ይልቁንም በርኩስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን፥ ጌትነትንም የሚንቁትን፤ ደፋሮችና እምቢተኞች ስለ ሆኑ ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይፈሩም፤ ዳሩ ግን መላእክት፥ በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ምንም ያህል ቢልቁ፥ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። ይሁን እንጂ፥ እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት እንደ ተወለዱ፥ በፍጥረታዊ ስሜታቸው እንደሚኖሩ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች ናቸው። የማያውቁትን ነገር እየተሳደቡ፥ ከእነርሱም ጋር አብረው ይጠፋሉ፤ የበደላቸውን ዋጋም ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኩሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤ ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዐይኖች አላቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው። እነርሱ የቀናውን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ ክፉ በመሥራት የሚገኘውን ገንዘብ የወደደውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ ነገር ግን በለዓም ስለ መተላለፉ ተገሥጿአል፤ መናገር የማይችለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብደት አገደ። እነዚህ ሰዎች ውሃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማ ለዘለዓለም ይጠብቃቸዋል። ከንቱና የትዕቢት ቃል ይናገራሉና፤ በስሕተትም ከሚኖሩት ለጥቂት ያመለጡትን ሰዎች በሥጋ ሴሰኛ ምኞት በማታለል ያስታሉ። ራሳቸው የጥፋት ባርያዎች ሆነው “ነጻ ትወጣላችሁ፤” እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ የተገዛ ባርያ ነውና። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ፥ ዳግመኛ በእርሷ ተጠልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሯቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ይሆንባቸዋል። የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ ይልቅ የጽድቅን መንገድ ሳያውቁ ቀርተው ቢሆን ኖሮ በተሻላቸው ነበር። “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤” እንዲሁም “እርያ ብትታጠብ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች፤” የሚለው እውነተኛ ምሳሌ ደርሶባቸዋል።
2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2 ያንብቡ
ያዳምጡ 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2:10-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos