2 ነገሥት 18:9-37
2 ነገሥት 18:9-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ የእስራኤል ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ወጣ፤ ከበባትም። በሦስተኛውም ዓመት ያዛት፤ በሕዝቅያስ በስድስተኛው ዓመተ መንግሥት፥ በእስራኤል ንጉሥ በሆሴዕ በዘጠነኛው ዓመተ መንገሥት፥ ሰማርያ ተያዘች። የአሦርም ንጉሥ እስራኤልን ወደ አሦር አፈለሰ፤ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ፥ በሜዶንም አውራጃዎች አኖራቸው፤ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙምና፥ ቃል ኪዳኑንም አፍርሰዋልና፥ የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አልሰሙምና፤ አላደረጉምምና። ሕዝቅያስም በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጣ፤ ወሰዳቸውም። የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ፥ “በድያለሁ፥ ከእኔ ተመለስ፤ የምትጭንብኝንም ሁሉ እሸከማለሁ” ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ለኪሶ መልእክተኞችን ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ ጫነበት። ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤተ መዛግብት የተገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው። በዚያን ጊዜም ሕዝቅያስ ከእግዚአብሔር መቅደስ ደጆችና የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከለበጣቸው መቃኖች ወርቁን ቈረጠ፤ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠው። የአሦርም ንጉሥ ተርታንንና ራፌስን ራፋስቂስንም ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላካቸው። ወጥተውም ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ፤ በአጣቢውም እርሻ መንገድ ባለችው በላዪኛዪቱ ኩሬ መስኖ አጠገብ ቆሙ። ሕዝቅያስንም ጠሩ፤ የቤቱም አዛዥ የኬልቅዩ ልጅ ኤልያቄም ጸሓፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሓፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ወጡ። ራፋስቂስም አላቸው፥ “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ታላቁ ንጉሥ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ይህ የምትተማመንበት መተማመኛ ምንድን ነው? የከንፈር ቃል ለሰልፍ ምክርና ኀይል እንደሚሆን ትናገራለህ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብፅ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል፥ ያቈስለውማል፤ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። እናንተም፦ በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትሉኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፦ በኢየሩሳሌም ባለው በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን? አሁንም እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፤ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሶች በግብፅ ስትታመን፥ ከጌታዬ አገልጋዮች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ትመልስ ዘንድ እንዴት ይቻልሃል? አሁን በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን ስፍራ እናጠፋ ዘንድ ወጥተናልን? እግዚአብሔር፦ ወደዚች ሀገር ወጥታችሁ አጥፉአት አለን።” የኬልቅዩም ልጅ ኤልያቄም ሳምናስም ዮአስም ራፋስቂስን፥ “እኛ እንሰማለንና በሱርስት ቋንቋ ለአገልጋዮችህ ተናገር፤ በዕብራይስጥም ቋንቋ አትናገረን፤ በቅጥርም ላይ ያለው ሕዝብ በሚሰማው ቋንቋ ለምን ትናገራለህ?” አሉት። ራፋስቂስ ግን፥ “በውኑ ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ እናንተና ወደ ጌታችሁ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን?” አላቸው። ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ፥ “የታላቁን የአሦር ንጉሥ ቃል ስሙ፤ ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል፤ ይህችንም ከተማ የአሦር ንጉሥ ሊይዛት አይችልም እያለ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሶር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ከእኔ ጋር ታረቁ፤ ወደ እኔም ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፤ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን፥ ወይራና ማር ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ በሕይወት እንድትኖሩ፥ እንዳትሞቱም ነው። ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር ያድናችኋል ብሎ ያታልላችኋልና አትስሙት። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? የኤማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፋሩዋይምና የሄና የዒዋም አማልክት ወዴት አሉ? ስማርያን ከእጄ አድነዋታልን? እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድናት ዘንድ ከሀገሮቹ አማልክት ሁሉ ሀገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?” ሕዝቡም ዝም አሉ፥ አንዳችም ቃል አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና። የቤቱ አዛዥ የኬልቅዩ ልጅ ኤልያቄም፥ ጸሓፊው ሳምናስ፥ ታሪክ ጸሓፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ ገቡ፥ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።
2 ነገሥት 18:9-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ የእስራኤልም ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ገሥግሦ ከተማዪቱን ከበባት፤ በሦስተኛውም ዓመት መጨረሻ ያዛት። ሰማርያ የተያዘችውም ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፣ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር። የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ማርኮ ወደ አሦር በማፍለስ በአላሔ፣ በጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብና በማዴ ከተሞች አሰፈራቸው። ይህ የደረሰባቸውም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመስማት ይልቅ ኪዳኑን ስላፈረሱ ነበር፤ ትእዛዞቹን አላደመጡም፤ ደግሞም አልፈጸሙም። ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች ሁሉ አጥቅቶ ያዛቸው። ስለዚህ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ “በደለኛው እኔ ነኝ፤ ተመለስልኝ፤ እኔም የምትጠይቀኝን ሁሉ እከፍላለሁ፤” ሲል በለኪሶ ወደ ሰፈረው ወደ አሦር ንጉሥ ይህን መልእክት ላከ። የአሦርም ንጉሥ፣ የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ እንዲያገባለት ጠየቀው። ስለዚህ ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው። በዚህ ጊዜም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መዝጊያዎችና መቃኖች ላይ የለበጠውን ወርቅ ነቃቅሎ ለአሦር ንጉሥ ሰጠው። የአሦር ንጉሥ ከለኪሶ የጦሩን ጠቅላይ አዛዥ፣ ዋና አዛዡንና የጦር መሪውን ከታላቅ ሰራዊት ጋራ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ ወደ ልብስ ዐጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው የላይኛው ኵሬ ውሃ ቦይ በሚወርድበት ስፍራ ሲደርሱ ቆሙ። ወደ ንጉሡም ላኩበት፤ ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ፣ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ፣ ታሪክ መዝጋቢውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ሄዱ። የጦር አዛዡም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፤ “ ‘ታላቁ ንጉሥ፣ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ እስከዚህ የተማመንህበት ነገር ምንድን ነው? የጦር ስልትና ኀይል አለኝ ትላለህ፤ ነገር ግን ባዶ ቃል ብቻ ትናገራለህ። በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተደግፈህ ነው? እነሆ፤ እንዲህ የምትመካባት ግብጽ የሚደገፍባትን ሰው እጅ ወግታ የምታቈስል፣ የተቀጠቀጠች ሸንበቆ ናት። የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንም ለሚመኩበት ሁሉ እንደዚሁ ነው። ደግሞም፣ “በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን” የምትለኝ ከሆነ፣ የኰረብታ ላይ ማምለኪያዎቹንና መሠዊያዎቹን ሕዝቅያስ አፍርሶበት ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ “እናንተ መስገድ ያለባችሁ በዚህ መሠዊያ ፊት ብቻ ነው” ብሎ የለምን? “ ‘አሁን ናና፣ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋራ ተደራደር፤ የሚጋልቧቸው ሰዎች ካሉህ፣ ሁለት ሺሕ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። የምትመካው በግብጽ ሠረገሎችና ፈረሶች ሆኖ ሳለ፣ ከጌታዬ የበታች የጦር ሹማምት እንኳ አንዱን እንዴት መመለስ ትችላለህ? በተጨማሪም አደጋ ጥዬ ይህችን ስፍራ ለማጥቃትና ለማጥፋት የመጣሁት፣ ያለ እግዚአብሔር ይመስልሃል? በዚህች አገር ላይ ዘምቼ እንዳጠፋት የነገረኝ ራሱ እግዚአብሔር ነው።’ ” ከዚያም የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ሳምናስና ዮአስ የጦር አዛዡን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ስለምንሰማ፣ እባክህን በሶርያ ቋንቋ ተናገር፤ በቅጥሩ ላይ ያሉት ሰዎች በሚሰሙት በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት። ነገር ግን የጦር አዛዡ መልሶ፣ “ጌታዬ እነዚህን ቃሎች እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነበርን? እንደ እናንተ የራሳቸውን ኵስ ለመብላትና ሽንታቸውንም ለመጠጣት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎችም አይደለምን?” አላቸው። የጦር አዛዡም ቆሞ በዕብራይስጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እንግዲህ የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ! ንጉሡ እንዲህ ይላል፤ ከእጄ ሊያድናችሁ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ ደግሞም ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር በርግጥ ያድነናል፤ ይህች ከተማ ለአሦር ንጉሥ ዐልፋ አትሰጥም’ እያለ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። “ሕዝቅያስን አትስሙ። የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእኔ ጋራ ተስማሙ፤ ወደ እኔም ውጡ። ከዚያም እያንዳንዳችሁ ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጕድጓዳችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤ ይኸውም የእናንተኑ ወደምትመስለው ምድር እህልና የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን ተክል፣ የወይራ ዛፍና ማር ወዳለባት እስካገባችሁ ድረስ ነው፤ እናንተም ሞትን ሳይሆን ሕይወትን ምረጡ።’ “ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር ይታደገናል’ በማለት ስለሚያሳስታችሁ አትስሙት። ለመሆኑ ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ የታደገ ከአሕዛብ አማልክት የትኛው ነው? የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም፣ የሄናና የዒዋም አማልክት ታዲያ የት ደረሱ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ የታደገ ማን አለ? ታዲያ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዴት ከእጄ ሊታደጋት ይችላል?” ነገር ግን ሕዝቡ ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም፤ ንጉሡ፣ “መልስ እንዳትሰጡ” ሲል አዝዞ ነበርና። ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ እንዲሁም ታሪክ መዝጋቢው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ የጦር አዛዡ የተናገረውንም ሁሉ ነገሩት።
2 ነገሥት 18:9-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በንጉሡ በሕዝቅያስ በአራተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በኤላ ልጅ በሆሴዕ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ወጣ፤ ከበባትም። ከሦስት ዓመት በኋላም ወሰዳት፤ በሕዝቅያስ በስድስተኛው ዓመት፥ በእስራኤል ንጉሥ በሆሴዕ በዘጠነኛው ዓመት፥ ሰማርያ ተያዘች። የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ወደ አሦር አፈለሰ፤ በአላሔና በአቦር በጎዛንም ወንዝ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው፤ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙምና፥ ቃል ኪዳኑንም አፍርሰዋልና፥ የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አልሰሙምና፥ አላደረጉምና። በንጉሡም በሕዝቅያስ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጣ፤ ወሰዳቸውም። የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ “በድያለሁ፤ ከእኔ ተመለስ፤ የምትጭንብኝን ሁሉ እሸከማለሁ፤” ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ለኪሶ ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ ጫነበት። ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤተ መዛግብት የተገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው። በዚያን ጊዜም ሕዝቅያስ ከእግዚአብሔር መቅደስ ደጆችና የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከለበጣቸው መቃኖች ወርቁን ቈረጠ፤ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠው። የአሦርም ንጉሥ ተርታንንና ራፌስን ራፋስቂስንም ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ። ወጥተውም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ በመጡም ጊዜ በአጣቢው እርሻ መንገድ ባለችው በላይኛይቱ ኩሬ መስኖ አጠገብ ቆሙ። ንጉሡንም ጠሩ፤ የቤቱም አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ወጡ። ራፋስቂስም አላቸው “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ ይህ የምትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው? የከንፈር ቃል ለሰልፍ ምክርና ኀይል እንደሚሆን ትናገራለህ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብጽ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል፤ ያቈስለውማል፤ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው።’ እናንተም ‘በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን፤’ ብትሉኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ‘በኢየሩሳሌም ባለው በዚህ መሠዊያ ፊት ሰገዱ፤’ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያውቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን? አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፤ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። ስለ ሠረገሎችና ሰለ ፈረሰኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱ አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል? አሁን በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን ስፍራ አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር ‘ወደዚች አገር ወጥተህ አጥፋት፤’ አለኝ።” የኬልቅያስም ልጅ ኤልያቄም ሳምናስም ዮአስም ራፋስቂስን “እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን፤” አሉት። ራፋስቂስ ግን “ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን?” አላቸው። ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኽ “የታላቁን የአሦር ንጉሥ ቃል ስሙ፤ ንጉሡ እንዲህ ይላል ‘ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ ሕዝቅያስም “እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል፤ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም፤” ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። ሕዝቅያስንም አትስሙ፤’ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል ‘ከእኔ ጋር ታረቁ፤ ወደ እኔም ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፤ ከጕድጓዳችሁም ውሃ ጠጡ፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን፥ ወይራና ማር ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ በሕይወት እንድትኖሩ እንዳትሞቱም ነው። ሕዝቅያስም “እግዚአብሔር ያድነናል፤” ብሎ ቢያታልላችሁ አትስሙት። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይምና የሄና የዒዋም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከአገሮቹ አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?’” ሕዝቡም ዝም አሉ፤ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና። የቤቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።
2 ነገሥት 18:9-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ይህም ማለት ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር በእስራኤል ላይ አደጋ በመጣል ሰማርያን ከበበ፤ በተከበበችበትም በሦስተኛው ዓመት ሰማርያ በሙሉ ተያዘች፤ ይህም የሆነው ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፥ ሆሴዕ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር። የአሦር ንጉሠ ነገሥት እስራኤላውያንን ማርኮ ወደ አሦር በመውሰድ ከእነርሱ ጥቂቶቹ በሐላሕ ከተማ ጥቂቶቹ በጎዛን አውራጃ በሚገኘው በሐቦር ወንዝ አጠገብ፥ ሌሎቹ ደግሞ በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ። ሰማርያ የወደቀችበት ምክንያት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ነው፤ ይኸውም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አፈረሱ፤ የእግዚአብሔር አገልጋይ በሆነው በሙሴ አማካይነት ለተሰጠ ሕግ ሁሉ ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ቃሉን ማዳመጥም ሆነ ሕጉን መጠበቅ አልፈለጉም። ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም አደጋ በመጣል የተመሸጉትን የይሁዳን ከተሞች ያዘ፤ ሕዝቅያስም በላኪሽ ሰፍሮ ለነበረው ለሰናክሬም “እኔ በድያለሁ፤ እባክህን አቁም፤ የምትጠይቀኝን ሁሉ እከፍላለሁ” ሲል መልእክት ላከ፤ ንጉሠ ነገሥቱም “እኔ የምፈልገው ዐሥር ሺህ ኪሎ ብርና አንድ ሺህ ኪሎ ወርቅ እንድትልክልኝ ነው” ሲል መለሰለት። ሕዝቅያስም በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ዕቃ ግምጃ ቤት የነበረውን ብር ሁሉ ሰብስቦ ላከለት፤ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ መግቢያ በሮች ላይ ተለብጦ የነበረውን ወርቅና እርሱም ራሱ በቤተ መቅደሱ የበር ዐምዶች ላይ ለብጦት የነበረውን ወርቅ ጭምር ወደ ሰናክሬም ላከ። ይህ በዚህ እንዳለ የአሦር ንጉሠ ነገሥት እንደገና የተጠናከረ ታላቅ ሠራዊት ከላኪሽ ተንቀሳቅሶ ወደ ኢየሩሳሌም በመዝመት በሕዝቅያስ ላይ አደጋ እንዲጥልበት አዘዘ፤ ያም ሠራዊት ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ሦስት የጦር አዛዦቹ የሚመራ ነበር፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ደረሱ ከላይኛው ኲሬ ውሃ በሚተላለፍበት ቦይ አጠገብ ወደ ልብስ አጣቢዎች መስክ የሚወስደውን መንገድ ያዙ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሕዝቅያስ መልእክት ላኩበት፤ ሕዝቅያስም ባለሟሎቹ የሆኑ ሦስት ባለሥልጣኖች ሄደው እንዲገናኙአቸው አዘዘ፤ እነርሱም የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ የሆነ የሒልቂያ ልጅ ኤልያቄም፥ እንዲሁም የቤተ መንግሥት ጸሐፊ የሆነው ሼብናና የቤተ መዛግብት ኀላፊ የሆነው የአሳፍ ልጅ ዮአሕ ነበሩ፤ ከአሦር የጦር አዛዦች አንዱ እንዲህ አላቸው፦ “ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ለመሆኑ እንደዚህ አድርገህ የተማመንክበት ነገር ምንድን ነው? የቃላት ጋጋታ የጦርነትን ስልትና ኀይል የሚተካ ይመስልሃልን? ማን ይረዳኛል ብለህ ነው በአሦር ላይ ለማመፅ ያሰብከው? የግብጽ ንጉሥ ይረዳኛል ብለህ አስበህ ከሆነ፥ የተቀጠቀጠ ሸምበቆ እንደሚመረኰዝ ሰው መሆንህ ነው፤ እርሱ ተሰብሮ ስንጣሪው እጅህን ያቈስልሃል፤ እንግዲህ የግብጽ ንጉሥ ለሚተማመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው’ ሲል የአሦር ንጉሠ ነገሥት ይጠይቅሃል።” የአሦር የጦር አዛዥ ንግግሩን በመቀጠል እንደገና እንዲህ አለ፦ “አምላክህ እግዚአብሔር እንደሚረዳህ አድርገህ ታስባለህን? ይህማ እንዳይሆን፥ አንተ የእግዚአብሔርን የተቀደሱ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን ደምስሰህ ‘የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ማምለክ የሚገባቸው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው በአንድ መሠዊያ ብቻ ነው’ ብለህ ወስነሃል። አሁንም በንጉሠ ነገሥቱ ስም ለፍልሚያ እጠይቅሃለሁ፤ መጋለብ የሚችሉ በቂ ሰዎች ታገኝ እንደ ሆነ እስቲ ሁለት ሺህ ፈረሶች ልስጥህ! አንተ እኮ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከሆነው ከአሦር ተራ የጦር መኰንን ጋር እንኳ መወዳደር አትችልም፤ ግብጻውያን ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይልኩልኛል ብለህ የምትጠባበቀውም በዚሁ ምክንያት ነው። እኔ በአንተ አገር ላይ አደጋ የጣልኩባትና የደመሰስኳት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃልን? እግዚአብሔር ራሱ በዚህች አገር ላይ አደጋ እንድጥልባትና እንድደመስሳት አዞኛል።” ከዚህም በኋላ ኤልያቄምና፥ ሼብና እንዲሁም ዮአሕ ይህን የጦር አዛዥ “ፍቹን ስለምናውቅ በሶርያ ቋንቋ እንድትነግረን እንለምንሃለን፤ በቅጽር ላይ ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሚሰሙት በዕብራይስጥ ቋንቋ አትናገረን” አሉት። እርሱም “የአሦር ንጉሠ ነገሥት ይህን ሁሉ ለእናንተና ለንጉሣችሁ ብቻ እንድናገር የላከኝ መሰላችሁን? ከቶ አይደለም፤ ልክ እንደ እናንተ ኩሳቸውን ለመብላትና ሽንታቸውን ለመጠጣት የሚገደዱ ሰዎችም ጭምር ስለ ሆኑ፥ እኔ የምናገረውን በቅጽሩ ላይ ያሉት ሰዎች ሁሉ እንዲሰሙት ነው” ሲል መለሰላቸው። ከዚህም በኋላ ያ የአሦር ባለሥልጣን ከተቀመጠበት ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ እያለ መናገር ጀመረ፤ “የአሦር ንጉሠ ነገሥት የሚነግራችሁን ስሙ! በሕዝቅያስ አትታለሉ! እርሱ ሊያድናችሁ ከቶ አይችልም! ሕዝቅያስ ‘በእግዚአብሔር ታመኑ፤ እርሱ ያድናችኋል፤ ከተማችንም በአሦርያውያን ሠራዊት እጅ እንዳትገባ ይከላከልልናል’ እያለ የሚሰብካችሁን አትስሙ፤ ሕዝቅያስ የሚላችሁን አታዳምጡ፤ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ከከተማችሁ ወጥታችሁ እጃችሁን እንድትሰጡ አዞአችኋል፤ ይህን ብታደርጉ ሁላችሁም እያንዳንዳችሁ የወይን ተክሎቻችሁን ዘለላና የበለስ ዛፎቻችሁን ፍሬ ትበላላችሁ፤ ከጒድጓዶቻችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤ ይህም ሁሉ የሚሆነው ንጉሠ ነገሥቱ የእናንተን አገር ወደምትመስል ምድር ወስዶ እስከሚያሰፍራችሁ ድረስ ነው፤ በዚያችም ምድር ወይን ጠጅ የሚገኝባቸው የወይን ተክል ቦታዎችና በቂ የእንጀራ እህል የሚመረትባቸው እርሻዎች አሉ፤ ምድሪቱም የወይራ ፍሬና የወይራ ዘይት እንዲሁም ማር. የሞላባት ናት፤ ንጉሠ ነገሥቱ የሚያዛችሁን ብትፈጽሙ በሕይወት ትኖራላችሁ እንጂ አትሞቱም፤ ስለዚህ ሕዝቅያስ ‘እግዚአብሔር ይታደጋችኋል’ እያለ በመስበክ አያሞኛችሁ፤ ለመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች አማልክት አንዱ እንኳ ከአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አገሩን ያዳነ ይገኛልን? ታዲያ ይህ ከሆነ የሐማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሰፋርዋይም የሄናዕና የዒዋ አማልክትስ የት ደረሱ? ከእነርሱ አንዱ እንኳ ሰማርያን ከእጄ ማዳን ችሎአልን? የእነዚህ ሁሉ አገሮች አማልክት ከንጉሠ ነገሥታቶቻችን እጅ አገሮቻቸውን ለማዳን የቻሉበት ጊዜ አለን? ታዲያ እንግዲህ እናንተ ‘እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድናታል’ ብላችሁ የምታስቡት እንዴት ነው?” ሕዝቡም ቀደም ሲል ንጉሥ ሕዝቅያስ ባዘዛቸው መሠረት አንዲት ቃል ሳይናገሩ ዝም አሉ፤ ከዚህ በኋላ ኤልያቄምና ሼብና እንዲሁም ዮአሕ በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ቀርበው የአሦራውያን ባለሥልጣን የተናገረውን አስረዱት።
2 ነገሥት 18:9-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ይህም ማለት ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፥ የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር በእስራኤል ላይ አደጋ በመጣል ሰማርያን ከበበ፤ በተከበበችበትም በሦስተኛው ዓመት ሰማርያ በሙሉ ተያዘች፤ ይህም የሆነው ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፥ ሆሴዕ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር። የአሦር ንጉሠ ነገሥት እስራኤላውያንን ማርኮ ወደ አሦር በመውሰድ ከእነርሱ ጥቂቶቹ በሐላሕ ከተማ ጥቂቶቹ በጎዛን አውራጃ በሚገኘው በሐቦር ወንዝ አጠገብ፥ ሌሎቹ ደግሞ በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ። ሰማርያ የወደቀችበት ምክንያት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ነው፤ ይኸውም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አፈረሱ፤ የእግዚአብሔር አገልጋይ በሆነው በሙሴ አማካይነት ለተሰጠ ሕግ ሁሉ ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ቃሉን ማዳመጥም ሆነ ሕጉን መጠበቅ አልፈለጉም። ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም አደጋ በመጣል የተመሸጉትን የይሁዳን ከተሞች ያዘ፤ ሕዝቅያስም በላኪሽ ሰፍሮ ለነበረው ለሰናክሬም “እኔ በድያለሁ፤ እባክህን አቁም፤ የምትጠይቀኝን ሁሉ እከፍላለሁ” ሲል መልእክት ላከ፤ ንጉሠ ነገሥቱም “እኔ የምፈልገው ዐሥር ሺህ ኪሎ ብርና አንድ ሺህ ኪሎ ወርቅ እንድትልክልኝ ነው” ሲል መለሰለት። ሕዝቅያስም በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ዕቃ ግምጃ ቤት የነበረውን ብር ሁሉ ሰብስቦ ላከለት፤ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ መግቢያ በሮች ላይ ተለብጦ የነበረውን ወርቅና እርሱም ራሱ በቤተ መቅደሱ የበር ዐምዶች ላይ ለብጦት የነበረውን ወርቅ ጭምር ወደ ሰናክሬም ላከ። ይህ በዚህ እንዳለ የአሦር ንጉሠ ነገሥት እንደገና የተጠናከረ ታላቅ ሠራዊት ከላኪሽ ተንቀሳቅሶ ወደ ኢየሩሳሌም በመዝመት በሕዝቅያስ ላይ አደጋ እንዲጥልበት አዘዘ፤ ያም ሠራዊት ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ሦስት የጦር አዛዦቹ የሚመራ ነበር፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ደረሱ ከላይኛው ኲሬ ውሃ በሚተላለፍበት ቦይ አጠገብ ወደ ልብስ አጣቢዎች መስክ የሚወስደውን መንገድ ያዙ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሕዝቅያስ መልእክት ላኩበት፤ ሕዝቅያስም ባለሟሎቹ የሆኑ ሦስት ባለ ሥልጣኖች ሄደው እንዲገናኙአቸው አዘዘ፤ እነርሱም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነ የሒልቂያ ልጅ ኤልያቄም፥ እንዲሁም የቤተ መንግሥት ጸሐፊ የሆነው ሼብናና የቤተ መዛግብት ኃላፊ የሆነው የአሳፍ ልጅ ዮአሕ ነበሩ፤ ከአሦር የጦር አዛዦች አንዱ እንዲህ አላቸው፦ “ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ለመሆኑ እንደዚህ አድርገህ የተማመንክበት ነገር ምንድነው? የቃላት ጋጋታ የጦርነትን ስልትና ኃይል የሚተካ ይመስልሃልን? ማን ይረዳኛል ብለህ ነው በአሦር ላይ ለማመፅ ያሰብከው? የግብጽ ንጉሥ ይረዳኛል ብለህ አስበህ ከሆነ፥ የተቀጠቀጠ ሸምበቆ እንደሚመረኰዝ ሰው መሆንህ ነው፤ እርሱ ተሰብሮ ስንጣሪው እጅህን ያቆስልሃል፤ እንግዲህ የግብጽ ንጉሥ ለሚተማመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው’ ሲል የአሦር ንጉሠ ነገሥት ይጠይቅሃል።” የአሦር የጦር አዛዥ ንግግሩን በመቀጠል እንደገና እንዲህ አለ፦ “አምላክህ እግዚአብሔር እንደሚረዳህ አድርገህ ታስባለህን? ይህማ እንዳይሆን፥ አንተ የእግዚአብሔርን የተቀደሱ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን ደምስሰህ ‘የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ማምለክ የሚገባቸው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው በአንድ መሠዊያ ብቻ ነው’ ብለህ ወስነሃል። አሁንም በንጉሠ ነገሥቱ ስም ለፍልሚያ እጠይቅሃለሁ፤ መጋለብ የሚችሉ በቂ ሰዎች ታገኝ እንደሆነ እስቲ ሁለት ሺህ ፈረሶች ልስጥህ! አንተ እኮ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከሆነው ከአሦር ተራ የጦር መኰንን ጋር እንኳ መወዳደር አትችልም፤ ግብጻውያን ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይልኩልኛል ብለህ የምትጠባበቀውም በዚሁ ምክንያት ነው። እኔ በአንተ አገር ላይ አደጋ የጣልኩባትና የደመሰስኳት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃልን? እግዚአብሔር ራሱ በዚህች አገር ላይ አደጋ እንድጥልባትና እንድደመስሳት አዞኛል።” ከዚህም በኋላ ኤልያቄምና፥ ሼብና እንዲሁም ዮአሕ ይህን የጦር አዛዥ “ፍቹን ስለምናውቅ በሶርያ ቋንቋ እንድትነግረን እንለምንሃለን፤ በቅጽር ላይ ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሚሰሙት በዕብራይስጥ ቋንቋ አትናገረን” አሉት። እርሱም “የአሦር ንጉሠ ነገሥት ይህን ሁሉ ለእናንተና ለንጉሣችሁ ብቻ እንድናገር የላከኝ መሰላችሁን? ከቶ አይደለም፤ ልክ እንደ እናንተ ኩሳቸውን ለመብላትና ሽንታቸውን ለመጠጣት የሚገደዱ ሰዎችም ጭምር ስለ ሆኑ፥ እኔ የምናገረውን በቅጽሩ ላይ ያሉት ሰዎች ሁሉ እንዲሰሙት ነው” ሲል መለሰላቸው። ከዚህም በኋላ ያ የአሦር ባለ ሥልጣን ከተቀመጠበት ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ እያለ መናገር ጀመረ፤ “የአሦር ንጉሠ ነገሥት የሚነግራችሁን ስሙ! በሕዝቅያስ አትታለሉ! እርሱ ሊያድናችሁ ከቶ አይችልም! ሕዝቅያስ ‘በእግዚአብሔር ታመኑ፤ እርሱ ያድናችኋል፤ ከተማችንም በአሦርያውያን ሠራዊት እጅ እንዳትገባ ይከላከልልናል’ እያለ የሚሰብካችሁን አትስሙ፤ ሕዝቅያስ የሚላችሁን አታዳምጡ፤ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ከከተማችሁ ወጥታችሁ እጃችሁን እንድትሰጡ አዞአችኋል፤ ይህን ብታደርጉ ሁላችሁም እያንዳንዳችሁ የወይን ተክሎቻችሁን ዘለላና የበለስ ዛፎቻችሁን ፍሬ ትበላላችሁ፤ ከጉድጓዶቻችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤ ይህም ሁሉ የሚሆነው ንጉሠ ነገሥቱ የእናንተን አገር ወደምትመስል ምድር ወስዶ እስከሚያሰፍራችሁ ድረስ ነው፤ በዚያችም ምድር ወይን ጠጅ የሚገኝባቸው የወይን ተክል ቦታዎችና በቂ የእንጀራ እህል የሚመረትባቸው እርሻዎች አሉ፤ ምድሪቱም የወይራ ፍሬና የወይራ ዘይት እንዲሁም ማር የሞላባት ናት፤ ንጉሠ ነገሥቱ የሚያዛችሁን ብትፈጽሙ በሕይወት ትኖራላችሁ እንጂ አትሞቱም፤ ስለዚህ ሕዝቅያስ ‘እግዚአብሔር ይታደጋችኋል’ እያለ በመስበክ አያሞኛችሁ፤ ለመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች አማልክት አንዱ እንኳ ከአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አገሩን ያዳነ ይገኛልን? ታዲያ ይህ ከሆነ የሐማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሰፋርዋይም የሄናዕና የዒዋ አማልክትስ የት ደረሱ? ከእነርሱ አንዱ እንኳ ሰማርያን ከእጄ ማዳን ችሎአልን? የእነዚህ ሁሉ አገሮች አማልክት ከንጉሠ ነገሥታቶቻችን እጅ አገሮቻቸውን ለማዳን የቻሉበት ጊዜ አለን? ታዲያ እንግዲህ እናንተ ‘እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድናታል’ ብላችሁ የምታስቡት እንዴት ነው?” ሕዝቡም ቀደም ሲል ንጉሥ ሕዝቅያስ ባዘዛቸው መሠረት አንዲት ቃል ሳይናገሩ ዝም አሉ፤ ከዚህ በኋላ ኤልያቄምና ሼብና እንዲሁም ዮአሕ በኀዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ቀርበው የአሦራውያን ባለ ሥልጣን የተናገረውን አስረዱት።