የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15:1-17

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15:1-17 መቅካእኤ

ከዚህ በኋላ አቤሴሎም ሠረገላና ፈረሶች፥ ፊት ፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። አቤሴሎምም በማለዳ ተነሥቶ ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በር በሚወስደው መንገድ ዳር ይቆም ነበር። ማናቸውም ባለ ጉዳይ አቤቱታውን ለንጉሡ አቅርቦ ለማስወሰን በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ፥ አቤሴሎም ወደ እርሱ እየጠራ፥ “አንተ ከየትኛው ከተማ ነው የመጣኸው?” በማለት ይጠይቀዋል፤ ያም ሰው፥ “አገልጋይህ ከእስራኤል ነገዶች ከአንዱ ነው” ብሎ ይመልስለታል። ከዚያም አቤሴሎም፥ “ተመልከት! ጉዳይህማ ትክክልና ተገቢም ነው፤ ነገር ግን ከንጉሥ ተወክሎ የሚሰማህ የለም” ይለው ነበር። ከዚህም ሌላ አቤሴሎም፥ “በምድሪቱ ላይ ዳኛ እኔ በሆንኩ ኖሮ! አቤቱታ ወይም ክስ ያለበት ሁሉ ወደ እኔ ሲመጣ፥ ፍትሕ እንዲያገኝ ባደረግሁ ነበር” ይል ነበር። እንዲሁም ማናቸውም ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ እጅ በሚነሣው ጊዜ፥ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ ይይዘውና ይስመው ነበር። አቤሴሎም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጣ እስራኤላዊ ሁሉ አቀራረቡ እንዲህ ነበር፤ ስለዚህ አቤሴሎም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ። ከአራት ዓመት በኋላም አቤሴሎም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “በኬብሮን ለጌታ የተሳልሁትን ስእለት ለማድረስ እንድሄድ ፍቀድልኝ፤ እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በገሹር ሳለሁ ‘ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደሆነ፥ በኬብሮን ለጌታ እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።” ንጉሡም፥ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ተነሥቶም ወደ ኬብሮን ሄደ። ነገር ግን አቤሴሎም፥ በመላው የእስራኤል ነገዶች መሀል “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፥ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ’ ” የሚሉ የምስጢር መልእክተኞችን ላከ። ከአቤሴሎም ጋር ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አብረውት ሄደው ነበር፤ በእንግድነት ተጋብዘው በቅንነት ከመሄዳቸው በስተቀር፥ ስለጉዳዩ ምንም ነገር አያውቁም ነበር። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው ጊሎአዊው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየበዛ ሄደ። መልእክተኛም መጥቶ፥ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል” ብሎ ለዳዊት ነገረው። ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት አገልጋዮቹ ሁሉ፥ “ተነሡ እንሽሽ፤ ያለበለዚያ ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ ፈጥኖ እንዳይዘን፥ ክፉም እንዳያመጣብን፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ስለት እንዳይመታ ፈጥናችሁ እንሂድ” አላቸው። የንጉሡ አገልጋዮቹም፥ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት። ስለዚህ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ ካስቀራቸው ዐሥር ዕቁባቶች በቀር፥ ንጉሡም እርሱንም ተከትለው መላው ቤተሰቡ ሸሹ፤ ንጉሡም እርሱንም ተከትለው ሕዝቡ ሁሉ ወጣ፤ ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቤት ቆሙ።