው አገልጋይ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፣ “እነዚህ ሰዎች የመዳንን መንገድ የሚነግሯችሁ፣ የልዑል እግዚአብሔር ባሮች ናቸው!” በማለት ትጮኽ ነበር፤ ይህንም ብዙ ቀን ደጋገመችው፤ ጳውሎስ ግን በዚህ እጅግ በመታወኩ ዘወር ብሎ ያን መንፈስ፣ “ከርሷ እንድትወጣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዝሃለሁ” አለው፤ መንፈሱም በዚያው ቅጽበት ወጣላት። አሳዳሪዎቿም የገንዘብ ማግኛ ተስፋቸው ወጥቶ መሄዱን በተረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጐተቱ ባለሥልጣኖች ወዳሉበት ወደ ገበያ ቦታ አመጧቸው። ገዦቹም ፊት አቅርበዋቸው እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ሳሉ፣ ከተማችንን አውከዋል፤ ደግሞም እኛ ሮማውያን መቀበል ወይም መፈጸም ያልተፈቀደልንን ልማድ በሕዝቡ መካከል ይነዛሉ።” ሕዝቡም ተባብረው በጳውሎስና በሲላስ ላይ ተነሡባቸው፤ ገዦቹም ልብሳቸው ተገፍፎ በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ። ክፉኛ ከተደበደቡ በኋላም ወደ ወህኒ ቤት አስገቧቸው፤ የወህኒ ቤት ጠባቂውም ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም ይህን የመሰለ ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፣ ወደ ወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገብቶ እግራቸውን ከግንድ ጋራ አጣብቆ አሰራቸው።