የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ሳሙኤል 15:1-17

2 ሳሙኤል 15:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚ​ህም በኋላ አቤ​ሴ​ሎም ሰረ​ገ​ላና ፈረ​ሶች፥ በፊ​ቱም የሚ​ሮጡ አምሳ ሰዎች አዘ​ጋጀ። አቤ​ሴ​ሎ​ምም በማ​ለዳ ተነ​ሥቶ በበሩ ጎዳና ይቆም ነበር፤ አቤ​ሴ​ሎ​ምም ከን​ጉሥ ለማ​ስ​ፈ​ረድ ጉዳይ የነ​በ​ረ​ውን ሁሉ ወደ እርሱ እየ​ጠራ፥ “አንተ ከወ​ዴት ከተማ ነህ?” ብሎ ይጠ​ይቅ ነበር። እር​ሱም፥ “እኔ አገ​ል​ጋ​ይህ ከእ​ስ​ራ​ኤል ወገን ከአ​ን​ዲቱ ነኝ” ይለው ነበር። አቤ​ሴ​ሎ​ምም፥ “ነገ​ርህ መል​ካም ነው፤ ቀላ​ልም ነው፤ ነገር ግን ከን​ጉሥ ዘንድ የሚ​ሰ​ማህ የለም” ይለው ነበር። አቤ​ሴ​ሎ​ምም፥ “ነገ​ርና ክር​ክር ያለው ሁሉ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ፥ ቅንም ፍርድ እፈ​ር​ድ​ለት ዘንድ በሀ​ገር ላይ ፈራጅ አድ​ርጎ ማን በሾ​መኝ?” ይል ነበር። ሰውም እጅ ለመ​ን​ሣት ወደ እርሱ በቀ​ረበ ጊዜ እጁን ዘር​ግቶ አቅፎ ይስ​መው ነበር። በን​ጉሡ ዘንድ ሊፋ​ረዱ ለሚ​መጡ ለእ​ስ​ራ​ኤል ሁሉ አቤ​ሴ​ሎም እን​ዲህ ያደ​ርግ ነበር፤ አቤ​ሴ​ሎ​ምም የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ሰዎች ልብ ማረከ። እን​ዲ​ህም ሆነ፤ ከአ​ራት ዓመት በኋላ አቤ​ሴ​ሎም አባ​ቱን፥ “ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ሳ​ል​ሁ​ትን ስእ​ለት በኬ​ብ​ሮን አደ​ርግ ዘንድ ልሂድ። እኔ አገ​ል​ጋ​ይህ በሶ​ርያ ጌድ​ሶር ሳለሁ፦ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ቢመ​ል​ሰኝ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መሥ​ዋ​ዕት አቀ​ር​ባ​ለሁ ብዬ ስእ​ለት ተስዬ ነበ​ርና” አለው። ንጉ​ሡም፥ “በሰ​ላም ሂድ” አለው፤ ተነ​ሥ​ቶም ወደ ኬብ​ሮን ሄደ። አቤ​ሴ​ሎ​ምም፥ “የመ​ለ​ከት ድምፅ በሰ​ማ​ችሁ ጊዜ፥ አቤ​ሴ​ሎም በኬ​ብ​ሮን ነገሠ” በሉ የሚሉ ጕበ​ኞ​ችን ወደ እስ​ራ​ኤል ነገድ ሁሉ ላከ። የተ​ጠ​ሩ​ትም ሁለት መቶ ሰዎች ከአ​ቤ​ሴ​ሎም ጋር ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ሄዱ፤ እነ​ር​ሱም በየ​ዋ​ህ​ነት ሄዱ፤ ነገ​ሩ​ንም ሁሉ ከቶ አያ​ው​ቁም ነበር። አቤ​ሴ​ሎ​ምም መሥ​ዋ​ዕት በሚ​ሠ​ዋ​በት ጊዜ የዳ​ዊት አማ​ካሪ ወደ ነበ​ረው ጌሎ​ና​ዊው አኪ​ጦ​ፌል ወደ ከተ​ማው ጊሎ ላከ። ሴራ​ውም ጽኑ ሆነ፤ ከአ​ቤ​ሴ​ሎ​ምም ጋር ያለው ሕዝብ እጅግ በዛ። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ሰዎች ልብ ወደ አቤ​ሴ​ሎም ተመ​ል​ሶ​አል የሚል መል​እ​ክ​ተኛ ወደ ዳዊት ሄደ። ዳዊ​ትም ከእ​ርሱ ጋር በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ያሉ​ትን አገ​ል​ጋ​ዮ​ቹን ሁሉ፥ “ተነሡ እን​ሽሽ፤ ከአ​ቤ​ሴ​ሎም እጅ የም​ን​ድ​ን​በት የለ​ን​ምና፤ ፈጥኖ እን​ዳ​ይ​ዘን፥ ክፉም እን​ዳ​ያ​መ​ጣ​ብን፤ ከተ​ማ​ዪ​ቱ​ንም በሰ​ልፍ ስለት እን​ዳ​ይ​መታ ፈጥ​ና​ችሁ እን​ሂድ” አላ​ቸው። የን​ጉ​ሡም ብላ​ቴ​ኖች ንጉ​ሡን፥ “እነሆ፥ ጌታ​ችን ንጉሥ የመ​ረ​ጠ​ውን ሁሉ እኛ አገ​ል​ጋ​ዮ​ችህ እና​ደ​ር​ጋ​ለን” አሉት። ንጉ​ሡና ከእ​ር​ሱም በኋላ ቤተ ሰቡ ሁሉ በእ​ግ​ራ​ቸው ወጡ፤ ንጉ​ሡም ቁባ​ቶቹ የነ​በሩ ዐሥ​ሩን ሴቶች ቤቱን ይጠ​ብቁ ዘንድ ተወ። ንጉ​ሡና ሕዝቡ ሁሉ በእ​ግር ወጡ፤ በሩ​ቅም ቦታ ቆሙ።

2 ሳሙኤል 15:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች እንዲሁም ፊት ፊቱ የሚሮጡ አምሳ ሰዎች ለራሱ አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ሆን ብሎ ይቆም ነበር። ማናቸውም ባለ ጕዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፣ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፣ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፣ “አገልጋይህ ከአንዱ የእስራኤል ነገዶች ነው” ብሎ ይመልስለታል። ከዚያም አቤሴሎም፣ “ተመልከት! ጕዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ የትኛው የንጉሥ እንደ ራሴ ነው ታዲያ የሚያይልህ?” ይለዋል። ቀጠል አድርጎም፣ “ምነው ዳኛ ሆኜ በምድሪቱ ላይ በተሾምሁ አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ እየመጣ ፍትሕ እንዲያገኝ አደርገው ነበር” ይል ነበር። እንዲሁም ማናቸውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፣ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር። አቤሴሎም ፍትሕ ለማግኘት ወደ ንጉሡ የሚመጣውን እስራኤላዊ ሁሉ የሚቀርበው በዚህ መንገድ ስለ ነበር፣ የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በጌሹር ሳለሁ ‘እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደ ሆነ፣ በኬብሮን ለእግዚአብሔር እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።” ንጉሡም፣ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ። ከዚያም አቤሴሎም፣ “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፣ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ’ ” የሚሉ የምስጢር ሠራተኞችን በመላው የእስራኤል ነገዶች አሰማራ። ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አብረውት ሄዱ፤ በእንግድነት ተጋብዘው በየዋህነት ከመሄዳቸው በስተቀር፣ ስለ ጕዳዩ የሚያውቁት አንዳችም ነገር አልነበረም። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው ጊሎኣዊው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየጨመረ መጣ። መልእክተኛም መጥቶ፣ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኗል” ብሎ ለዳዊት ነገረው። ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት ሹማምቱ ሁሉ፣ “ተነሡ እንሽሽ፤ አለዚያ አንዳችንም ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ አሁኑኑ ከዚህ መውጣት አለብን፤ ካልሆነ ገሥግሦ መጥቶ ከያዘን እኛን ያጠፋናል፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ይመታታል” አላቸው። የንጉሡ ሹማምትም፣ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት። ንጉሡ ከመላው ቤተ ሰቡ ጋር ወጣ፤ ቤተ መንግሥቱንም እንዲጠብቁ ዐሥር ቁባቶች አስቀረ። ስለዚህ ንጉሡ መላውን ሕዝብ አስከትሎ ወጣ፤ ጥቂት ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቦታ ቆሙ።

2 ሳሙኤል 15:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዚህም በኋላ አቤሴሎም ሰረገላና ፈረሶች፥ በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ በበሩ አደበባይ ይቆም ነበር፥ አቤሴሎምም ከንጉሥ ለማስፈረድ ጉዳይ የነበረውን ሁሉ ወደ እርሱ እየጠራ፦ አንተ ከወዴት ከተማ ነህ? ብሎ ይጠይቅ ነበር። እርሱም፦ እኔ ባሪያህ ከእስራኤል ነገድ ከአንዲቱ ነኝ ብሎ ይመልስ ነበር። አቤሴሎምም፦ ነገርህ እውነትና ቅን ነው፥ ነገር ግን ከንጉሥ ታዝዞ የሚሰማህ የለም ይለው ነበር። አቤሴሎምም፦ ነገርና ክርክር ያለው ሁሉ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ ቅንም ፍርድ እፈርድለት ዘንድ በአገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ? ይል ነበር። ሰውም እጅ ሊነሣው ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ እጁን ዘርግቶ ይይዝና ይስመው ነበር። እንዲሁም አቤሴሎም ከንጉሥ ፍርድ ሊሰማ ከእስራኤል ዘንድ በሚመጣ ሁሉ ያደርግ ነበር፥ አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። እንዲህም ሆነ፥ ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም ንጉሡን፦ ለእግዚአብሔር የተሳልሁትን ስእለት ለመስጠት ወደ ኬብሮን፥ እባክህ፥ ልሂድ። እኔ ባሪያህ በሶርያ ጌሹር ሳለሁ፦ እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም ቢመልሰኝ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀርባለሁ ብዬ ስእለት ተስዬ ነበር አለው። ንጉሡም፦ በደኅና ሂድ አለው፥ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። አቤሴሎምም በእስራኤል ነገድ ሁሉ፦ የቀንደ መለከት ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፦ አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ የሚሉ ጉበኞች ላከ። የተጠሩትም ሁለት መቶ ሰዎች ከአቤሴሎም ጋር በየዋህነት ከኢየሩሳሌም ሄዱ፥ የሚሆነውንም ነገር ከቶ አያውቁም ነበር። አቤሴሎምም የዳዊት መካር የነበረውን የጊሎ ሰው አኪጦፌልን ከከተማው ከጊሎ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ አስጠራው። ሴራውም ጽኑ ሆነ፥ ከአቤሴሎምም ጋር ያለውች ሕዝብ እየበዛ ሄደ። ለዳዊትም፦ የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል የሚል ወሬኛ መጣለት። ዳዊትም ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ያሉትን ባሪያዎቹን ሁሉ፦ ተነሡ፥ እንሽሽ፥ ያለዚያ ከአቤሴሎም እጅ የሚድን ከእኛ የለምና፥ መጥቶም እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ አላቸው። የንጉሡም ባሪያዎች ንጉሡን፦ እነሆ፥ ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ እኛ ባሪያዎችህ እሺ ብለን እናደርጋለን አሉት። ንጉሡም ከእርሱም በኋላ ቤተ ሰቡ ሁሉ ወጡ፥ ንጉሡም አሥሩን ሴቶች ቁባቶቹን ቤቱን ይጠብቁ ዘንድ ተወ። ንጉሡም ከእርሱም በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ወጡ፥ በቤትሜርሐቅም ቆሙ።

2 ሳሙኤል 15:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ አቤሴሎም አንድ ሠረገላና ፈረሶች ለራሱ አደራጀ፤ እንዲሁም ኀምሳ ጋሻ ጃግሬዎች እንዲኖሩት አደረገ፤ በማለዳ እየተነሣ በመሄድ ወደ ከተማይቱ ቅጽር በር በሚያስገባው መንገድ ዳር ይቆም ነበር፤ ንጉሡ ጉዳዩን እንዲያይለት የሚፈልግ ጠብ ክርክር ያለበት ሰው ሁሉ ወደዚያ ሲመጣ አቤሴሎም ጠርቶ ከወዴት እንደ መጣ ይጠይቀዋል፤ ሰውየው ከየትኛው ነገድ መሆኑን ከነገረው በኋላ፥ አቤሴሎም፥ “ተመልከት፤ ሕግ አንተን ይደግፍሃል፤ ነገር ግን በንጉሡ ተወክሎ ጉዳይህን በትክክል የሚያይልህ የለም” ይለዋል፤ ንግግሩንም በመቀጠል “እኔ ዳኛ ብሆን እንዴት በወደድሁ ነበር! ክርክር ወይም አቤቱታ ያለበት ሰው ወደ እኔ ሲመጣ እኔ ትክክለኛውን ፍርድ እሰጠው ነበር” ይለዋል። ሰውየው በፊቱ ለጥ ብሎ እጅ ለመንሣት በሚቀርብበት ጊዜ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ በማቀፍ ይስመዋል። አቤሴሎም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጡት ሁሉ እንደዚህ ያደርግ ስለ ነበር የእነርሱን ልብ ለመማረክ ቻለ። ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም ንጉሥ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ! ለእግዚአብሔር የተሳልኩትን ስእለት ለመፈጸም ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ! እኔ አገልጋይህ በሶርያ በምትገኘው በገሹር በኖርኩበት ጊዜ ‘ወደ ኢየሩሳሌም ብትመልሰኝ መሥዋዕት አቀርብልሃለሁ’ ብዬ ለእግዚአብሔር ስእለት ተስዬ ነበር።” ንጉሡም “በሰላም ሂድ!” አለው፤ ስለዚህም አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ፤ “ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገዶች ሁሉ መልእክተኞችን ልኮ የእምቢልታ ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ ድምፃችሁን ከፍ በማድረግ ‘አቤሴሎም የኬብሮን ንጉሥ ሆኗል!’ ብላችሁ ጩኹ” ብለው እንዲነግሩአቸው አደረገ። በአቤሴሎም ጋባዥነት ከእርሱ ጋር ከኢየሩሳሌም የሄዱ ሁለት መቶ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ተከትለውት የሄዱት ስለ ሤራው ምንም ነገር ሳያውቁ በቅንነት ነበር። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ከንጉሥ ዳዊት አማካሪዎች አንዱ የሆነውን አኪጦፌል ተብሎ የሚጠራውን ሰው መልእክተኛ በመላክ ከጊሎ ከተማ አስጠራ፤ በንጉሡ ላይ የተጠነሰሰው ሤራ እየጠነከረ፥ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቊጥር እየጨመረ ሄደ። አንድ መልእክተኛ ዳዊትን “እስራኤላውያን ታማኝነታቸውን ለአቤሴሎም በመግለጥ ላይ ናቸው” አለው። ስለዚህም ዳዊት ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ለሚገኙት መኳንንቱ ሁሉ “ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ ከፈለግን በፍጥነት ከዚህ ሸሽተን እንውጣ! እንግዲህ ፍጠኑ! አለበለዚያ በፍጥነት መጥቶ ድል ይመታናል፤ በከተማይቱ ያገኘውንም ሁሉ ይገድላል!” አላቸው። እነርሱም “እሺ ንጉሥ ሆይ! አንተ ያልከውን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ነን” ሲሉ መለሱለት። ስለዚህ ንጉሡ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቁለት ዘንድ ካስቀራቸው ዐሥር ቊባቶች በቀር ቤተሰቡንና መኳንንቱን ሁሉ በማስከተል ሸሽቶ ሄደ። ንጉሡና ተከታዮቹ ሁሉ ከከተማይቱ ወጥተው በሚሄዱበት ጊዜ በከተማይቱ መጨረሻ ላይ በሚገኘው አንድ ቤት አጠገብ ቆሙ፤

2 ሳሙኤል 15:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች፥ ፊት ፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ይቆም ነበር። ማናቸውም ባለ ጉዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፥ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፥ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፥ “አገልጋይህ ከእስራኤል ነገዶች ከአንዱ ነው” ብሎ ይመልስለታል። ከዚያም አቤሴሎም፥ “ተመልከት! ጉዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ ነገር ግን ከንጉሥ ተወክሎ የሚሰማህ የለም” ይለው ነበር። ከዚህም ሌላ አቤሴሎም፥ “በምድሪቱ ላይ ዳኛ እኔ በሆንኩ ኖሮ! አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ ሲመጣ፥ ፍትሕ እንዲያገኝ ባደረግሁ ነበር” ይል ነበር። እንዲሁም ማናቸውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፥ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር። አቤሴሎም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጣ እስራኤላዊ ሁሉ አቀራረቡ እንዲህ ነበር፤ ስለዚህ አቤሴሎም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “በኬብሮን ለጌታ የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በገሹር ሳለሁ ‘ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደሆነ፥ በኬብሮን ለጌታ እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።” ንጉሡም፥ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። ነገር ግን አቤሴሎም፥ በመላው የእስራኤል ነገዶች መሀል “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፥ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ’ ” የሚሉ የምስጢር መልእክተኞችን ላከ። ከአቤሴሎም ጋር ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አብረውት ሄደው ነበር፤ በእንግድነት ተጋብዘው በቅንነት ከመሄዳቸው በስተቀር፥ ስለጉዳዩ ምንም ነገር አያውቁም ነበር። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው ጊሎአዊው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየበዛ ሄደ። መልእክተኛም መጥቶ፥ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል” ብሎ ለዳዊት ነገረው። ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት አገልጋዮቹ ሁሉ፥ “ተነሡ እንሽሽ፤ ያለበለዚያ ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ ፈጥኖ እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ” አላቸው። የንጉሡ አገልጋዮቹም፥ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት። ስለዚህ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ ካስቀራቸው ዐሥር ዕቁባቶች በቀር፥ ንጉሡም እርሱንም ተከትለው መላው ቤተሰቡ ሸሹ፤ ንጉሡም እርሱንም ተከትለው ሕዝቡ ሁሉ ወጣ፤ ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቤት ቆሙ።