2 ዜና መዋዕል 20:20-23
2 ዜና መዋዕል 20:20-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ማልደውም ተነሡ፤ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና፥ “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢዩም እመኑ፤ ነገሩም ይቀናላችኋል” አለ። ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን፥ “ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ” የሚሉትንም፥ በቅድስና የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔርም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ኀይልን ሰጣቸው፤ እነርሱም ተመቱ። የአሞንና የሞዓብ ልጆችም በሴይር ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ፥ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እርስ በርሳቸው ሊጠፋፉ ተነሡ።
2 ዜና መዋዕል 20:20-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በማግስቱም ጧት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ አድምጡኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው። ከሕዝቡም ጋር ከተመካከረ በኋላ ከሰራዊቱ ፊት ቀድመው በመሄድ፣ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” እያሉ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩና ስለ ቅድስናውም ክብር የሚያወድሱ ሰዎችን መደበ። መዘመርና ማወደስ እንደ ጀመሩም፣ እግዚአብሔር ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራ ሰዎች ላይ ድብቅ ጦር አመጣባቸው፤ ተሸነፉም። የአሞንና የሞዓብ ሰዎችም የሴይርን ተራራ ሰዎች ለማጥፋትና ለመደምሰስ ተነሡባቸው። ከሴይር የመጡትን ሰዎች ካጠፉ በኋላም፣ እርስ በርስ ተጠፋፉ።
2 ዜና መዋዕል 20:20-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ማልደውም ተነሡ፤ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ! ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፤ ነገሩም ይሰላላችኋል” አለ። ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን “ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤” የሚሉትን፥ ጌጠኛ ልብስ ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩትን መዘምራንን አቆመ። ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡ በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተመቱ። የአሞንና የሞዓብም ልጆችም በሴይርም ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እያንዳንዱ ባልንጀራውን ለማጥፋት ተረዳዳ።
2 ዜና መዋዕል 20:20-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሰዎቹ በማግስቱ ጠዋት በማለዳ ተነሥተው ተቆዓ ተብሎ ከሚጠራ ስፍራ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓማ አገር ሄዱ፤ ወደዚያ ለመሄድ ጒዞ በመጀመር ላይ ሳሉም ኢዮሣፍጥ እነርሱን “የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ተማመኑ፤ እርሱም ብርታትን ይሰጣችኋል፤ የእግዚአብሔር ነቢያት የሚነግሩአችሁንም እመኑ፤ ይሳካላችኋልም” አላቸው። ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ከሕዝቡ ጋር ከተመካከረ በኋላ መዘምራኑ በተቀደሱ በዓላት የሚለብሱአቸውን ካባዎች ለብሰው “ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ!” እያሉ በመዘመር በሠራዊቱ ፊት ለፊት እንዲያልፉ አዘዘ። መዘምራኑ መዘመርና ማመስገን በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔር በወራሪዎቹ ሠራዊት ላይ ድብቅ ጦር አምጥቶባቸው፥ ግራ ተጋቡ፤ ስለዚህ ዐሞናውያንና ሞአባውያን በኤዶማውያን ሠራዊት ላይ አደጋ ጥለው በሙሉ ደመሰሱአቸው፤ ከዚያም በመቀጠል በጭካኔ እርስ በርሳቸው ተፋጁ፤
2 ዜና መዋዕል 20:20-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ማልደውም በመነሣት ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና እንዲህ አለ፦ “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ! ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በጌታ እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሳካላችኋል።” ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን፦ “ጽኑ ፍቅሩ ለዘዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ” የሚሉትንም ጌጠኛ ልብስም ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለጌታም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡ በአሞንና በሙዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ ጌታ ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተሸነፉ። የአሞንና የሞዓብም ልጆችም በሴይርም ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ሊገድሉአቸውና ሊያጠፉአቸውም ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ አንዱ ሌላውን በማገዝ እርስ በርስ ተጠፋፉ።