2 ነገሥት 10:10-17
2 ነገሥት 10:10-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እነሆ፥ እግዚአብሔር በአክአብ ቤት ላይ ከተናገረው ከእግዚአብሔር ቃል በምድር ላይ አንዳች እንዳይወድቅ አሁን ዕወቁ፤ እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ ቃል የተናገረውን አድርጎአል” አላቸው። ኢዩም ከአክአብ ቤት በኢይዝራኤል የቀረውን ሁሉ፥ ታላላቆቹንም ሁሉ፥ ወዳጆቹንና ካህናቱን ሁሉ ገደላቸው፤ ከእነርሱ አንድስ እንኳ አላስቀረም። ተነሥቶም ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድም ወዳለው ወደ በግ ጠባቂዎች ቤት በደረሰ ጊዜ፥ ኢዩ ከይሁዳ ንጉሥ ከአካዝያስ ወንድሞች ጋር ተገናኝቶ፥ “እናንተ እነማን ናችሁ?” አለ፤ እነርሱም፥ “እኛ የይሁዳ ንጉሥ የአካዝያስ ወንድሞች ነን፤ የንጉሡንና የእቴጌዪቱን ልጆች ደኅንነት እንነግረው ዘንድ ወረድን” አሉት። እርሱም፥ “በሕይወታቸው ያዙአቸው” ብሎ አዘዘ። በበግ ጠባቂዎች ቤትም አጠገብ አርባ ሁለቱን ሰዎች ገደሉአቸው፤ ከእነርሱም አንድ ሰው እንኳ አላስቀረም። ከዚያም በሄደ ጊዜ የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን በመንገድ አገኘው፤ ተቀብሎም መረቀው፤ ኢዩም፥ “ልቤ ከልብህ ጋር ቅን እንደ ሆነ ያህል ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን?” አለው። ኢዮናዳብም፥ “አዎን” አለው። ኢዩም፥ “እውነትህስ ከሆነ እጅህን ስጠኝ” አለ። እጁንም ሰጠው፤ ወደ እርሱም ወደ ሰረገላው አወጣው። “ከእኔ ጋር ና፥ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔርም እንደምቀና ታያለህ” አለው። ከእርሱም ጋር በሰረገላው አስቀመጠው። ወደ ሰማርያም ገብቶ ለኤልያስ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስኪያጠፋው ድረስ በሰማርያ የቀረውን የአክአብን ሰው ገደለ።
2 ነገሥት 10:10-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ እግዚአብሔር በአክዓብ ቤት ላይ ከተናገረው ቃል አንዲቱ እንኳ በምድር ላይ ወድቃ እንደማትቀር ዕወቁ። እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ የተናገረውን ፈጽሟል።” ስለዚህ ኢዩ ከአክዓብ ቤት የቀረውን ሁሉ፣ ታላላቆቹን ሰዎች በሙሉ፣ የቅርብ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳይቀር በኢይዝራኤል ገደላቸው። ከዚያም ኢዩ ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ ቤት ኤከድ ወደ ተባለው የበግ ጠባቂዎችም ቤት ሲደርስ፣ ከይሁዳ ንጉሥ ከአካዝያስ ሥጋ ዘመዶች ጥቂቶቹን አግኝቶ፣ “እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱም፣ “እኛ የአካዝያስ ሥጋ ዘመዶች ነን፤ ንጉሣዊውን ቤተ ሰብና የእቴጌዪቱን ልጆች ለመጠየቅ ወደዚህ ወርደን መጥተናል” አሉ። እርሱም፣ “ከነሕይወታቸው ያዟቸው!” ሲል አዘዘ፤ ስለዚህ ከነሕይወታቸው ወስደው በቤት ኤከድ ጕድጓድ አጠገብ አርባ ሁለቱን ሰዎች ገደሏቸው፤ አንድ እንኳ አላስቀረም። ከዚያም ተነሥቶ ሲሄድ የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ወደ እርሱ ሲመጣ መንገድ ላይ አገኘው። ኢዩም ሰላምታ ሰጥቶት “ልቤ ለልብህ ታማኝ የሆነውን ያህል የአንተስ ልብ ለልቤ እንዲሁ ታማኝ ነውን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮናዳብም፣ “አዎን፤ ነው!” ብሎ መለሰ። ኢዩም፣ “እንግዲያውስ እጅህን ስጠኝ” አለው። እጁንም ሰጠው፤ ከዚያም ኢዩ ደግፎ ወደ ሠረገላው አወጣው። ኢዩም፣ “በል አብረን እንሂድና ለእግዚአብሔር ያለኝን ቅናት እይልኝ” አለው፤ ከዚያም በሠረገላው ይዞት ሄደ። ኢዩ ወደ ሰማርያ በደረሰ ጊዜ፣ ከአክዓብ ቤተ ሰብ በዚያ የቀረውን ሁሉ ገደለ። ለነቢዩ ለኤልያስ በተነገረውም የእግዚአብሔር ቃል መሠረት አጠፋቸው።
2 ነገሥት 10:10-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔር በአክዓብ ቤት ላይ ከተናገረው ከእግዚአብሔር ቃል በምድር ላይ አንዳች እንዳይወድቅ አሁን እወቁ፤ እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ የተናገረውን አድርጎአል፤” አላቸው። ኢዩም ከአክዓብ ቤት የቀረውን ሁሉ፥ ታላላቆቹንም ሁሉ፥ ወዳጆቹንና ካህናቱን ማንም ሳይቀር በኢይዝራኤል ገደላቸው። ተነሥቶም ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድም ወዳለው ወደ በግ ጠባቂዎች ቤት በደረሰ ጊዜ፥ ኢዩ ከይሁዳ ንጉሥ ከአካዝያስ ወንድሞች ጋር ተገናኝቶ “እናንተ እነማን ናችሁ?” አለ። እነርሱም “እኛ የአካዝያስ ወንድሞች ነን፤ የንጉሡንና የእቴጌይቱን ልጆች ደኅንነት ለመጠየቅ እንወርዳለን፤” አሉት። እርሱም “በሕይወታቸው ያዙአቸው!” አለ። ያዙአቸውም፤ በበግ ጠባቂዎችም ቤት አጠገብ ባለው ጕድጓድ አርባ ሁለቱን ሰዎች ገደሉአቸው፤ ማንንም አላስቀረም። ከዚያም በሄደ ጊዜ የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን ተገናኘው፤ ደኅንነቱንም ጠይቆ “ልቤ ከልብህ ጋር እንደ ሆነ ያህል ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን?” አለው፤ ኢዮናዳብም “እንዲሁ ነው፤” አለው። ኢዩም “እንዲሁ እንደ ሆነስ እጅህን ስጠኝ፤” አለ። እጁንም ሰጠው፤ ወደ ሠረገላውም አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጠውና “ከእኔ ጋር ና፤ ለእግዚአብሔርም መቅናቴን እይ፤” አለው። በሠረገላውም አስቀመጠው። ወደ ሰማርያም በመጣ ጊዜ ለኤልያስ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስኪያጠፋው ድረስ ከአክዓብ በሰማርያ የቀረውን ሁሉ ገደለ።
2 ነገሥት 10:10-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህም ሁሉ እግዚአብሔር ስለ አክዓብ ትውልድ የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን ያስረዳል፤ እግዚአብሔር በአገልጋዩ በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት የተናገረውን ቃል ፈጽሞታል።” ከዚህም በኋላ ኢዩ በኢይዝራኤል የሚኖሩትን ሌሎቹን የአክዓብን ዘመዶች፥ ባለሟሎቹ የነበሩትን ባለሥልጣኖች እንዲሁም የቅርብ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳይቀር ሁሉንም ገደለ። ኢዩ ከኢይዝራኤል ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድ ሳለም “የእረኞች ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሲደርስ፥ ከሟቹ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ዘመዶች መካከል ጥቂቶቹን አግኝቶ “እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም “እኛ የአካዝያስ ዘመዶች ነን፤ አሁንም የንግሥት ኤልዛቤልን ልጆችና የቀሩትንም ንጉሣውያን ቤተሰብ እጅ ለመንሣት ወደ ኢይዝራኤል መሄዳችን ነው” ሲሉ መለሱለት። ኢዩም “እነዚህን ሰዎች ከነሕይወታቸው ያዙአቸው!” ሲል ለጭፍሮቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ ጭፍሮቹም ያዙአቸውና ኢዩ በዚያው በውሃ ጒድጓድ አጠገብ ገደላቸው። ብዛታቸውም በሙሉ አርባ ሁለት ሲሆን፥ ከእነርሱ አንድ እንኳ በሕይወት አልተረፈም። ኢዩ ተነሥቶ እንደገና ጒዞ ቀጠለ፤ በመንገድ ሳለም የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን አገኘ፤ ኢዩም ሰላምታ ከሰጠው በኋላ “እኔና አንተ በሐሳብ አንድ ነን፤ ታዲያ ከእኔ ጋር ትተባበራለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮናዳብም “አዎ እተባበርሃለሁ” ሲል መለሰ። ኢዩም “እንግዲያውስ ጨብጠኝ” ሲል መለሰለት፤ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኢዩ ደግፎት በሠረገላው ላይ አስቀመጠውና፥ “ከእኔ ጋር ሆነህ እኔ ለእግዚአብሔር ምን ያኽል ታማኝ እንደ ሆንኩ ራስህ ተመልከት” አለው፤ አብረውም እየጋለቡ ወደ ሰማርያ ሄዱ። እዚያም በደረሱ ጊዜ ኢዩ አንድም ሳያስቀር የአክዓብን ዘመዶች በሙሉ ፈጀ፤ ይህም ሁሉ የሆነው እግዚአብሔር በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት ነበር።
2 ነገሥት 10:10-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህም ሁሉ እግዚአብሔር ስለ አክዓብ ትውልድ የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን ያስረዳል፤ እግዚአብሔር በአገልጋዩ በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት የተናገረውን ቃል ፈጽሞታል።” ከዚህም በኋላ ኢዩ በኢይዝራኤል የሚኖሩትን ሌሎቹን የአክዓብን ዘመዶች፥ ባለሟሎቹ የነበሩትን ባለ ሥልጣኖች እንዲሁም የቅርብ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳይቀር ሁሉንም ገደለ። ኢዩ ከኢይዝራኤል ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድ ሳለም “የእረኞች ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሲደርስ፥ ከሟቹ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ዘመዶች መካከል ጥቂቶቹን አግኝቶ “እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም “እኛ የአካዝያስ ዘመዶች ነን፤ አሁንም የንግሥት ኤልዛቤልን ልጆችና የቀሩትንም ንጉሣውያን ቤተሰብ እጅ ለመንሣት ወደ ኢይዝራኤል መሄዳችን ነው” ሲሉ መለሱለት። ኢዩም “እነዚህን ሰዎች ከነሕይወታቸው ያዙአቸው!” ሲል ለጭፍሮቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ ጭፍሮቹም ያዙአቸውና ኢዩ በዚያው በውሃ ጉድጓድ አጠገብ ገደላቸው። ብዛታቸውም በሙሉ አርባ ሁለት ሲሆን፥ ከእነርሱ አንድ እንኳ በሕይወት አልተረፈም። ኢዩ ተነሥቶ እንደገና ጉዞ ቀጠለ፤ በመንገድ ሳለም የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን አገኘ፤ ኢዩም ሰላምታ ከሰጠው በኋላ “እኔና አንተ በሐሳብ አንድ ነን፤ ታዲያ ከእኔ ጋር ትተባበራለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮናዳብም “አዎ እተባበርሃለሁ” ሲል መለሰ። ኢዩም “እንግዲያውስ ጨብጠኝ” ሲል መለሰለት፤ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኢዩ ደግፎት በሠረገላው ላይ አስቀመጠውና፥ “ከእኔ ጋር ሆነህ እኔ ለእግዚአብሔር ምን ያኽል ታማኝ እንደሆንኩ ራስህ ተመልከት” አለው፤ አብረውም እየጋለቡ ወደ ሰማርያ ሄዱ። እዚያም በደረሱ ጊዜ ኢዩ አንድም ሳያስቀር የአክዓብን ዘመዶች በሙሉ ፈጀ፤ ይህም ሁሉ የሆነው እግዚአብሔር በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት ነበር።