2 ሳሙኤል 12:1-31
2 ሳሙኤል 12:1-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ላከ፤ ወደ እርሱም መጥቶ አለው፥ “በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ፥ አንዱም ድሃ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ባለጠጋውም እጅግ ብዙ የበግና የላም መንጋ ነበረው። ለድሃው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፤ አሳደጋትም፤ ተንከባከባትም፤ ከእርሱና ከልጆቹ ጋር አደገች፤ ከእንጀራውም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበረ፤ እንደ ልጁም ነበረች። ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፤ የዚያንም የድሃውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ። ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ ተቈጣ፤ ዳዊትም ናታንን፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው ሞት የሚገባው ነው። ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት አድርጎ ይመልስ” አለው። ናታንም ዳዊትን አለው፥ “ይህን ያደረገ ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፤ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፤ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር። አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጤያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፤ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፤ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። ስለዚህም አቃልለኸኛልና፥ የኬጤያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘለዓለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ከቤትህ ክፉ ነገርን አስነሣብሃለሁ፤ ሚስቶችህንም በዐይኖችህ እያየህ እወስዳለሁ፤ ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፤ በዚችም ፀሐይ ፊት ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ።” ዳዊትም ናታንን፥ “እግዚአብሔርን በድያለሁ” አለው። ናታንም ዳዊትን አለው፥ “እግዚአብሔር ደግሞ ኀጢአትህን አርቆልሃል፤ አትሞትምም። ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች መነሣሣት ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል” አለው። ናታንም ወደ ቤቱ ተመለሰ። እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሠፈው፤ እጅግም ታምሞ ነበር። ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአሔርን ለመነ፤ ዳዊትም ጾመ፤ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ። የቤቱም ሽማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እንቢ አለ፤ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም። በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ። የዳዊትም ብላቴኖች፥ “ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፤ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደ ሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን? በራሱ ላይ ክፉ ያደርጋል” ብለው ሕፃኑ እንደ ሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ። ዳዊትም ብላቴኖቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደ ሞተ ዐወቀ፤ ዳዊትም ብላቴኖቹን፥ “ሕፃኑ ሞቶአል?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሞቶአል” አሉት። ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፤ ተቀባም፤ ልብሱንም ለወጠ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ። ወደ ቤቱም መጣ፦ እንጀራም አምጡልኝ አለ፤ በፊቱም እንጀራ አቀረቡለት፤ በላም። ብላቴኖቹም፥ “ይህ ስለ ሕፃኑ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው? እርሱ በሕይወት ሳለ ጾምህና አለቀስህ፤ እንቅልፍም አጣህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ፤ ጠጣህም” አሉት። ዳዊትም፥ “ሕፃኑ ሕያው ሳለ፤ ምናልባት እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁም። አሁን ግን ሞቶአል፤ የምጾመው ስለ ምንድን ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም” አለ። ዳዊትም ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርስዋም ገባ፤ ከእርስዋም ጋር ተኛ፤ ፀነሰችም፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ ስሙንም ሰሎሞን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ወደደው። ደግሞም በነቢዩ በናታን እጅ ልኮ ስሙን ስለ እግዚአብሔር ፍቁረ እግዚአብሔር ብሎ ጠራው። ኢዮአብም የአሞንን ልጆች ከተማ ራባትን ወጋ፤ የመንግሥታቸውንም ከተማ ያዘ። ኢዮአብም ወደ ዳዊት እንዲህ ብሎ መልእክተኞችን ላከ፥ “ራባትን ወግቻለሁ፤ የውኃውንም ከተማ ይዤአለሁ። አሁንም ከተማዪቱን እኔ ቀድሜ እንዳልይዝ፥ በስሜም እንዳትጠራ፥ የቀረውን ሕዝብ ሰብስብ፥ ከተማዪቱንም ከብበህ ቀድመህ ያዛት።” ዳዊትም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ራባት ሄደ፤ ወግቶም ያዛት። የንጉሣቸውንም የሜልኮምን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ። ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበር፤ ክቡር ዕንቍም ነበረበት፤ ዳዊትም በራሱ ላይ አደረገው። ከከተማዪቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። በውስጥዋም የነበሩትን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያ በብረት መጥረቢያም ሥር አኖራቸው፤ በሸክላ ጡብ እቶንም አሳለፋቸው። በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ። ዳዊትም፥ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
2 ሳሙኤል 12:1-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ባለጠጋ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ። ባለ ጠጋው እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤ ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም። ተንከባከባት፤ አብራውም ከልጆቹ ጋር አደገች፤ አብራው ትበላ፤ ከጽዋው ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደ ገዛ ልጁ ነበረች። “ወደ ባለ ጠጋውም ቤት እንግዳ መጣ፤ ባለ ጠጋው ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ ከዚህ ይልቅ የድኻውን እንስት ጠቦት በግ ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።” ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ሕያው እግዚአብሔርን ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለ ማዘኑም ስለ በጊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።” ከዚያም ናታን፣ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤ የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፣ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ አስታቀፍሁህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ፣ ከዚህ በላይ ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር። ታዲያ በፊቱ ክፉ ነገር በማድረግ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ያቃለልኸው ስለ ምንድን ነው? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታህ፤ ሚስት እንድትሆንህም ሚስቱን ወሰድሃት፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው። ስለዚህ ሰይፍ ለዘላለም ከቤትህ አይርቅም፤ እኔን አቃልለኸኛል፤ ሚስት እንድትሆንህም የኬጢያዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደሃታልና።’ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ ከራስህ ቤት ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ዐይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለአንተ ቅርብ ለሆነ ሰው ለአንዱ እሰጣለሁ፤ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህንኑ ነገር በቀን ብርሃን በእስራኤል ሁሉ ፊት እገልጠዋለሁ።’ ” ከዚያም ዳዊት ለናታን፣ “እግዚአብሔርን በጣም በድያለሁ” አለው። ናታንም እንዲህ አለው፣ “እግዚአብሔር ኀጢአትህን አስወግዶልሃል። አንተ አትሞትም፤ ይህን በመፈጸምህ ግን፣ የእግዚአብሔር ጠላቶች እጅግ እንዲያቃልሉት ስላደረግህ፣ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።” ናታን ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ፣ የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ሕፃን እግዚአብሔር ከባድ ሕመም ላይ ጣለው። ዳዊት ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ጾመም፤ ከዚያም ወደ ክፍሉ ገብቶ በተከታታይ ሌሊቱን መሬት ላይ ተኝቶ ዐደረ። የቤተ ሰቡ ሰው፣ ሽማግሌዎችም ከመሬት ሊያስነሡት በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እንቢ አለ፤ አብሯቸውም አንዳች ነገር አልበላም። በሰባተኛው ቀን ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት አገልጋዮችም፣ “እነሆ ሕፃኑ በሕይወት እያለ የነገርነውን ዳዊት አልሰማንም፤ ታዲያ አሁን የሕፃኑን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? በራሱ ላይ ጕዳት ሊያደርስ ይችላል” ብለው መንገሩን ፈሩ። ዳዊት አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ አይቶ፣ ሕፃኑ መሞቱን ዐወቀ፤ ስለዚህ፣ “ሕፃኑ ሞተ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አዎን ሞቷል” ብለው መለሱለት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ከመሬት ተነሣ፤ ከታጠበ፣ ከተቀባና ልብሱን ከለወጠ በኋላ፣ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ሄዶ ሰገደ። ከዚያም ወደ ክፍሉ ገባ፤ በራሱም ጥያቄ ምግብ አቅርበውለት በላ። አገልጋዮቹም፣ “እንደዚህ ያደረግኸው ለምንድን ነው? ሕፃኑ በሕይወት እያለ ጾምህ፤ አለቀስህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ በላህ” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፤ “በርግጥ ሕፃኑ በሕይወት እያለ፣ ‘እግዚአብሔር ይቅር ብሎኝ ሕፃኑን በሕይወት ያኖረው ይሆናል’ ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁ። አሁን ግን ሕፃኑ ስለ ሞተ፣ የምጾመው ለምንድን ነው? መልሼ ላመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ፣ እርሱ ወደ እኔ አይመለስ!” ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርሷም ገብቶ አብሯት ተኛ፤ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሰሎሞን አለው። እግዚአብሔርም ወደደው፤ እግዚአብሔር ሕፃኑን ስለ ወደደም ስሙ ይዲድያ ተብሎ እንዲጠራ በነቢዩ በናታን በኩል ቃል ላከ። በዚያን ጊዜም ኢዮአብ የአሞናውያንን ከተማ ረባትን ወግቶ የቤተ መንግሥቱን ምሽግ ያዘ። ከዚያም ኢዮአብ እንዲህ በማለት ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ “ረባትን ወግቼ የውሃውን ከተማ ይዤአለሁ፤ እንግዲህ የቀረውን ሰራዊት አሰባስበህ ከተማዪቱን ክበብና ያዛት፤ አለዚያ እኔ ከተማዪቱን እይዛትና በስሜ መጠራቷ ነው።” ስለዚህ ዳዊት መላውን ሰራዊት አሰባስቦ ወደ ረባት በመሄድ ወግቶ ያዛት። የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ የዘውዱ ክብደት አንድ መክሊት ወርቅ የሚመዝን ሲሆን፣ በከበረ ዕንቍም ያጌጠ ነበር፤ ይህም በዳዊት ራስ ላይ ተጫነ። ዳዊትም ከከተማዪቱ እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤ እዚያ የነበሩትንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፣ የብረት መቈፈሪያና መጥረቢያ ተጠቅመው ሥራ እንዲሠሩ አደረጋቸው፣ እንዲሁም የሸክላ ጡብ አሠራቸው። እንዲህ ያለውም ሥራ በሌሎቹ የአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲፈጸም አደረገ። ከዚያም ዳዊትና ሰራዊቱ በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
2 ሳሙኤል 12:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ናታንን ወደ ዳዊት ላከ፥ ወደ እርሱም መጥቶ አለው፦ በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ አንዱም ድሀ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ባለጠጋውም እጅግ ብዙ በግና ላም ነበረው። ለድሀው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፥ አሳደጋትም፥ ከልጆቹም ጋር በእርሱ ዘንድ አደገች፥ እንጀራውንም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበር፥ እንደ ልጁም ነበረች። ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፥ የዚያንም የድሀውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ። ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው የሞት ልጅ ነው። ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት ይመልስ አለው። ናታንም ዳዊትን አለው፦ ያ ሰው አንተ ነህ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፥ የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፥ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር። አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፥ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፥ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። ስለዚህም አቃልለኽኛልና፥ የኬጢያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ከቤትህ ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፥ ሚስቶችህንም በዓይንህ ፊት እወስዳለሁ፥ ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፥ በዚህችም ፀሐይ ዓይን ፊት ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፥ እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ። ዳዊትም ናታንን፦ እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው። ናታንም ዳዊትን፦ እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፥ አትሞትም። ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች ታላቅ የስድብ ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል አለው። ናታንም ወደ ቤቱ ተመለሰ። እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሠፈ፥ እጅግም ታምሞ ነበር። ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፥ ዳዊትም ጾመ፥ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ። የቤቱም ሽማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፥ እርሱ ግን እንቢ አለ፥ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም። በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ። የዳዊትም ባሪያዎች፦ ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፥ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደ ሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን? በነፍሱ ክፉ ያደርጋል ብለው ሕፃኑ እንደ ሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ። ዳዊትም ባሪያዎቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደ ሞተ አወቀ፥ ዳዊትም ባሪያዎቹን፦ ሕፃኑ ሞቶአል? አላቸው። እነርሱም፦ ሞቶአል አሉት። ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፥ ተቀባም፥ ልብሱንም ለወጠ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ። ወደ ቤቱም መጣ፦ እንጀራ አምጡልኝ አለ፥ በፊቱም አቀረቡለት፥ በላም። ባሪያዎቹም፦ ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድር ነው? በሕይወት ሳለ ስለ ሕፃኑ ጾምህና አለቀስህ፥ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ አሉት። እርሱም፦ ሕፃኑ ሕያው ሳለ፦ እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ አለቀስሁም። አሁን ግን ሞቶአል፥ የምጾመው ስለ ምንድር ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም አለ። ዳዊትም ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፥ ወደ እርስዋም ገባ፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ፥ ወንድ ልጅም ወለደች፥ ስሙንም ሰሎሞን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ወደደው፥ ደግሞም በነቢዩ በናታን እጅ ልኮ ስሙን ስለ እግዚአብሔር ይዲድያ ብሎ ጠራው። ኢዮአብም የአሞንን ልጆች ከተማ ረባትን ወጋ፥ የውኃውንም ከተማ ያዘ። ኢዪአብም ወደ ዳዊት፦ ረባትን ወግቻለሁ፥ የውኃውንም ከተማ ይዤአለሁ። አሁንም ከተማይቱን እንዳልይዝ፥ በስሜም እንዳትጠራ፥ የቀረውን ሕዝብ ሰብስብ፥ ከተማይቱንም ከብበህ ያዝ ብሎ መልእክተኞችን ላከ። ዳዊትም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ረባት ሄደ፥ ወግቶም ያዛት። የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ። ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበር፥ ክቡር ዕንቁም ነበረበት፥ ዳዊትም በራሱ ላይ አደረገው። ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። በውስጥዋም የነበሩትን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቆፈሪያና በብረት መጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፥ የሸክላ ጡብም እንዲያቃጥሉ አደረጋቸው፥ በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲህ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
2 ሳሙኤል 12:1-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ነቢዩን ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ ናታንም ወደ ዳዊት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱ አንዱ ሀብታም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ድኻ ነበር፤ ሀብታሙ ሰው ብዙ የቀንድ ከብቶችና የበግ መንጋ ነበሩት፤ ድኻው ግን በገንዘቡ የገዛት አንዲት የበግ ግልገል ብቻ ነበረችው፤ እርስዋን እየተንከባከበ ከልጆቹ ጋር በቤቱ ውስጥ ያሳድጋት ነበር፤ ከሚመገበው ይመግባት፥ ከሚጠጣውም ያጠጣት ነበር፤ ስትተኛም ያቅፋት ነበር፤ ያቺም ግልገል ልክ እንደ ልጁ ነበረች፤ አንድ ቀን ወደ ሀብታሙ ሰው ቤት አንድ መንገደኛ መጣ፤ ሀብታሙ ሰው ለእንግዳው የሚሆን ምግብ ለማዘጋጀት ከእንሰሶቹ አንዱን ማረድ አልፈለገም፤ ይህንንም በማድረግ ፈንታ የድኻውን ሰው ግልገል ወስዶ በማረድ ለእንግዳው ምግብ አዘጋጀ።” ዳዊት በሀብታሙ ሰው ታሪክ እጅግ ተቈጥቶ “ይህን ያደረገው ሰው ሞት እንደሚገባው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! ይህን የመሰለ የጭካኔ ሥራ በመፈጸሙ ከዚያ ሰው የወሰደበትን አራት እጥፍ አድርጎ መመለስ አለበት” አለ። ናታንም ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ራስህ ነህ! የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እኔ ንጉሥ አደረግኹህ፤ ከሳኦልም እጅ በመታደግ አዳንኩህ፤ መንግሥቱንና ሚስቶቹን ሰጠሁህ፤ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ አነገሥኩህ፤ ይህም ሁሉ እንኳ የማይበቃህ ቢሆን ኖሮ በተጨማሪ እጥፍ አድርጌ በሰጠሁህ ነበር፤ ታዲያ ትእዛዜን የናቅኸው ስለምንድን ነው? ይህንንስ ክፉ ነገር ለምን አደረግህ? ኦርዮን በጦር ሜዳ አስገደልከው፤ ንጹሑን ሰው ዐሞናውያን እንዲገድሉት አደረግህ፤ ሚስቱንም ወሰድክ! አንተ ለእኔ ስላልታዘዝክ የኦርዮን ሚስት ስለ ወሰድክ፥ እነሆ ከቤትህ በሰይፍ የሚገደል አይጠፋም፤ ከቤተሰብህ አንዱ ተነሥቶ ችግር እንዲያደርስብህ የማደርግ መሆኔን በመሐላ አረጋግጥልሃለሁ፤ ሚስቶችህን ወስጄ ለሌላ ሰው በምሰጥበት ጊዜ ይህ ነገር እንደሚፈጸም ትገነዘባለህ፤ እርሱም ከሚስቶችህ ጋር በቀን ብርሃን ይገናኛል። አንተ ይህን ኃጢአት በስውር ሠርተሃል፤ እኔ ግን እስራኤል ሁሉ ይመለከቱ ዘንድ ይህን ነገር የቀን ብርሃን ባለበት በግልጥ አደርጋለሁ።’ ” ዳዊትም “ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዝኛለሁ” አለ። ናታንም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እግዚአብሔር ይቅር ስላለህ አትሞትም፤ ነገር ግን ይህን በደል በመፈጸም እግዚአብሔርን ስለ ናቅህ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።” ከዚህ በኋላ ናታን ወደ ቤቱ ሄደ። የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ልጅ እግዚአብሔር በከባድ ሕመም ቀሠፈው፤ ዳዊትም ሕፃኑን እንዲፈውስለት በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን ለመነ፤ በየሌሊቱም ወደ መኝታ ክፍሉ እየገባ በመሬት ላይ ይተኛ ነበር፤ የቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች ወደ እርሱ ቀርበው ከመሬት ላይ ሊያስነሡት ሞከሩ፤ እርሱ ግን ከመሬት ላለመነሣትና ከእነርሱም ጋር ምንም ነገር ላለመቅመስ ወሰነ፤ ከአንድ ሳምንትም በኋላ ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት ባለሟሎችም መርዶውን ለመንገር ፈርተው “ሕፃኑ በሕይወት በነበረበት ጊዜ እንኳ ዳዊት ስንመክረው አልሰማንም፤ ታዲያ፥ አሁን የልጁን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? ምናልባት በራሱ ላይ አንዳች ጒዳት ማድረስ ይችል ይሆናል!” አሉ። ዳዊት እርስ በርሳቸው ሲያንሾካሹኩ በሰማ ጊዜ ሕፃኑ መሞቱን ተረዳ፤ ስለዚህም “ሕፃኑ ሞተ እንዴ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አዎ ሞቶአል” ሲሉ መለሱለት። ዳዊትም ከተኛበት መሬት ተነሥቶ ሰውነቱን ታጠበ፤ ቅባት ተቀባ፤ ልብሱንም ለወጠ፤ ከዚያም ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄዶ ሰገደ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም ሲመለስ ምግብ እንዲያቀርቡለት ጠየቀ፤ እንደ ቀረበለትም ወዲያውኑ ተመገበ፤ ባለሟሎቹም “ይህ ነገር ምን እንደ ሆነ ለማወቅ አልቻልንም፤ ሕፃኑ በሕይወት በነበረበት ጊዜ በመጾም አለቀስክለት፤ እርሱ ከሞተ በኋላ ግን ወዲያውኑ ተነሥተህ ተመገብክ!” አሉት። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሕፃኑ በሕይወት ሳለ መጾሜና ማልቀሴ እርግጥ ነው፤ እግዚአብሔር ምሕረት አድርጎልኝ ሕፃኑ እንዳይሞት ያደርግ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር፤ አሁን ግን ከሞተ በኋላ ስለምን እጾማለሁ? ሕፃኑን እንደገና በሕይወት እንዲኖር ማድረግ ይቻለኛልን? እኔ አንድ ቀን ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ ተመልሶ አይመጣም።” ከዚህ በኋላ ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ከእርስዋም ጋር ግንኙነት አደረገ፤ እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ዳዊትም የልጁን ስም “ሰሎሞን” ብሎ ጠራው፤ እግዚአብሔር ሕፃኑን ስለ ወደደው፥ “ይዲድያ” የሚል ስም እንዲያወጣለት ነቢዩ ናታንን አዘዘው፤ ይህም “በእግዚአብሔር የተወደደ” ማለት ነው። በዚያን ጊዜ ኢዮአብ ራባ ተብላ የምትጠራውን የዐሞናውያንን ከተማ ለመያዝ የሚያደርገውን ዘመቻ በመቀጠል የከተማ ውሃ የሚገኝበትን ምሽግ ያዘ። መልእክተኞችንም ልኮ ለዳዊት እንዲህ ብለው እንዲነግሩት አደረገ፤ “በራባ ላይ አደጋ ጥዬ የውሃ ማመንጫውን ምሽግ ይዤአለሁ፤ እነሆ አሁን ከሠራዊትህ ቀሪውን ክፍል አሰባስብና በከተማይቱ ላይ አደጋ በመጣል አንተው ራስህ ያዛት፤ አለበለዚያ እኔ ከተማይቱን ይዤ በስሜ እንድትጠራ አደርጋለሁ።” ስለዚህም ዳዊት ሠራዊቱን ሁሉ አሰባስቦ ወደ ራባ በመዝመት አደጋ ጥሎ ያዛት፤ ዳዊት የዐሞናውያን አምላክ ከሆነው ሚልኮም ተብሎ ከሚጠራው ጣዖት ራስ ላይ ሠላሳ አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝነውንና በውስጡም የከበረ ዕንቊ ያለበትን ዘውድ ወስዶ በራሱ ላይ ደፋው፤ እንዲሁም ከከተማይቱ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤ ሰዎቹም በመጋዝ፥ በብረት ዶማና በብረት መጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ ጡብ እንዲሠሩለትም አስገደዳቸው፤ በሌሎቹ የዐሞን ከተሞች ሁሉ ያሉትን ሰዎችም እንዲሁ በዚሁ ዐይነት እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ ከዚህ በኋላ እርሱና ሠራዊቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
2 ሳሙኤል 12:1-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ሀብታም ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ። ሀብታሙ እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤ ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም። እየተንከባከበ አብራውም ከልጆቹ ጋር አደገች፤ አብራው ትበላ፤ ከጽዋውም ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደገዛ ልጁ ነበረች። ወደ ሀብታሙም ቤት እንግዳ መጣ፤ ሀብታሙ ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ የድኻውን ግልገል ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።” ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ጌታ ምስክሬ ነው! ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለማዘኑም ስለ ግልገሊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።” ከዚያም ናታን፥ ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ የሚለው ይህን ነው፤ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤ የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በእቅፍህ አኖርኩ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤትም ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ፤ ከዚህ በላይ ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር። ታዲያ በፊቱ ክፉ ነገር በማድረግ፥ የጌታን ቃል ያቃለልኸው ስለምንድን ነው? ሒታዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታህ፤ ሚስት እንድትሆንህም ሚስቱን ወሰድሃት፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው። ስለዚህ እኔን አቃለኸኛል፤ ሚስት እንድትሆንህም የሒታዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደሃታልና፥ ሰይፍ ለዘለዓለም ከቤትህ አይርቅም።’ ” ጌታ እንዲህ ይላል፤ “እነሆ ከራስህ ቤት ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ዐይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለአንተ ቅርብ ለሆነ ሰው ለአንዱ እሰጣለሁ፤ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህንኑ ነገር በቀን ብርሃን በእስራኤል ሁሉ ፊት እገልጠዋለሁ።” ከዚያም ዳዊት ለናታን፥ “ጌታን በድያለሁ” አለው። ናታንም እንዲህ አለው፥ “ጌታ ኃጢአትህን አስወግዶልሃል። አንተ አትሞትም፤ ይህን በመፈጸምህ ግን፥ የጌታ ጠላቶች እጅግ እንዲያቃልሉት ስላደረግህ፥ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።” ናታን ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ፥ የኦርዮን ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ሕፃን ጌታ ከባድ ሕመም ላይ ጣለው። ዳዊት ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ጾመም፤ ወደ ክፍሉ ገብቶም ሌሊቱን መሬት ላይ ተኝቶ ዐደረ። የቤተሰቡ ሽማግሌዎችም ከመሬት ሊያሰነሡት በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እምቢ አለ፤ አብሮአቸውም አንዳች ምግብ አልበላም። በሰባተኛው ቀን ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት አገልጋዮችም፥ “እነሆ ሕፃኑ በሕይወት እያለ የነገርነውን ዳዊት አልሰማንም ታዲያ አሁን የሕፃኑን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? በራሱ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል” ብለው መንገሩን ፈሩ። ዳዊት አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ አይቶ፥ ሕፃኑ መሞቱን ዐወቀ፤ ስለዚህ፥ “ሕፃኑ ሞተ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፥ “አዎን ሞቷል” ብለው መለሱለት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ከመሬት ተነሣ፤ ከታጠበ፥ ከተቀባና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ወደ ጌታ ቤት ሄዶ ሰገደ። ከዚያም ወደ ክፍሉ ገባ፤ በራሱም ጥያቄ ምግብ አቅርበውለት በላ። አገልጋዮቹም፥ “እንደዚህ ያደረግኸው ለምንድን ነው? ሕፃኑ በሕይወት እያለ ጾምህ፤ አለቀስህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ በላህ” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፤ “በእርግጥ ሕፃኑ በሕይወት እያለ፥ ‘ጌታ ይቅር ብሎኝ ሕፃኑን በሕይወት ያኖረው ይሆናል’ ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁ። አሁን ግን ሕፃኑ ስለ ሞተ፥ የምጾመው ለምንድን ነው? መልሼ ላመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ፥ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም” አለ። ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርሷም ገብቶ አብሮአት ተኛ፤ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሰሎሞን አለው። ጌታም ወደደው፤ ጌታ ሕፃኑን ስለ ወደደም ስሙ ይዲድያ ተብሎ እንዲጠራ በነቢዩ በናታን በኩል ቃል ላከ። በዚያን ጊዜም ኢዮአብ የአሞናውያንን ከተማ ራባትን ወግቶ የቤተ መንግሥቱን ምሽግ ያዘ። ከዚያም ኢዮአብ እንዲህ በማለት ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ “ራባን ወግቼ የውሃውንም ከተማ ይዤአለሁ፤ እንግዲህ የቀረውን ሠራዊት አሰባስበህ ከተማዪቱን ክበብና ያዛት፤ ያለበለዚያ እኔ ከተማዪቱን እይዛትና በስሜ መጠራቷ ነው።” ስለዚህ ዳዊት መላውን ሠራዊት አሰባስቦ ወደ ራባ በመሄድ ወግቶ ያዛት። የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ የዘውዱ ክብደት የሚመዝነው አንድ መክሊት ወርቅ ሲሆን፥ በከበረ ዕንቁም ያጌጠ ነበር፤ ይህም በዳዊት ራስ ላይ ተጫነ። ዳዊትም ከከተማዪቱ እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤ እዚያ የነበሩትንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፥ የብረት መቆፈሪያና መጥረቢያ ተጠቅመው ሥራ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ እንዲሁም የሸክላ ጡብ አሠራቸው። እንዲህ ያለውም ሥራ በአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲፈጸም አደረገ። ከዚያም ዳዊትና ሠራዊቱ በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።