መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 12
12
እግዚአብሔር በነቢዩ በናታን ዳዊትን እንደ ገሠጸው
1እግዚአብሔርም ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ላከ፤ ወደ እርሱም መጥቶ አለው፥ “በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ፥ አንዱም ድሃ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። 2ባለጠጋውም እጅግ ብዙ የበግና የላም መንጋ ነበረው። 3ለድሃው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፤ አሳደጋትም፤ ተንከባከባትም፤ ከእርሱና ከልጆቹ ጋር አደገች፤ ከእንጀራውም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበረ፤ እንደ ልጁም ነበረች። 4ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፤ የዚያንም የድሃውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ። 5ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ ተቈጣ፤ ዳዊትም ናታንን፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው ሞት የሚገባው ነው። 6ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሰባት” ይላል። አድርጎ ይመልስ” አለው።
7ናታንም ዳዊትን አለው፥ “ይህን ያደረገ ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፤ 8የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፤ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር። 9አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጤያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፤ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፤ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። 10ስለዚህም አቃልለኸኛልና፥ የኬጤያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘለዓለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም። 11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ከቤትህ ክፉ ነገርን አስነሣብሃለሁ፤ ሚስቶችህንም በዐይኖችህ እያየህ እወስዳለሁ፤ ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፤ በዚችም ፀሐይ ፊት ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። 12አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ።” 13ዳዊትም ናታንን፥ “እግዚአብሔርን በድያለሁ” አለው። ናታንም ዳዊትን አለው፥ “እግዚአብሔር ደግሞ ኀጢአትህን አርቆልሃል፤ አትሞትምም። 14ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች መነሣሣት ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል” አለው። 15ናታንም ወደ ቤቱ ተመለሰ።
እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሠፈው፤ እጅግም ታምሞ ነበር። 16ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአሔርን ለመነ፤ ዳዊትም ጾመ፤ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ። 17የቤቱም ሽማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እንቢ አለ፤ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም። 18በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ። የዳዊትም ብላቴኖች፥ “ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፤ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደ ሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን? በራሱ ላይ ክፉ ያደርጋል” ብለው ሕፃኑ እንደ ሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ። 19ዳዊትም ብላቴኖቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደ ሞተ ዐወቀ፤ ዳዊትም ብላቴኖቹን፥ “ሕፃኑ ሞቶአል?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሞቶአል” አሉት። 20ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፤ ተቀባም፤ ልብሱንም ለወጠ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ። ወደ ቤቱም መጣ፦ እንጀራም አምጡልኝ አለ፤ በፊቱም እንጀራ አቀረቡለት፤ በላም። 21ብላቴኖቹም፥ “ይህ ስለ ሕፃኑ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው? እርሱ በሕይወት ሳለ ጾምህና አለቀስህ፤ እንቅልፍም አጣህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ፤ ጠጣህም” አሉት። 22ዳዊትም፥ “ሕፃኑ ሕያው ሳለ፤ ምናልባት እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁም። 23አሁን ግን ሞቶአል፤ የምጾመው ስለ ምንድን ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም” አለ።
24ዳዊትም ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርስዋም ገባ፤ ከእርስዋም ጋር ተኛ፤ ፀነሰችም፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ ስሙንም ሰሎሞን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ወደደው። 25ደግሞም በነቢዩ በናታን እጅ ልኮ ስሙን ስለ እግዚአብሔር ፍቁረ እግዚአብሔር#ዕብ. “ያዴዲያ” ይላል። ብሎ ጠራው።
ዳዊት አሞናውያንን ድል እንደ አደረገ
(1ዜ.መ. 20፥1-3)
26ኢዮአብም የአሞንን ልጆች ከተማ ራባትን ወጋ፤ የመንግሥታቸውንም ከተማ ያዘ። 27ኢዮአብም ወደ ዳዊት እንዲህ ብሎ መልእክተኞችን ላከ፥ “ራባትን ወግቻለሁ፤ የውኃውንም ከተማ ይዤአለሁ። 28አሁንም ከተማዪቱን እኔ ቀድሜ እንዳልይዝ፥ በስሜም እንዳትጠራ፥ የቀረውን ሕዝብ ሰብስብ፥ ከተማዪቱንም ከብበህ ቀድመህ ያዛት።” 29ዳዊትም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ራባት ሄደ፤ ወግቶም ያዛት። 30የንጉሣቸውንም የሜልኮምን ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ። ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበር፤ ክቡር ዕንቍም ነበረበት፤ ዳዊትም በራሱ ላይ አደረገው። ከከተማዪቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። 31በውስጥዋም የነበሩትን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያ በብረት መጥረቢያም ሥር አኖራቸው፤ በሸክላ ጡብ እቶንም አሳለፋቸው።#ዕብ. “በመጋዝና በብረት መቈፈሪያ፥ በመጥረቢያም እንዲሠሩ አደረጋቸው” ይላል። በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ። ዳዊትም፥ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 12: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ