የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 4:1-11

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 4:1-11 አማ54

እስራኤልም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሊዋጉ ወጡ፥ በአቤንኤዘር አጠገብ ሰፈሩ፥ ፍልስጥኤማውያንም በአፌቅ ሰፈሩ። ፍልስጥኤማውያንም በእስራኤል ላይ ተሰለፉ፥ ሰልፋም በተመደበ ጊዜ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ፊት ተመቱ፥ ጦርነት በተደረገበትም ስፍራ ከእስራኤል አራት ሺህ የሚያህሉ ሰዎችን ገደሉ። ሕዝቡም ወደ ሰፈር በመጡ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች፦ ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ፊት ስለ ምን መታን? በመካከላችን እንዲሄድ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ አሉ። ሕዝቡም ወደ ሴሎ ላኩ፥ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጠውን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዚያ አመጡ፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፥ ምድሪቱም አስተጋባች። ፍልስጥኤማውያንም የእልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ፦ በዕብራውያን ሰፈር ያለው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምንድር ነው? አሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደገባ አስተዋሉ። ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው፥ እግዚአብሔር ወደ ሰፈር መጥቶአል አሉ። ደግሞም እንዲህ አሉ፦ ወዮልን፥ ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር አልሆነም። ወዮልን፥ ከእነዚህ ከኃያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነዚህ አማልክት ግብጻውያንን በምድረ በዳ በልዩ በልዩ መቅሠፍት የመቱ ናቸው። እናንተ ፍልስጥኤማውያን ሆይ፥ አይዞአችሁ፥ ጎብዙ፥ እናንተ ባሪያዎች እንዳደረጋችኋቸው ዕብራውያን ባሪያዎች እንዳያደርጉአችሁ ጎብዙ፥ ተዋጉ። ፍልስጥኤማውያንም ተዋጉ፥ እስራኤልም ተመቱ፥ ሁሉም እያንዳንዱ ወደ ድንኳናቸው ሸሹ፥ እጅግም ታላቅ ግድያ ሆነ፥ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ። የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ።