ሐዋርያት ሥራ 12:12-19
ሐዋርያት ሥራ 12:12-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ በአስተዋለ ጊዜ ብዙዎች ወንድሞች ተሰብስበው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ። ጴጥሮስም በሩን አንኳኳ፤ ሮዴ የምትባል ብላቴናም ልትከፍትለት መጣች። የጴጥሮስም ድምፅ መሆኑን ዐውቃ ከደስታ የተነሣ አልከፈተችለትም፤ ነገር ግን ጴጥሮስ በበር ቆሞ ሳለ ሮጣ ነገረቻቸው። እነርሱም “አብደሻልን? አንድ ጊዜ ታገሺ” አሉአት፤ እርስዋ ግን እርሱ እንደ ሆነ ታረጋግጥ ነበር። እነርሱም፥ “ምናልባት መልአኩ ይሆናል” አሉ። ጴጥሮስ ግን በሩን ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ ከፍተውም ባዩት ጊዜ ተደነቁ። እርሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ አመለከታቸው፤ ከወኅኒ ቤትም እግዚአብሔር እንደ አወጣው ነገራቸው፤ “ይህንም ለያዕቆብና ለወንድሞች ሁሉ ንገሩ” አላቸው፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። በነጋ ጊዜም ወታደሮች፥ “ጴጥሮስ ምን ሆነ?” ብለው ታወኩ። ሄሮድስ ግን አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ፤ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከዚህም በኋላ ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ።
ሐዋርያት ሥራ 12:12-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይህን ከተረዳ በኋላም፣ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው በአንድነት ወደሚጸልዩበት፣ ማርቆስ ወደተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ። እዚያ ደርሶ የውጭውን በር ባንኳኳ ጊዜ፣ ሮዳ የተባለች አንዲት የቤት ሠራተኛ ማን እንደ ሆነ ለማጣራት ወደ በሩ ሄደች። የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ፣ በጣም ከመደሰቷ የተነሣ በሩን ሳትከፍት ሮጣ በመመለስ፣ ጴጥሮስ በሩ ላይ ቆሞ እንደሚገኝ ተናገረች። ሰዎቹም፣ “አብደሻል እንዴ!” አሏት፤ እርሷ ግን ይህንኑ ደጋግማ በነገረቻቸው ጊዜ፣ “እንግዲያውስ የርሱ መልአክ ነው” አሉ። ጴጥሮስ ግን በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ እነርሱም በሩን ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ። እርሱም ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ፣ ጌታ ከእስር ቤት እንዴት እንዳወጣው አስረዳቸው፣ “ስለ ሁኔታው ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሯቸው” አላቸው፤ ከዚያም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። በማግስቱም ጧት ወታደሮቹ፣ “ጴጥሮስ የት ገባ?” እያሉ በመካከላቸው ትልቅ ትርምስ ተፈጠረ። ሄሮድስም ጴጥሮስን አስፈልጎ ባጣው ጊዜ፣ ዘብ ጠባቂዎቹን በጥብቅ ከመረመረ በኋላ እንዲገደሉ አዘዘ።
ሐዋርያት ሥራ 12:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ። ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤ የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፥ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። እነርሱም፦ “አብደሻል” አሉአት። እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ሆነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም፦ “መልአኩ ነው” አሉ። ጴጥሮስ ግን ማንኳኳቱን አዘወተረ፤ ከፍተውም አዩትና ተገረሙ። ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ተረከላቸውና፦ “ይህን ለያዕቆብና ለወንድሞቹ ንገሩ” አላቸው። ወጥቶም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። በነጋም ጊዜ፦ “ጴጥሮስን ምን አግኝቶት ይሆን?” ብለው በጭፍሮች ዘንድ ብዙ ሁከት ሆነ። ሄሮድስም አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከይሁዳም ወደ ቂሣርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ።
ሐዋርያት ሥራ 12:12-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህን ካረጋገጠ በኋላ ብዙ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው ወደሚጸልዩበት ወደ ማርያም ቤት ሄደ፤ ይህችም ማርያም ማርቆስ የተባለው የዮሐንስ እናት ነበረች። ጴጥሮስ እዚያ ደርሶ የውጪውን በር ባንኳኳ ጊዜ ሮዳ የምትባል አንዲት ገረድ ማን እንደ ሆነ ለማወቅ ወደ በሩ መጣች። የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑን ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ ብዛት የተነሣ በሩን ሳትከፍት ሮጣ ወደ ውስጥ ገባችና “ጴጥሮስ በበር ቆሞአል!” ስትል ተናገረች። እነርሱም “አብደሻል!” አሉአት። እርስዋ ግን “በእውነት እርሱ ነው!” ስትል አረጋገጠች፤ እነርሱም እንግዲያውስ “የእርሱ ጠባቂ መልአክ ይሆናል” አሉ። ጴጥሮስ ግን በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ እነርሱም በሩን ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ። እርሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ አመልክቶ ጌታ ከወህኒ ቤት እንዴት እንዳስወጣው አወራላቸውና “ይህን ነገር ለያዕቆብና ለቀሩት ምእመናን ንገሩ” አላቸው። ተለይቶአቸውም ወደ ሌላ ቦታ ሄደ። በነጋም ጊዜ ወታደሮቹ “ጴጥሮስ ምን ደርሶበት ይሆን?” በማለት እጅግ ታወኩ። ሄሮድስም በበኩሉ ጴጥሮስን አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ዘብ ጠባቂዎችን ከመረመረ በኋላ እንዲገደሉ አዘዘ፤ ከዚህም በኋላ ሄሮድስ ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ሄዶ እዚያ ተቀመጠ።
ሐዋርያት ሥራ 12:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ። ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤ የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፤ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። እነርሱም “አብደሻል!” አሏት። እርሷ ግን እንዲሁ እንደሆነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም “መልአኩ ነው፤” አሉ። ጴጥሮስ ግን ማንኳኳቱን አዘወተረ፤ ከፍተውም አዩትና ተገረሙ። ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ተረከላቸውና “ይህን ለያዕቆብና ለወንድሞቹ ንገሩ፤” አላቸው። ወጥቶም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። በነጋም ጊዜ “ጴጥሮስን ምን አግኝቶት ይሆን?” ብለው በጭፍሮች ዘንድ ብዙ ሁከት ሆነ። ሄሮድስም አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ፤ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከይሁዳም ወደ ቂሣርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ።