2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 10
10
የአክዓብ ዘሮች ሁሉ መገደል
1ብዛታቸው ሰባ የሚሆን የአክዓብ ልጆች በሰማርያ ከተማ ይኖሩ ነበር፤ ኢዩ ደብዳቤ ጽፎ የደብዳቤውን አንዳንድ ቅጂ ለከተማይቱ ገዢዎች፥ ለታወቁ የአገር ሽማግሌዎችና የአክዓብን ተወላጆች ለሚያሳድጉ ሞግዚቶች ሁሉ ላከ፤ የደብዳቤውም ቃል፥ 2“እናንተ ለንጉሡ ተወላጆች ኃላፊዎች ናችሁ፤ ፈረሶችና ሠረገሎች የጦር መሣሪያዎችና የተመሸጉ ከተሞች ሁሉ በእናንተ እጅ ይገኛሉ፤ እንግዲህ ይህ ደብዳቤ እንደ ደረሳችሁ ወዲያውኑ፥ 3ከንጉሡ ተወላጆች የተሻለውን አንዱን መርጣችሁ አንግሡት፤ ለእርሱም በመከላከል ተዋጉለት!” የሚል ነበር።
4ከዚህም የተነሣ የሰማርያ ገዢዎች በፍርሃት ተሸብረው፥ “ንጉሥ ኢዮራምና ንጉሥ አካዝያስ ሊቋቋሙ ያልቻሉትን እኛ እንዴት ኢዩን ልንቋቋመው እንችላለን?” አሉ። 5ስለዚህም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊና የከተማይቱ ገዢ ከታወቁ የአገር ሽማግሌዎችና ከአሳዳጊ ሞግዚቶች ጋር በመተባበር ለኢዩ “እኛ አገልጋዮችህ ነን፤ አንተ የምታዘንን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች ነን፤ እኛ ማንንም አናነግሥም፤ አንተ መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” ሲሉ መልእክት ላኩ።
6ኢዩም “እናንተ ከእኔ ጋር ከተባበራችሁና ትእዛዜንም ለመፈጸም ዝግጁዎች ከሆናችሁ፥ ነገ በዚህ ጊዜ የንጉሥ አክዓብን ዘሮች ሁሉ ራሶቻቸውን ቆርጣችሁ ይዛችሁልኝ ኑ” ሲል ሌላ ደብዳቤ ጻፈላቸው።
ሰባው የንጉሥ አክዓብ ተወላጆች በሰማርያ አሳዳጊዎቻቸው በሆኑ በታወቁ የአገር ሽማግሌዎች ጥበቃ ሥር ነበሩ፤ 7የኢዩ ደብዳቤ እንደ ደረሳቸው የሰማርያ መሪዎች ሰባውንም የአክዓብ ተወላጆች በሙሉ ገደሉ፤ ራሶቻቸውንም በመቁረጥ በቅርጫት ሞልተው በኢይዝራኤል ወደነበረው ወደ ኢዩ ላኩለት።
8ኢዩ የአክዓብ ትውልድ ራሶች ተቆርጠው መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ በከተማይቱ ቅጽር በር በሁለት ረድፍ ተከምረው እስከ ተከታዩ ቀን ጧት ድረስ እንዲቆዩ ትእዛዝ ሰጠ፤ 9በማግስቱም ማለዳ ወደ ከተማይቱ ቅጽር በር ሄዶ በዚያ ለተሰበሰቡት ሕዝብ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “በንጉሥ ኢዮራም ላይ በማሤር የገደልኩት እኔ ነበርኩ፤ ስለዚህም እናንተ በዚያ ጉዳይ አትጠየቁበትም፤ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ የገደለ ማን ነው? 10ይህም ሁሉ እግዚአብሔር ስለ አክዓብ ትውልድ የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን ያስረዳል፤ እግዚአብሔር በአገልጋዩ በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት የተናገረውን ቃል ፈጽሞታል።” 11#ሆሴዕ 1፥4።ከዚህም በኋላ ኢዩ በኢይዝራኤል የሚኖሩትን ሌሎቹን የአክዓብን ዘመዶች፥ ባለሟሎቹ የነበሩትን ባለ ሥልጣኖች እንዲሁም የቅርብ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳይቀር ሁሉንም ገደለ።
የንጉሥ አካዝያስ ዘመዶች በሙሉ መገደል
12ኢዩ ከኢይዝራኤል ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድ ሳለም “የእረኞች ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሲደርስ፥ 13ከሟቹ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ዘመዶች መካከል ጥቂቶቹን አግኝቶ “እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲል ጠየቀ።
እነርሱም “እኛ የአካዝያስ ዘመዶች ነን፤ አሁንም የንግሥት ኤልዛቤልን ልጆችና የቀሩትንም ንጉሣውያን ቤተሰብ እጅ ለመንሣት ወደ ኢይዝራኤል መሄዳችን ነው” ሲሉ መለሱለት። 14ኢዩም “እነዚህን ሰዎች ከነሕይወታቸው ያዙአቸው!” ሲል ለጭፍሮቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ ጭፍሮቹም ያዙአቸውና ኢዩ በዚያው በውሃ ጉድጓድ አጠገብ ገደላቸው። ብዛታቸውም በሙሉ አርባ ሁለት ሲሆን፥ ከእነርሱ አንድ እንኳ በሕይወት አልተረፈም።
የቀሩት የአክዓብ ዘመዶች በሙሉ መገደል
15ኢዩ ተነሥቶ እንደገና ጉዞ ቀጠለ፤ በመንገድ ሳለም የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን አገኘ፤ ኢዩም ሰላምታ ከሰጠው በኋላ “እኔና አንተ በሐሳብ አንድ ነን፤ ታዲያ ከእኔ ጋር ትተባበራለህን?” ሲል ጠየቀው።
ኢዮናዳብም “አዎ እተባበርሃለሁ” ሲል መለሰ።
ኢዩም “እንግዲያውስ ጨብጠኝ” ሲል መለሰለት፤ እጅ ለእጅ ተያይዘው ኢዩ ደግፎት በሠረገላው ላይ አስቀመጠውና፥ 16“ከእኔ ጋር ሆነህ እኔ ለእግዚአብሔር ምን ያኽል ታማኝ እንደሆንኩ ራስህ ተመልከት” አለው፤ አብረውም እየጋለቡ ወደ ሰማርያ ሄዱ። 17እዚያም በደረሱ ጊዜ ኢዩ አንድም ሳያስቀር የአክዓብን ዘመዶች በሙሉ ፈጀ፤ ይህም ሁሉ የሆነው እግዚአብሔር በነቢዩ ኤልያስ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት ነበር።
ባዓል ተብሎ የሚጠራውን ጣዖት የሚያመልኩ መገደል
18ኢዩ የሰማርያን ሕዝብ በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ንጉሥ አክዓብ በዓልን ያገለገለው በመጠኑ ነበር፤ እኔ ግን ከእርሱ ይበልጥ ላገለግለው እፈልጋለሁ፤ 19ስለዚህም የበዓልን ነቢያት በሙሉ፥ በዓልን የሚያመልኩትንና ካህናቱን ጭምር በአንድነት ጠርታችሁ ሰብስቡልኝ፤ በምንም ምክንያት የሚቀር አይኑር፤ እኔ ለበዓል ታላቅ መሥዋዕት ስለማቀርብ በዚያ የማይገኝ ማንም ሰው ቢኖር በሞት ይቀጣል።” ይህም ሁሉ በዓልን የሚያመልኩትን ሁሉ ለመግደል ኢዩ ያቀደው የተንኰል ዘዴ ነበር። 20ከዚህም በኋላ ኢዩ “በዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት ክብረ በዓል ይደረግ!” ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ ይህም በዐዋጅ ተነገረ። 21ኢዩም በእስራኤል ምድር ሁሉ መልእክት አስተላለፈ፤ በዓልን የሚያመልኩ ሁሉ ተሰበሰቡ፤ አንድም እንኳ የቀረ ሰው አልነበረም፤ ሁሉም ወደ በዓል ቤተ መቅደስ ገብተው ዳር እስከ ዳር ሞሉት፤ 22ከዚህም በኋላ ኢዩ የተቀደሱ አባላት ኃላፊ የሆነውን ካህን አልባሳቱን ሁሉ አውጥቶ ለበዓል አምላኪዎች ያጐናጽፋቸው ዘንድ አዘዘ። 23ከዚህም በኋላ ኢዩ ራሱ የሬካብ ልጅ ከሆነው ከኢዮናዳብ ጋር አብሮ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ፤ በዚያም ለሕዝቡ “እንግዲህ በዚህ የሚገኙት የበዓል አምላኪዎች ብቻ መሆናቸውንና እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንድም አለመኖሩን በሚገባ አረጋግጡ” ሲል ተናገረ፤ 24ወዲያውም እርሱና ኢዮናዳብ ለበዓል የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም ልዩ ልዩ መሥዋዕት ለማቅረብ ገቡ፤ ከዚህም ቀደም ብሎ ኢዩ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ሰማኒያ ወታደሮች በማሰለፍ “እነዚህን ሁሉ ሰዎች እንድትገድሉ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ እንዲያመልጥ የሚያደርግ ማንም ሰው ቢኖር በዚያ ሰው ምትክ እርሱ ራሱ ይገደላል!” ሲል መመሪያ ሰጥቶአቸው ነበር።
25ኢዩ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ ወዲያውኑ ለዘብ ጠባቂዎችና ለጦር መኰንኖች “ገብታችሁ እነዚህን ሁሉ ግደሉ፤ አንድም ሰው እንዳያመልጥ!” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ሰይፍ ሰይፋቸውን በመምዘዝ ገብተው ሁሉንም ገደሉ፤ ሬሳቸውንም ሁሉ እየጐተቱ ወደ ውጪ አወጡት፤ ከዚህም በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ገብተው፥ 26በዚያ ያመልኩት የነበረውን የድንጋይ ዐምድ ወደ ውጪ አውጥተው በእሳት አቃጠሉት፤ 27በዚህም ዓይነት ጣዖት አምላኪዎቹ የተቀደሰ ነው ብለው የሚያምኑበትን የድንጋይ ዐምድና ቤተ መቅደሱን አፈራረሱ፤ ቤተ መቅደሱንም መጸዳጃ አደረጉት፤ ዛሬም በዚሁ ዓይነት ይገኛል። 28ኢዩ በእስራኤል የነበረውን የበዓልን ጣዖታዊ አምልኮ ያስወገደው በዚህ ዓይነት ዘዴ ነበር፤ 29#1ነገ. 12፥28-30።ነገር ግን ኢዩ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራውን የንጉሥ ኢዮርብዓምን የኃጢአት መንገድ ከመከተል አልተገታም፤ ኢዩ ራሱ ቀደም ሲል የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በቤትኤልና በዳን ላቆማቸው የወርቅ ጥጃ ምስሎች መስገዱ አልቀረም። 30ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ኢዩን “በአክዓብ ተወላጆች ሁሉ ላይ ልታደርግ የሚገባህን ባዘዝኩህ መሠረት ፈጽመሃል፤ ከዚህም የተነሣ የአንተ ትውልድ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ላይ እንደሚነግሡ የተስፋ ቃል እሰጥሃለሁ” አለው። 31ኢዩ ግን ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ሕግ በፍጹም ልቡ ታዛዥ ሆኖ አልተገኘም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራቸውን የኢዮርብዓምን ክፉ አርአያነት ተከተለ።
የኢዩ መሞት
32በዚያም ዘመን እግዚአብሔር የእስራኤል ግዛት ስፋቱ እንዲቀነስ ማድረግ ጀመረ፤ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል እስራኤልን ድል ነሥቶ የእስራኤልን ግዛት ሁሉ ያዘ። 33እርሱም የያዘው ግዛት፥ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ፥ በስተ ደቡብ በኩል ከአርኖን ወንዝ በላይ እስከምትገኘው እስከ አሮዔር ከተማ የሚደርስ ሲሆን ይህም የጋድ፥ የሮቤልና በምሥራቅ የሚገኘው የምናሴ ነገድ እኩሌታ ይኖሩባቸው የነበሩትን የገለዓድንና የባሳንን ግዛቶች ያጠቃልላል።
34ኢዩ ያደረገው ሌላው ነገርና የጀግንነት ሥራውም ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 35ከዚህም በኋላ ኢዩ ሞተ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮአካዝ ነገሠ፤ 36ኢዩ መኖሪያውን በሰማርያ በማድረግ በእስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን ሀያ ስምንት ዓመት ነበር።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 10: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ