የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ጴጥሮስ 2:10-22

2 ጴጥሮስ 2:9-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል። ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፤ ዳሩ ግን መላእክት በኀይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ፥ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደ ሌላቸው እንስሶች ሆነው፥ በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፤ የዐመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤ ምንዝር የሞላባቸው ኀጢአትንም የማይተዉ ዐይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው። ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ እርሱ የዐመፃን ደመወዝ ወደደ፤ ነገር ግን ስለ መተላለፉ ተዘለፈ፤ ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ። ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው እነዚህ ውሃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው። ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፤ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ። ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው “አርነት ትወጣላችሁ፤” እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና። በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። ዕውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤” ደግሞ “የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች፤” እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።

2 ጴጥሮስ 2:10-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በተለይም በርኩስ ምኞት የሥጋ ፍላጎታቸውን የሚከተሉትንና ሥልጣንን የሚንቁትን ለፍርድ ጠብቆ ያቈያቸዋል። እነዚህ ሰዎች ደፋሮችና እብሪተኞች ስለሆኑ ሰማያውያንን ፍጡራን ሲሳደቡ አይፈሩም፤ ነገር ግን መላእክት ከእነርሱ ይልቅ ብርቱና ኀያል ሆነው ሳሉ፣ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብ ቃል አይሰነዝሩም። እነዚህ ሰዎች ግን ምንም በማያውቁት ነገር እየገቡ ይሳደባሉ፤ እነርሱም ለመያዝና ለመገደል እንደ ተወለዱ፣ በስሜታቸው ብቻ እንደሚመሩና ልቦናም እንደሌላቸው አራዊት ናቸው፤ የሚጠፉትም እንደ እንስሳት ነው። ለዐመፃቸው የሚገባውን የዐመፅ ዋጋ ይቀበላሉ። በጠራራ ፀሓይ ሲፈነጥዙ እንደ ደስታ ይቈጥሩታል፤ በግብዣ ላይ ሳሉ ነውረኞችና ርኩሶች ሆነው ከእናንተም ጋር በፍቅር ግብዣ ላይ ይቀመጣሉ። ዐይናቸው ቅንዝር የተሞላ በመሆኑ ኀጢአትን ከመሥራት አይቈጠቡም፤ ጽኑ ያልሆኑትን ነፍሳት ያስታሉ፤ ሥሥትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው! ቀናውን መንገድ ትተው፣ የዐመፅን ደመወዝ የወደደውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለው ስተዋል፤ እርሱ ግን ስለ መተላለፉ ተገሥጿል፤ መናገር የማይችል አህያ በሰው ቋንቋ ተናግሮ የነቢዩን እብደት ገታ። እነዚህ ሰዎች የደረቁ ምንጮችና በዐውሎ ነፋስ የሚነዱ ደመናዎች ናቸው፤ የሚጠብቃቸውም ድቅድቅ ጨለማ ነው፤ ከንቱ ቃል እየደረደሩ በስሕተት ከሚኖሩት መካከል አምልጠው የመጡትን ሰዎች በሴሰኛ ሥጋዊ ምኞት በማባበል ያታልላሉና። እነርሱ ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው ሳሉ፣ ሌሎችን ነጻ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤ ሰው ለተገዛለት ለዚያ ነገር ባሪያ ነውና። ጌታችንንና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ እንደ ገና ተጠላልፈው ቢሸነፉ፣ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ ይሆንባቸዋል። የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ፣ ቀድሞውኑ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት ይሻላቸው ነበር። “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል” እንዲሁም “ዐሣማ ቢታጠብም ተመልሶ በጭቃ ላይ ይንከባለላል” የሚለው ምሳሌ እውን ይሆንባቸዋል።

2 ጴጥሮስ 2:9-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል። ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፤ ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደ ሌላቸው እንስሶች ሆነው፥ በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፤ የዓመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤ ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው። ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ እርሱ የዓመፃን ደመወዝ ወደደ፥ ነገር ግን ስለ መተላለፉ ተዘለፈ፤ ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ። ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው እነዚህ ውኃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው። ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፥ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ። ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው፦ አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና። በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ፦ የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።

2 ጴጥሮስ 2:10-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በተለይም እነዚያን ርኩስ የሆነውን የሥጋ ፍትወታቸውን የሚከተሉትንና የእግዚአብሔርን ሥልጣን የሚንቁትን ለፍርድ ጠብቆ ያቈያቸዋል። እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን ደፋሮችና ትዕቢተኞች ስለ ሆኑ የሰማይ ሥልጣናትን ሲሳደቡ አይፈሩም። መላእክት ከእነርሱ በኀይልና በሥልጣን የሚበልጡ ቢሆኑም እንኳ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ ዘለፋን የተመላ ክስ አያቀርቡባቸውም። እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን ግን ለማስተዋል ያቃታቸውን ነገር ይሳደባሉ፤ እነርሱ ለመጠመድና ለመገደል እንደ ተወለዱ፥ በተፈጥሮ ስሜት እንደሚኖሩና አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች ናቸው፤ እንስሶች እንደሚጠፉ እነርሱም ፈጽመው ይጠፋሉ። በደል ስለ ፈጸሙ ዋጋቸውን ይቀበላሉ፤ የእነርሱ ደስታ በጠራራ ፀሐይ መስከርና ያለ ቅጥ መፈንጠዝ ነው፤ በዚህ ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያቸው ከእናንተ ጋር በሚጋበዙበት ጊዜ አታላይ በሆነው ሥጋዊ ድርጊታቸው ነውረኞችና አሳፋሪዎች ናቸው። ኃጢአት ከማድረግ የማይቈጠብ ቅንዝረኛ ዐይን አላቸው፤ የኃጢአት መሥራት ፍላጎታቸው መቼም አይረካም፤ በእምነት ጸንተው ያልቆሙትን ሰዎች ያታልላሉ፤ ለገንዘብ ይስገበገባሉ። የተረገሙ ሰዎች ናቸው። እነርሱ የቀናውን መንገድ ትተው ጠፍተዋል፤ ክፉ በመሥራት የሚገኘውን ገንዘብ የወደደውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለው ተሳስተዋል። በለዓም ግን ስለ ኃጢአቱ ተገሥጾአል፤ መናገር የማትችል አህያ በሰው ቃል ተናግራ የነቢዩን የእብደት ሥራ ተቃውማለች። እነዚህ ሰዎች ውሃ እንደሌለባቸው ምንጮች ናቸው፤ በዐውሎ ነፋስ እንደሚወሰዱ ደመናዎች ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማም ይጠብቃቸዋል። በስሕተት ከሚኖሩት ሰዎች መካከል አምልጠው ከመጡ ገና ብዙ ያልቈዩትን ሰዎች ከንቱ የሆነ የዕብሪት ቃል በመናገር፥ በሥጋዊ ፍትወትና በሴሰኛነት በማባበል ያታልሉአቸዋል። “ነጻ ትወጣላችሁ” እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል። ሰው ሲሸነፍ ላሸናፊው ባሪያ ሆኖ ስለሚገዛ እነርሱም ራሳቸው የኃጢአት ባሪያዎች ናቸው። ጌታችንንና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኲሰት ካመለጡ በኋላ ተመልሰው በዚያው ርኲሰት ተይዘው ቢሸነፉ ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የባሰ ይሆንባቸዋል፤ የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ ይልቅ የጽድቅን መንገድ ሳያውቁ ቀርተው ቢሆን ኖሮ በተሻላቸው ነበር። “የተፋውን ለመዋጥ ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል።” እንዲሁም “ዐሣማ ከታጠበ በኋላ ተመልሶ በጭቃ ላይ ይንከባለላል” የሚለው እውነተኛ ምሳሌ ደርሶባቸዋል።

2 ጴጥሮስ 2:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ይልቁንም በርኩስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን፥ ጌትነትንም የሚንቁትን፤ ደፋሮችና እምቢተኞች ስለ ሆኑ ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይፈሩም፤ ዳሩ ግን መላእክት፥ በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ምንም ያህል ቢልቁ፥ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። ይሁን እንጂ፥ እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት እንደ ተወለዱ፥ በፍጥረታዊ ስሜታቸው እንደሚኖሩ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች ናቸው። የማያውቁትን ነገር እየተሳደቡ፥ ከእነርሱም ጋር አብረው ይጠፋሉ፤ የበደላቸውን ዋጋም ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኩሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤ ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዐይኖች አላቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው። እነርሱ የቀናውን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ ክፉ በመሥራት የሚገኘውን ገንዘብ የወደደውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ ነገር ግን በለዓም ስለ መተላለፉ ተገሥጿአል፤ መናገር የማይችለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብደት አገደ። እነዚህ ሰዎች ውሃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማ ለዘለዓለም ይጠብቃቸዋል። ከንቱና የትዕቢት ቃል ይናገራሉና፤ በስሕተትም ከሚኖሩት ለጥቂት ያመለጡትን ሰዎች በሥጋ ሴሰኛ ምኞት በማታለል ያስታሉ። ራሳቸው የጥፋት ባርያዎች ሆነው “ነጻ ትወጣላችሁ፤” እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ የተገዛ ባርያ ነውና። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ፥ ዳግመኛ በእርሷ ተጠልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሯቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ይሆንባቸዋል። የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ ይልቅ የጽድቅን መንገድ ሳያውቁ ቀርተው ቢሆን ኖሮ በተሻላቸው ነበር። “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤” እንዲሁም “እርያ ብትታጠብ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች፤” የሚለው እውነተኛ ምሳሌ ደርሶባቸዋል።