1 ሳሙኤል 4:1-11
1 ሳሙኤል 4:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በእነዚያም ወራት እንዲህ ሆነ። ፍልስጥኤማውያን ለጦርነት በእስራኤላውያን ላይ ተሰበሰቡ። እስራኤልም ሊዋጉአቸው ወጡ፤ በአቤኔዜር አጠገብም ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንም በአፌቅ ሰፈሩ። ፍልስጥኤማውያንም እስራኤልን ለመውጋት ተሰለፉ፤ እስራኤልም ሸሹ፤ በፍልስጥኤማውያንም ፊት ድል ሆኑ፤ ጦርነት በተደረገበትም ስፍራ ከእስራኤል አራት ሺህ ሰዎች ተገደሉ። ሕዝቡም ወደ ሰፈር በተመለሱ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች፥ “ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ፊት ስለምን ጣለን? በፊታችን እንድትሄድ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንድታድነን፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ” አሉ። ሕዝቡም ወደ ሴሎ ላኩ፤ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጠውን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዚያ አመጡ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባች ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፤ ምድሪቱም አስተጋባች። ፍልስጥኤማውያንም የእልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ “በዕብራውያን ሰፈር ያለው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምንድን ነው?” አሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደ ደረሰች አስተዋሉ። ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው፥ “አማልክት ወደ እነርሱ ወደ ሰፈር መጥተዋል” አሉ። ደግሞም እንዲህ አሉ፥ “ወዮልን! አቤቱ፥ ዛሬ አድነን፤ ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር አልሆነምና። ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነዚህ አማልክት ግብፃውያንን በምድረ በዳ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ ናቸው። እናንተ ፍልስጥኤማውያን ሆይ! በርቱ፤ ጐብዙ፤ እናንተ ባሪያዎች እንዳደረጋችኋቸው ዕብራውያን ባሪያዎች እንዳያደርጓችሁ በርቱ፤ ተዋጉ።” ከዚህም በኋላ ተዋጉአቸው፤ እስራኤልም በፍልስጥኤማውያን ፊት ወደቁ፤ ሁሉም እያንዳንዳቸው ወደ ድንኳናቸው ሸሹ፤ እጅግም ታላቅ ግድያ ሆነ፤ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ። የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ።
1 ሳሙኤል 4:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የሳሙኤልም ቃል ወደ እስራኤል ሁሉ ደረሰ። በዚያ ዘመን እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ሊወጉ ወጡ፤ እስራኤላውያን በአቤንኤዘር፣ ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በአፌቅ ሰፈሩ። ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመግጠም ሰራዊታቸውን አሰለፉ፤ ጦርነቱ እንደ ተፋፋመም፣ እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ተሸነፉ፤ በጦርነቱም ላይ አራት ሺሕ ያህል እስራኤላውያን ተገደሉ። ሰራዊቱ ወደ ሰፈር በተመለሰ ጊዜ የእስራኤል አለቆች፣ “ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን እንድንሸነፍ ያደረገን ለምንድን ነው? አብሮን እንዲወጣ፣ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ” አሉ። ስለዚህ ሕዝቡ ሰዎችን ወደ ሴሎ ልከው፣ በኪሩቤል መካከል በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት አስመጡ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከኪዳኑ ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ። የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ፣ ምድሪቱ እስክትናወጥ ድረስ እስራኤላውያን ሁሉ ታላቅ የደስታ ጩኸት አሰሙ። ፍልስጥኤማውያንም ይህን ታላቅ ጩኸት ሲሰሙ፣ “በዕብራውያን ሰፈር የምንሰማው ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁ። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ሰፈር መምጣቱን በተረዱ ጊዜ፤ ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው እንዲህ አሉ፤ “አምላክ ወደ ሰፈሩ መጥቷል፤ ወዮልን! እንዲህ ዐይነት ነገር ገጥሞን አያውቅም። ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? ግብፃውያንን በምድረ በዳ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ እነዚሁ አማልክት ናቸው፤ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ በርቱ ወንድነታችሁም ይታይ፤ አለዚያ ባሪያ እንዳደረጋችኋቸው ሁሉ፣ ዕብራውያን እናንተን መልሰው ባሪያ ያደርጓችኋል። ወንድነታችሁ ይታይ፤ ተዋጉ!” ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ተዋጉ፤ እስራኤላውያንም ስለ ተሸነፉ እያንዳንዱ ወደየድንኳኑ ሸሸ። ታላቅ ዕልቂት ሆነ፤ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺሕ እግረኛ ወታደሮች ወደቁ። የእግዚአብሔር ታቦት ተማረከ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ተገደሉ።
1 ሳሙኤል 4:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እስራኤልም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሊዋጉ ወጡ፥ በአቤንኤዘር አጠገብ ሰፈሩ፥ ፍልስጥኤማውያንም በአፌቅ ሰፈሩ። ፍልስጥኤማውያንም በእስራኤል ላይ ተሰለፉ፥ ሰልፋም በተመደበ ጊዜ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ፊት ተመቱ፥ ጦርነት በተደረገበትም ስፍራ ከእስራኤል አራት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ገደሉ። ሕዝቡም ወደ ሰፈር በመጡ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች፦ ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ፊት ስለ ምን መታን? በመካከላችን እንዲሄድ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ አሉ። ሕዝቡም ወደ ሴሎ ላኩ፥ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጠውን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዚያ አመጡ፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፥ ምድሪቱም አስተጋባች። ፍልስጥኤማውያንም የእልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ፦ በዕብራውያን ሰፈር ያለው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምንድር ነው? አሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደገባ አስተዋሉ። ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው፥ እግዚአብሔር ወደ ሰፈር መጥቶአል አሉ። ደግሞም እንዲህ አሉ፦ ወዮልን፥ ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር አልሆነም። ወዮልን፥ ከእነዚህ ከኃያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነዚህ አማልክት ግብጻውያንን በምድረ በዳ በልዩ በልዩ መቅሠፍት የመቱ ናቸው። እናንተ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፥ አይዞአችሁ፥ ጎብዙ፥ እናንተ ባሪያዎች እንዳደረጋችኋቸው ዕብራውያን ባሪያዎች እንዳያደርጉአችሁ ጎብዙ፥ ተዋጉ። ፍልስጥኤማውያንም ተዋጉ፥ እስራኤልም ተመቱ፥ ሁሉም እያንዳንዱ ወደ ድንኳናቸው ሸሹ፥ እጅግም ታላቅ ግድያ ሆነ፥ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ። የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ።
1 ሳሙኤል 4:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት ወጡ፤ ስለዚህም እስራኤላውያን አቤንዔዜር ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንም አፌቅ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንም አደጋ መጣል ጀመሩ፤ ከከባድ ጦርነት በኋላ እስራኤላውያንን ድል በመንሣት በጦር ሜዳ አራት ሺህ ሰው ገደሉባቸው፤ ከጦርነት የተረፉት ወደ ሰፈራቸው በተመለሱ ጊዜ የእስራኤል መሪዎች እንዲህ አሉ፤ “ዛሬ ፍልስጥኤማውያን እኛን ድል ያደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር ስለምን ፈቀደላቸው? ከእኛ ጋር በመሄድ ከጠላቶቻችን እጅ ያድነን ዘንድ እንግዲህ እንሂድና የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከሴሎ እናምጣ።” ስለዚህም ወደ ሴሎ መልእክተኞች ልከው በታቦቱ ላይ ባሉ ኪሩቤል ዙፋኑን ያደረገ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግርማውን የሚገልጥበትን የቃል ኪዳኑን ታቦት አስመጡ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስም የቃል ኪዳኑን ታቦት አጅበው መጡ። የቃል ኪዳኑም ታቦት በዚያ ቦታ በደረሰ ጊዜ እስራኤላውያን ምድር እስክትናወጥ ድረስ ታላቅ የእልልታና የሆታ ድምፅ አሰሙ። ፍልስጥኤማውያንም ያንን የእልልታ ድምፅ ሰምተው “በዕብራውያን ሰፈር የምንሰማው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምን ይሆን?” ተባባሉ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዕብራውያን ሰፈር መምጣቱንም ባወቁ ጊዜ፥ ፈርተው እንዲህ አሉ፦ “ከአማልክት አንዱ ወደ እነርሱ ሰፈር መጥቶአል፤ እንግዲህ ወዮልን! ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ሁኔታ ደርሶብን አያውቅም፤ ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነርሱ ግብጻውያንን በበረሓ በተለያዩ መቅሠፍቶች የመቱ ናቸው። ፍልስጥኤማውያን ሆይ! እንግዲህ በርቱ! ጠንክሩ! ይህ ካልሆነ ቀድሞ እነርሱ የእኛ ባሪያዎች እንደ ነበሩ ሁሉ እኛም ደግሞ የዕብራውያን ባርያዎች ሆነን መቅረታችን ነው፤ ስለዚህ በወንድነት ጠንክራችሁ ተዋጉ!” ፍልስጥኤማውያንም በብርቱ ተዋግተው እስራኤላውያንን ድል ነሡ፤ እስራኤላውያንም ወደየድንኳናቸው ሸሹ፤ ታላቅ እልቂት ሆኖ ሠላሳ ሺህ እስራኤላውያን ወታደሮች ተገደሉ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦትም ተማረከ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስም ተገደሉ።
1 ሳሙኤል 4:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሳሙኤልም ቃል ወደ እስራኤል ሁሉ ደረሰ። በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ሊወጉ ወጡ፤ እነርሱ በአቤንኤዘር ሲሰፍሩ፥ ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በአፌቅ ሰፈሩ። ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመግጠም ሠራዊታቸውን አሰለፉ፤ ጦርነቱ እንደ ተፋፋመም፥ እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ተሸነፉ፤ በጦርነቱም ላይ አራት ሺህ ያህል እስራኤላውያን ተገደሉ። ሠራዊቱ ወደ ሰፈር በተመለሰ ጊዜ የእስራኤል አለቆች፥ “ዛሬ ጌታ በፍልስጥኤማውያን እንድንሸነፍ ያደረገን ለምንድን ነው? አብሮን እንዲወጣ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን የጌታን የኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ” አሉ። ስለዚህ ሕዝቡ ሰዎችን ወደ ሴሎ ልከው፥ በኪሩቤል መካከል በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን የሠራዊት ጌታን የኪዳን ታቦት አስመጡ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስ ከኪዳኑ ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ። የጌታ የኪዳኑ ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ፥ ምድር እስክትናወጥ ድረስ እስራኤላውያን ሁሉ ታላቅ የሆታ ድምፅ አሰሙ። ፍልስጥኤማውያንም ይህን ታላቅ የሆታ ድምፅ ሲሰሙ፥ “በዕብራውያን ሰፈር የምንሰማው ይህ ሁሉ የሆታ ድምፅ ምንድነው?” ሲሉ ጠየቁ። የጌታም ታቦት ወደ ሰፈር መምጣቱን በተረዱ ጊዜ፤ ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው እንዲህ አሉ፤ “አምላክ ወደ ሰፈሩ መጥቷል፤ ወዮልን! ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ዓይነት ነገር አጋጥሞን አያውቅም። ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? ግብፃውያንን በምድረ በዳ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ እነዚሁ አማልክት ናቸው፤ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ በርቱ! ወንድነታችሁም ይታይ፤ ያለዚያ ባርያ እንዳደረጋችኋቸው ሁሉ፥ ዕብራውያን እናንተን መልሰው ባርያ ያደርጓችኋል። ስለዚህ በወንድነት ጠንክራችሁ ተዋጉ!” ፍልስጥኤማውያንም ተዋጉ፤ እስራኤላውያንም ስለ ተሸነፉ እያንዳንዱ ወደየድንኳኑ ሸሸ። ታላቅ እልቂትም ሆነ፤ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኛ ወታድሮች ወደቁ። የእግዚአብሔር ታቦት ተማረከ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች ሖፍኒና ፊንሐስ ተገደሉ።