2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 9
9
የኢዩ በእስራኤል ላይ ተቀብቶ መንገሥ
1በዚያን ጊዜ ነቢዩ ኤልሳዕ ደቀመዛሙርቱ ከሆኑት ነቢያት አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “በገለዓድ ወደምትገኘው ወደ ራሞት ለመሄድ ተዘጋጅ፤ ይህንንም የዘይት ማሰሮ ያዝ፤ 2እዚያም በደረስህ ጊዜ የኢዮሣፍጥ ልጅ፥ የኒምሺ የልጅ ልጅ የሆነውን ኢዩን ፈልግ፤ እርሱንም ከጓደኞቹ በማስገለል ወደ ጓዳ አስገባው፤ 3ይህን የወይራ ዘይት በራሱ ላይ አፍስስበት፤ ‘አንተ ተቀብተህ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ እግዚአብሔር አዞአል’ ብለህም ንገረው፤ ከዚህም በኋላ በሩን በመክፈት በተቻለ ፍጥነት ከዚያ ስፍራ ተነሥተህ ሽሽ።”
4ስለዚህም ወጣቱ ነቢይ ወደ ራሞት ሄደ፤ 5እዚያም እንደ ደረሰ የጦር መኰንኖች ተቀምጠው ሲወያዩ አግኝቶ “ጌታዬ ለአንተ የምሰጥህ መልእክት አለኝ” አለው።
ኢዩም “ከእኛ መካከል ለማንኛችን ነው የምትናገረው?” ሲል ጠየቀው።
ነቢዩም “የምናገረው ለአንተው ነው” ሲል መለሰ። 6#1ነገ. 19፥16።ከዚህ በኋላ ሁለቱ ወደ ቤት ውስጥ ገብተው ወጣቱ ነቢይ የወይራውን ዘይት በኢዩ ራስ ላይ አፈሰሰበትና እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚናገረው ይህ ነው፤ ‘በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ተቀብተህ እንድትነግሥ አድርጌሃለሁ፤ 7አንተም የአክዓብ ልጅ የሆነውን ጌታህን ንጉሡን መግደል አለብህ፤ በዚህም ዓይነት የእኔን ነቢያትና ሌሎችንም አገልጋዮቼን የገደለችውን ኤልዛቤልን እበቀላታለሁ፤ 8መላው የአክዓብ ቤተሰብና ትውልዱ ሁሉ መሞት አለባቸው፤ እኔ ከእርሱ ቤተሰብ ወንድ የሆነውን ማንኛውንም ባርያም ሆነ ነጻ ሰው አስወግዳለሁ። 9የእስራኤል ነገሥታት በነበሩት በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓምና በአኪያል ልጅ በበዕሻ ቤተሰቦች ላይ ያደረግኹትን፥ ሁሉ በአክዓብ ቤተሰብ ላይ እፈጽማለሁ። 10#1ነገ. 21፥23።ኤልዛቤል የመቀበር ዕድል እንኳ አታገኝም፤ የእርሷም ሬሳ በኢይዝራኤል ግዛት ውሾች ይበሉታል፤’” ይህን ሁሉ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ወጣቱ ነቢይ በሩን በመክፈት ከዚያ ክፍል ወጥቶ ሸሸ።
11ኢዩም፦ ጓደኞቹ ወደ ሆኑት ወደ ጦር መኰንኖቹ በመጣ ጊዜ “ሁሉ ነገር ሰላም ነውን? ለመሆኑ ይህ እብድ ከአንተ ምን ይፈልጋል?” ሲሉ ጠየቁት።
ኢዩም “ሰውየውንም ሆነ እርሱ የሚናገረውን እናንተ ታውቁታላችሁ” አላቸው።
12እነርሱም “ኧረ እኛ አናውቅም፤ ምን እንደ ተናገረ አስረዳን!” ሲሉ መለሱለት።
ኢዩም፦ “‘በእስራኤል ላይ ተቀብተህ እንድትነግሥ እግዚአብሔር አዞአል’ አለኝ” ሲል አስረዳቸው።
13ወዲያውኑ የኢዩ ጓደኞች የነበሩት የጦር መኰንኖች ልብሳቸውን እያወለቁ ኢዩ በሚራመድበት ደረጃ ላይ አነጠፉ፤ በዚያም ላይ እንዲቆም አድርገው እምቢልታ ነፉ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ኢዩ ነግሦአል!” ሲሉ ጮኹ።
የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም መገደል
14ስለዚህ የናሜሲ የልጅ ልጅ፥ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዩ በኢዮራም ላይ አሤረ። በዚህ ጊዜ ኢዮራምና እስራኤል ሁሉ በሬማት የምትገኘውን ገለዓድን ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጥቃት ለማዳን ይጠብቁ ነበር። 15ንጉሥ ኢዮራም ግን የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን ጦርነት በገጠመው ጊዜ፥ ሶርያውያን ካደረሱበት ቊስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል ተመልሶ ነበር። ኢዩም፥ “እንግዲህ ሐሳባችሁ እንዲህ ከሆነ፥ ይህን ነገር ወደ ኢይዝራኤል ሄዶ እንዳይናገር፥ ማንም ሰው ከዚህች ከተማ ሾልኮ እንዳይወጣ ጠብቁ” አለ። 16ከዚህም በኋላ ኢዩ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ገሠገሠ፤ በዚህ ጊዜ ኢዮራም ገና ከቁስሉ አልዳነም ነበር፤ የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም ሊጠይቀው መጥቶ በዚያ ይገኝ ነበር።
17በኢይዝራኤል ከተማ መጠበቂያ ግንብ ላይ የነበረው ቃፊር ኢዩና ተከታዩ ጭፍራ ሲመጡ መቃረባቸውን አይቶ፥ “ሰዎች እየጋለቡ ሲመጡ አያለሁ!” ሲል የጥሪ ድምፅ አሰማ።
ኢዮራምም “አንድ ፈረሰኛ ልከህ የሚመጡትን ሰዎች ሰላም ነውን? ብሎ እንዲጠይቅ አድርግ” አለው።
18መልእክተኛውም ጋልቦ ሄዶ ኢዩን “ንጉሡ አመጣጥህ በወዳጅነት እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋል” ሲል ጠየቀው።
ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!” ሲል መለሰለት።
በከተማይቱም መጠበቂያ ግንብ ላይ የነበረው ዘብ “መልእክተኛው በመምጣት ላይ ወዳለው ጭፍራ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ሲል አስረዳ፤ 19ሌላም መልእክተኛ ተልኮ ያንኑ ተመሳሳይ ጥያቄ ለኢዩ አቀረበለት፤ ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን ግንኙነት አለህ? ይልቅስ ወደ ኋላ አልፈህ ተከተለኝ!” ሲል መለሰለት።
20“ዘበኛውም እንደገና መልእክተኛው በመምጣት ላይ ወዳለው ጭፍራ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ካለ በኋላ “የጭፍራው መሪ ሠረገላ አነዳዱ እንደ እብድ ሰው ነው! እንዲያውም ልክ ኢዩን ይመስላል!” ሲል ተናገረ። 21ከዚህ በኋላ ንጉሥ ኢዮራም “ሠረገላዬን አዘጋጅልኝ” ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ ሠረገላውም ተዘጋጅቶለት እርሱና ንጉሥ አካዝያስ በየግል ሠረገላቸው እየጋለቡ ኢዩን ሊገናኙት ወጡ፤ እነርሱም ኢዩን ቀድሞ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ አገኙት። 22ኢዮራምም “ኢዩ ሆይ፥ አመጣጥህ በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀ።
ኢዩም፦ “እናትህ ኤልዛቤል ባመጣችው አስማትና የጣዖት አምልኮ ውስጥ ተነክረን እስካለን ድረስ ምን ሰላም አለ?” ሲል መለሰለት።
23ኢዮራምም ድምፁን ከፍ በማድረግ “አካዝያስ ሆይ! ይህ እኮ ክሕደት ነው!” እያለ ሠረገላውን መልሶ ሸሸ። 24ኢዩ ቀስቱን ስቦ ባለው ኃይል በመጠቀም ፍላጻውን ባስፈነጠረ ጊዜ ኢዮራምን ወግቶ በትከሻዎቹ መካከል እስከ ልቡ ዘለቀ፤ ኢዮራምም ሞቶ በሠረገላው ውስጥ ወደቀ። 25ኢዩ ቢድቃር ተብሎ የሚጠራውን የቅርብ ረዳቱን “ሬሳውን አንሥተህ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ ወርውረህ ጣለው፤ እኔና አንተ የንጉሥ ኢዮራም አባት ከነበረው ከአክዓብ በስተ ኋላ እየጋለብን ስንሄድ እግዚአብሔር በአክዓብ ላይ የተናገረውን ቃል አስታውስ፤ 26#1ነገ. 21፥19።‘ትናንትና የናቡቴንና የልጆቹን መገደል አየሁ፤ በዚሁ እርሻ ላይ እንደምቀጣህ እምላለሁ’ የሚል ነበር።” ስለዚህ ኢዩ “እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ የኢዮራምን ሬሳ አንሥተህ የናቡቴ ርስት በነበረው እርሻ ላይ በመወርወር ጣለው” ሲል የቅርብ ረዳቱን አዘዘ።
የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ መገደል
27ንጉሥ አካዝያስ የሆነውን ነገር ሁሉ በተመለከተ ጊዜ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ቤትሀጋን ከተማ ሸሽቶ ሄደ፤ ኢዩ ተከታትሎ እያሳደደው “እርሱንም ግደሉት!” ሲል ለወታደሮቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አካዝያስን ተከታትለው በዪብለዓም ከተማ አጠገብ በምትገኘው በጉር የአቀበት መንገድ ላይ በሠረገላው ሲበር መትተው አቆሰሉት፤ እርሱ ግን እንደ ምንም ጨክኖ መጊዶ ከተማ እስኪደርስ ተጓዘ፤ በዚያም ሞተ፤ 28ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖችም ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም ወስደው በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ቀበሩት።
29አካዝያስ የይሁዳ ንጉሥ የሆነው የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ነበር።
የንግሥት ኤልዛቤል መገደል
30በዚህም ጊዜ ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል ደረሰ፤ ኤልዛቤልም ይህን የሆነውን ነገር ሰምታ ዐይንዋን ተኳለች፤ ጠጉርዋንም ተሠርታ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ በመስኮት አዘንብላ ቁልቁል መንገዱን ትመለከት ነበር። 31ኢዩ የቅጽሩን በር አልፎ ሲገባ “አንተ ዚምሪ! አንተ የጌታህ ገዳይ ደግሞ እዚህ ምን አመጣህ?” ስትል ጮኸችበት።
32ኢዩ ቀና ብሎ ወደ ላይ በመመልከት ድምፁን ከፍ አድርጎ “ከእኔ ጋር የሚተባበር ማን ነው?” ሲል ጮኸ፤ ቁጥራቸው ከሁለት እስከ ሦስት የሆነ የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣኖች በመስኮት ብቅ ብለው ወደ እርሱ ተመለከቱ፤ 33ኢዩም “ኤልዛቤልን ወደ ታች ወርውሩአት!” አላቸው፤ እነርሱም አንሥተው በወረወሩአት ጊዜ ደምዋ በግንቡና በፈረሶች ላይ ተረጨ፤ ኢዩም በሬሳዋ ላይ ፈረሶቹንና ሠረገላውን ነዳበት፤ 34ወደ ቤተ መንግሥቱም ገብቶ ተመገበ፤ ከዚህም በኋላ “ምንም ቢሆን የንጉሥ ልጅ ነችና፥ ያችን የተረገመች ሴት ወስዳችሁ ቅበሩ” አለ። 35ሊቀብሩአት የሄዱ ሰዎች ግን ከራስ ቅልዋ፥ ከእግሮችዋና ከእጆችዋ አጥንት በቀር ምንም አላገኙም፤ 36#1ነገ. 21፥23።ይህንንም ሁሉ ለኢዩ በነገሩት ጊዜ ኢዩ እንዲህ አለ፤ “ይህ ሁሉ የተፈጸመው እግዚአብሔር በአገልጋዩ ቴስቢያዊው በኤልያስ አማካይነት አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ነው፤ ይኸውም ‘የኤልዛቤልም ሬሳ በኢይዝራኤል ግዛት ውሾች ይበሉታል፤ 37ከሬሳውም የሚተርፈው እንደ ፍግ በዚያ ይበተናል፤ ስለዚህም ማንም እርሷነትዋን ለይቶ በማወቅ፦ ይህች ኤልዛቤል ናት፥ ሊል አይችልም’ ያለው ነው።”
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 9: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ