ከዚህ በኋላ አቤሴሎም አንድ ሠረገላና ፈረሶች ለራሱ አደራጀ፤ እንዲሁም ኀምሳ ጋሻ ጃግሬዎች እንዲኖሩት አደረገ፤ በማለዳ እየተነሣ በመሄድ ወደ ከተማይቱ ቅጽር በር በሚያስገባው መንገድ ዳር ይቆም ነበር፤ ንጉሡ ጉዳዩን እንዲያይለት የሚፈልግ ጠብ ክርክር ያለበት ሰው ሁሉ ወደዚያ ሲመጣ አቤሴሎም ጠርቶ ከወዴት እንደ መጣ ይጠይቀዋል፤ ሰውየው ከየትኛው ነገድ መሆኑን ከነገረው በኋላ፥ አቤሴሎም፥ “ተመልከት፤ ሕግ አንተን ይደግፍሃል፤ ነገር ግን በንጉሡ ተወክሎ ጉዳይህን በትክክል የሚያይልህ የለም” ይለዋል፤ ንግግሩንም በመቀጠል “እኔ ዳኛ ብሆን እንዴት በወደድሁ ነበር! ክርክር ወይም አቤቱታ ያለበት ሰው ወደ እኔ ሲመጣ እኔ ትክክለኛውን ፍርድ እሰጠው ነበር” ይለዋል። ሰውየው በፊቱ ለጥ ብሎ እጅ ለመንሣት በሚቀርብበት ጊዜ አቤሴሎም እጁን ዘርግቶ በማቀፍ ይስመዋል። አቤሴሎም ፍርድ ለማግኘት ወደ ንጉሡ ለሚመጡት ሁሉ እንደዚህ ያደርግ ስለ ነበር የእነርሱን ልብ ለመማረክ ቻለ። ከአራት ዓመት በኋላ አቤሴሎም ንጉሥ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ! ለእግዚአብሔር የተሳልኩትን ስእለት ለመፈጸም ወደ ኬብሮን እንድሄድ ፍቀድልኝ! እኔ አገልጋይህ በሶርያ በምትገኘው በገሹር በኖርኩበት ጊዜ ‘ወደ ኢየሩሳሌም ብትመልሰኝ መሥዋዕት አቀርብልሃለሁ’ ብዬ ለእግዚአብሔር ስእለት ተስዬ ነበር።” ንጉሡም “በሰላም ሂድ!” አለው፤ ስለዚህም አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ፤ “ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገዶች ሁሉ መልእክተኞችን ልኮ የእምቢልታ ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ ድምፃችሁን ከፍ በማድረግ ‘አቤሴሎም የኬብሮን ንጉሥ ሆኗል!’ ብላችሁ ጩኹ” ብለው እንዲነግሩአቸው አደረገ። በአቤሴሎም ጋባዥነት ከእርሱ ጋር ከኢየሩሳሌም የሄዱ ሁለት መቶ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ተከትለውት የሄዱት ስለ ሤራው ምንም ነገር ሳያውቁ በቅንነት ነበር። አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ከንጉሥ ዳዊት አማካሪዎች አንዱ የሆነውን አኪጦፌል ተብሎ የሚጠራውን ሰው መልእክተኛ በመላክ ከጊሎ ከተማ አስጠራ፤ በንጉሡ ላይ የተጠነሰሰው ሤራ እየጠነከረ፥ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቊጥር እየጨመረ ሄደ። አንድ መልእክተኛ ዳዊትን “እስራኤላውያን ታማኝነታቸውን ለአቤሴሎም በመግለጥ ላይ ናቸው” አለው። ስለዚህም ዳዊት ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ለሚገኙት መኳንንቱ ሁሉ “ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ ከፈለግን በፍጥነት ከዚህ ሸሽተን እንውጣ! እንግዲህ ፍጠኑ! አለበለዚያ በፍጥነት መጥቶ ድል ይመታናል፤ በከተማይቱ ያገኘውንም ሁሉ ይገድላል!” አላቸው። እነርሱም “እሺ ንጉሥ ሆይ! አንተ ያልከውን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ነን” ሲሉ መለሱለት። ስለዚህ ንጉሡ ቤተ መንግሥቱን ይጠብቁለት ዘንድ ካስቀራቸው ዐሥር ቊባቶች በቀር ቤተሰቡንና መኳንንቱን ሁሉ በማስከተል ሸሽቶ ሄደ። ንጉሡና ተከታዮቹ ሁሉ ከከተማይቱ ወጥተው በሚሄዱበት ጊዜ በከተማይቱ መጨረሻ ላይ በሚገኘው አንድ ቤት አጠገብ ቆሙ፤
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 15:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos