በእነዚያም ወራት እንዲህ ሆነ። ፍልስጥኤማውያን ለጦርነት በእስራኤላውያን ላይ ተሰበሰቡ። እስራኤልም ሊዋጉአቸው ወጡ፤ በአቤኔዜር አጠገብም ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንም በአፌቅ ሰፈሩ። ፍልስጥኤማውያንም እስራኤልን ለመውጋት ተሰለፉ፤ እስራኤልም ሸሹ፤ በፍልስጥኤማውያንም ፊት ድል ሆኑ፤ ጦርነት በተደረገበትም ስፍራ ከእስራኤል አራት ሺህ ሰዎች ተገደሉ። ሕዝቡም ወደ ሰፈር በተመለሱ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች፥ “ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ፊት ስለምን ጣለን? በፊታችን እንድትሄድ፥ ከጠላቶቻችንም እጅ እንድታድነን፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ” አሉ። ሕዝቡም ወደ ሴሎ ላኩ፤ በኪሩቤልም ላይ የሚቀመጠውን የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከዚያ አመጡ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባች ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፤ ምድሪቱም አስተጋባች። ፍልስጥኤማውያንም የእልልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ “በዕብራውያን ሰፈር ያለው ይህ ታላቅ የእልልታ ድምፅ ምንድን ነው?” አሉ። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደ ደረሰች አስተዋሉ። ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው፥ “አማልክት ወደ እነርሱ ወደ ሰፈር መጥተዋል” አሉ። ደግሞም እንዲህ አሉ፥ “ወዮልን! አቤቱ፥ ዛሬ አድነን፤ ከዚህ አስቀድሞ እንዲህ ያለ ነገር አልሆነምና። ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነዚህ አማልክት ግብፃውያንን በምድረ በዳ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ ናቸው። እናንተ ፍልስጥኤማውያን ሆይ! በርቱ፤ ጐብዙ፤ እናንተ ባሪያዎች እንዳደረጋችኋቸው ዕብራውያን ባሪያዎች እንዳያደርጓችሁ በርቱ፤ ተዋጉ።” ከዚህም በኋላ ተዋጉአቸው፤ እስራኤልም በፍልስጥኤማውያን ፊት ወደቁ፤ ሁሉም እያንዳንዳቸው ወደ ድንኳናቸው ሸሹ፤ እጅግም ታላቅ ግድያ ሆነ፤ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ። የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ።
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 4 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 4:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos