በተለይም እነዚያን ርኩስ የሆነውን የሥጋ ፍትወታቸውን የሚከተሉትንና የእግዚአብሔርን ሥልጣን የሚንቁትን ለፍርድ ጠብቆ ያቈያቸዋል። እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን ደፋሮችና ትዕቢተኞች ስለ ሆኑ የሰማይ ሥልጣናትን ሲሳደቡ አይፈሩም። መላእክት ከእነርሱ በኀይልና በሥልጣን የሚበልጡ ቢሆኑም እንኳ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ ዘለፋን የተመላ ክስ አያቀርቡባቸውም። እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን ግን ለማስተዋል ያቃታቸውን ነገር ይሳደባሉ፤ እነርሱ ለመጠመድና ለመገደል እንደ ተወለዱ፥ በተፈጥሮ ስሜት እንደሚኖሩና አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች ናቸው፤ እንስሶች እንደሚጠፉ እነርሱም ፈጽመው ይጠፋሉ። በደል ስለ ፈጸሙ ዋጋቸውን ይቀበላሉ፤ የእነርሱ ደስታ በጠራራ ፀሐይ መስከርና ያለ ቅጥ መፈንጠዝ ነው፤ በዚህ ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያቸው ከእናንተ ጋር በሚጋበዙበት ጊዜ አታላይ በሆነው ሥጋዊ ድርጊታቸው ነውረኞችና አሳፋሪዎች ናቸው። ኃጢአት ከማድረግ የማይቈጠብ ቅንዝረኛ ዐይን አላቸው፤ የኃጢአት መሥራት ፍላጎታቸው መቼም አይረካም፤ በእምነት ጸንተው ያልቆሙትን ሰዎች ያታልላሉ፤ ለገንዘብ ይስገበገባሉ። የተረገሙ ሰዎች ናቸው። እነርሱ የቀናውን መንገድ ትተው ጠፍተዋል፤ ክፉ በመሥራት የሚገኘውን ገንዘብ የወደደውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለው ተሳስተዋል። በለዓም ግን ስለ ኃጢአቱ ተገሥጾአል፤ መናገር የማትችል አህያ በሰው ቃል ተናግራ የነቢዩን የእብደት ሥራ ተቃውማለች። እነዚህ ሰዎች ውሃ እንደሌለባቸው ምንጮች ናቸው፤ በዐውሎ ነፋስ እንደሚወሰዱ ደመናዎች ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማም ይጠብቃቸዋል። በስሕተት ከሚኖሩት ሰዎች መካከል አምልጠው ከመጡ ገና ብዙ ያልቈዩትን ሰዎች ከንቱ የሆነ የዕብሪት ቃል በመናገር፥ በሥጋዊ ፍትወትና በሴሰኛነት በማባበል ያታልሉአቸዋል። “ነጻ ትወጣላችሁ” እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል። ሰው ሲሸነፍ ላሸናፊው ባሪያ ሆኖ ስለሚገዛ እነርሱም ራሳቸው የኃጢአት ባሪያዎች ናቸው። ጌታችንንና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኲሰት ካመለጡ በኋላ ተመልሰው በዚያው ርኲሰት ተይዘው ቢሸነፉ ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የባሰ ይሆንባቸዋል፤ የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ ይልቅ የጽድቅን መንገድ ሳያውቁ ቀርተው ቢሆን ኖሮ በተሻላቸው ነበር። “የተፋውን ለመዋጥ ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል።” እንዲሁም “ዐሣማ ከታጠበ በኋላ ተመልሶ በጭቃ ላይ ይንከባለላል” የሚለው እውነተኛ ምሳሌ ደርሶባቸዋል።
2 የጴጥሮስ መልእክት 2 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 የጴጥሮስ መልእክት 2:10-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos