የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ሳሙኤል 25:23-38

1 ሳሙኤል 25:23-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አቤ​ግ​ያም ዳዊ​ትን ባየች ጊዜ ከአ​ህ​ያዋ ላይ ፈጥና ወረ​ደች፤ በዳ​ዊ​ትም ፊት በግ​ን​ባ​ርዋ ወደ​ቀች፤ ምድ​ርም ነክታ ሰገ​ደ​ች​ለት። በእ​ግ​ሩም ላይ ወደ​ቀች፤ እን​ዲ​ህም አለች፥ “ጌታዬ ሆይ! ይህ ኀጢ​ኣት በእኔ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪ​ያህ በጆ​ሮህ ልና​ገር፥ የባ​ሪ​ያ​ህ​ንም ቃል አድ​ምጥ። በዚህ ክፉ ሰው በና​ባል ላይ ጌታዬ ልቡን እን​ዳ​ይ​ጥል እለ​ም​ና​ለሁ፤ እንደ ስሙ እን​ዲሁ እርሱ ነው፤ ስሙ ናባል ነው፤ ስን​ፍ​ናም አድ​ሮ​በ​ታል፤ እኔ ባሪ​ያህ ግን አንተ የላ​ክ​ሃ​ቸ​ውን ብላ​ቴ​ኖ​ች​ህን አላ​የ​ሁም። አሁ​ንም ጌታዬ ሆይ! ሕያው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን! በሕ​ያው ነፍ​ስህ እም​ላ​ለሁ! ወደ ንጹሕ ደም እን​ዳ​ት​ገ​ባና፥ እጅ​ህን እን​ድ​ታ​ድን የከ​ለ​ከ​ለህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ነው፤ አሁ​ንም ጠላ​ቶ​ች​ህና በጌ​ታዬ ላይ ክፉ የሚሹ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ። አሁ​ንም ባሪ​ያህ ወደ ጌታዬ ያመ​ጣ​ች​ውን ይህን መተ​ያያ ተቀ​በል፤ በጌ​ታ​ዬም ዘንድ ለሚ​ቆሙ ሰዎች ስጣ​ቸው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለጌ​ታዬ የታ​መነ ቤትን ይሠ​ራ​ለ​ታ​ልና፥ የጌ​ታ​ዬ​ንም ጦር​ነት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይዋ​ጋ​ለ​ታ​ልና የእ​ኔን የባ​ሪ​ያ​ህን ኀጢ​ኣት፥ እባ​ክህ፥ ይቅር በል፤ በዘ​መ​ን​ህም ሁሉ ክፋት አይ​ገ​ኝ​ብ​ህም። የሚ​ያ​ሳ​ድ​ድ​ህና ነፍ​ስ​ህን የሚሻ ሰው ቢነሣ፥ የጌ​ታዬ ነፍስ በአ​ም​ላ​ክህ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ በሕ​ይ​ወት ማሰ​ሪያ የታ​ሰ​ረች ትሆ​ና​ለች፤ የጠ​ላ​ቶ​ችህ ነፍስ ግን በወ​ን​ጭፍ እን​ደ​ሚ​ወ​ነ​ጨፍ ትሁን። እን​ዲ​ህም ይሆ​ናል፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለጌ​ታዬ የተ​ና​ገ​ረ​ውን ቸር​ነት ሁሉ ያደ​ር​ግ​ል​ሃል፤ በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ላይ አለቃ አድ​ርጎ ይሾ​ም​ሃል፤ ይህ ርኵ​ሰ​ትና የልብ በደል፥ በከ​ንቱ ንጹሕ ደም ማፍ​ሰ​ስም ለጌ​ታዬ አይ​ሁ​ኑ​በት፤ የጌ​ታ​ዬም እጁ ትዳን፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ለጌ​ታዬ በጎ ያድ​ር​ግ​ለት፤ በጎም ታደ​ር​ግ​ላት ዘንድ ባሪ​ያ​ህን አስብ።” ዳዊ​ትም አቤ​ግ​ያን አላት፥ “ዛሬ እኔን ለመ​ገ​ና​ኘት አን​ቺን የላከ የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይመ​ስ​ገን። ጠባ​ይሽ የተ​ባ​ረከ ነው። ወደ ደም እን​ዳ​ል​ገባ፥ እጄ​ንም እን​ዳ​ድን ዛሬ የከ​ለ​ከ​ል​ሽኝ አን​ቺም የተ​ባ​ረ​ክሽ ነሽ። ነገር ግን ክፉ እን​ዳ​ላ​ደ​ር​ግ​ብሽ የከ​ለ​ከ​ለኝ የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ ሕያው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን! እኔን ለመ​ገ​ና​ኘት ፈጥ​ነሽ ባል​መ​ጣሽ ኖሮ፥ እስ​ኪ​ነጋ ድረስ ለና​ባል አጥር ተጠ​ግቶ የሚ​ሸን አንድ ስንኳ ባል​ቀ​ረ​ውም ብዬ ነበር።” ዳዊ​ትም ያመ​ጣ​ች​ውን ከእ​ጅዋ ተቀ​ብሎ፥ “በሰ​ላም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፥ ቃል​ሽን እንደ ሰማሁ፥ ፊት​ሽ​ንም እን​ዳ​ከ​በ​ርሁ ተመ​ል​ከቺ” አላት። አቤ​ግ​ያም ወደ ናባል መጣች፤ እነ​ሆም፥ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ ያደ​ርግ ነበር፤ ናባ​ልም እጅግ ሰክሮ ነበ​ርና ልቡ ደስ ብሎት ነበር፤ ስለ​ዚ​ህም እስ​ኪ​ነጋ ድረስ ታናሽ ነገር ወይም ታላቅ ነገር አል​ነ​ገ​ረ​ች​ውም ነበር። በነ​ጋ​ውም የወ​ይኑ ስካር ከና​ባል ባለፈ ጊዜ ሚስቱ ይህን ነገር ነገ​ረ​ችው፤ ልቡም በው​ስጡ ሞተ፤ እንደ ድን​ጋ​ይም ሆነ፤ ከዐ​ሥር ቀንም በኋላ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ናባ​ልን ቀሠ​ፈው፤ እር​ሱም ሞተ።

1 ሳሙኤል 25:23-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ወዲያው ከአህያዋ ወርዳ፣ በዳዊትም ፊት በግምባሯ ተደፍታ እጅ ነሣች። በእግሩም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በደሉ በእኔ ላይ ብቻ ይሁን፤ እባክህ አገልጋይህ ታናግርህ፤ የምትልህንም ስማ። ጌታዬ፣ ያን ባለጌ ሰው ናባልን ከቁም ነገር አይቍጠረው፤ ስሙ ራሱ ጅል ማለት ስለሆነ፣ ሰውየውም ልክ እንደ ስሙ ነው፤ ጅልነትም አብሮት የኖረ ነው። እኔ አገልጋይህ ግን ጌታዬ የላካቸውን ጕልማሶች አላየኋቸውም። ጌታዬ ሆይ፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ደም ከማፍሰስና በገዛ እጅህ ከመበቀል የጠበቀህ እግዚአብሔር ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና ጌታዬን ሊጐዱ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ፤ አገልጋይህም ለጌታዬ ያመጣችው ይህ ስጦታ አንተን ለሚከተሉ ጕልማሶች ይሰጥ። ጌታዬ የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለሚዋጋ እግዚአብሔርም ለጌታዬ ሥርወ መንግሥቱን በርግጥ ለዘላለም የሚያጸናለት በመሆኑ፣ እባክህ የእኔን የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህ። ማንም ሰው ሕይወትህን ለማጥፋት ቢያሳድድህ እንኳ፣ የጌታዬ ሕይወት በሕያዋን አንድነት እስራት ውስጥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ በሰላም ትጠበቃለች፤ የጠላቶችህን ሕይወት ግን፣ እንደ ወንጭፍ ድንጋይ ይወነጭፋል። እግዚአብሔር ለጌታዬ በሰጠው ተስፋ መሠረት በጎውን ነገር ሁሉ ባደረገለትና በእስራኤልም ላይ ባነገሠው ጊዜ፣ ጌታዬ የምታዝንበት ምክንያት ወይም የኅሊና ጸጸት አይኖርህም፤ በከንቱ ያፈሰስኸውም ደም ሆነ በገዛ እጅህ የተበቀልኸው የለምና። እግዚአብሔር በጎ ነገር ባደረገልህ ጊዜ እኔን አገልጋይህን ዐስበኝ።” ዳዊትም አቢግያን እንዲህ አላት፤ “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። ደም እንዳላፈስና በገዛ እጄ እንዳልበቀል ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። ጕዳት እንዳላደርስብሽ የጠበቀኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲህ በቶሎ መጥተሽ ባታገኚኝ ኖሮ፣ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ እንኳ ባልተረፈ ነበር።” ከዚያም ዳዊት ያመጣችለትን ከእጇ ተቀብሎ፣ “በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፤ ቃልሽን ሰምቻለሁ፤ የጠየቅሽኝንም ተቀብያአለሁ” አላት። አቢግያም ወደ ናባል በተመለሰች ጊዜ፣ እነሆ፤ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ትልቅ ግብዣ አድርጎ አገኘችው፤ ክፉኛም ሰክሮ ልቡ በደስታ ተሞልቶ ነበር። ስለዚህ እስኪነጋ ድረስ ምንም አልነገረችውም። ነግቶ የወይን ጠጁ ስካር ካለፈለት በኋላ የሆነውን ሁሉ ስትነግረው ልቡ ቀጥ አለ፤ ሰውነቱም እንደ ድንጋይ በድን ሆነ። ዐሥር ቀን ያህል ካለፈ በኋላ፣ እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፤ እርሱም ሞተ።

1 ሳሙኤል 25:23-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ከአህያዋ ላይ ፈጥና ወረደች፥ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ወደቀች፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣች። በእግሩም ላይ ወደቀች፥ እንዲህም አለች፦ ጌታዬ ሆይ፥ ይህ ኃጢአት በእኔ ላይ ይሁን፥ እኔ ባሪያህ በጆሮህ ልናገር፥ የባሪያህንም ቃል አድምጥ። በዚህ ምናምንቴ ሰው በናባል ላይ ጌታዬ ልቡን እንዳይጣል እለምናለሁ፥ እንደ ስሙ እንዲሁ እርሱ ነው፥ ስሙ ናባል ነው፥ ስንፍናም አድሮበታል፥ እኔ ባሪያህ ግን ከአንተ የተላኩትን የጌታዬን ጕልማሶች አላየሁም። አሁንም፥ ጌታዬ ሆይ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ! ወደ ደም እንዳትገባ፥ እጅህም ራስህን እንዳታድን የከለከለህ እግዚአብሔር ነው፥ አሁንም ጠላቶችህና በጌታዬ ላይ ክፉ የሚሹ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ። አሁንም ባሪያህ ወደ ጌታዬ ያመጣችው ይህ መተያያ ጌታዬን ለሚከተሉ ጕልማሶች ይሰጥ። የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለምትዋጋ እግዚአብሔር በእውነት ለጌታዬ የታመነ ቤት ይሠራልና የእኔን የባሪያህን ኃጢአት፥ እባክህ፥ ይቅር በል፥ በዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህም። ያሳድድህ ዘንድ ነፍስህንም ይሻ ዘንድ ሰው ቢነሣ፥ የጌታዬ ነፍስ በሕያዋን ወገን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የታሰረች ትሆናለች፥ የጠላቶችህንም ነፋስ ከወንጭፍ እንደሚጣል እንዲሁ ይጥላታል። እግዚአብሔርም ለጌታዬ የተናገረውን ቸርነት ሁሉ ባደረገልህ ጊዜ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ አድርጎ ባስነሣህ ጊዜ፥ አንተ በከንቱ ደም እንዳላፈሰስህ፥ በገዛ እጅህም እንዳልተሳካልህ ይህ ዕንቅፋትና የሕሊና ጸጸት በጌታዬ አይሆንልህም፥ እግዚአብሔርም ለጌታዬ በጎ ባደረገልህ ጊዜ፥ ባሪያህን አስብ። ዳዊትም አቢግያን አላት፦ ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። ወደ ደም እንዳልሄድ፥ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፥ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ። ነገር ግን ክፉ እንዳላደርግብሽ የከለከለኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔን ለመገናኘት ፈጥነሽ ባልመጣሽ ኖሮ፥ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ ስንኳ ባልቀረውም ነበር። ዳዊትም ያመጣችውን ከእጅዋ ተቀብሎ፦ በደኅና ወደ ቤትሽ ሂጂ፥ እነሆ፥ ቃልሽን ሰማሁ፥ ፊትሽንም አከበርሁ አላት። አቢግያም ወደ ናባል መጣች፥ እነሆም፥ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ ያደርግ ነበር፥ ናባልም እጅግ ሰክሮ ነበርና ልቡ ደስ ብሎት ነበር፥ ስለዚህም እስኪነጋ ድረስ ታናሽ ነገር ወይም ታላቅ ነገር አልነገረችውም ነበር። በነጋውም የጠጁ ስካር ከናባል ባለፈ ጊዜ ሚስቱ ይህን ነገር ነገረችው፥ ልቡም በውስጡ ሞተ፥ እንደ ድንጋይም ሆነ፥ ከአሥር ቀንም በኋላ እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፥ እርሱም ሞተ።

1 ሳሙኤል 25:23-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አቢጌልም ዳዊትን ባየችው ጊዜ በፍጥነት ከአህያዋ ወርዳ በዳዊት ጫማ አጠገብ መሬት ላይ ለጥ ብላ እጅ ነሣች፤ በጫማውም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ! እባክህ የእኔን የአገልጋይህን ቃል አድምጠኝ! በደሉን እኔ ልሸከም፤ የናባልን ጉዳይ ከቁም ነገር አታግባው! እርሱ ልክ እንድ አስሙ አጠራር ሞኝ ነው! ጌታዬ፥ የአንተ አገልጋዮች በመጡ ጊዜ እኔ በዚያ አልነበርኩም፤ የበቀል እርምጃ በመውሰድ ጠላቶችህን እንዳትገድል የጠበቀህ ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ እነሆ፥ እኔ አሁን በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ ጠላቶችህና አንተን ለመጒዳት የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ቅጣታቸውን ይቀበሉ፤ ጌታዬ ሆይ! እባክህ ይህ እኔ አገልጋይህ ያመጣሁልህን ስጦታ ተቀብለህ ለአገልጋዮችህ ይሁን። ጌታዬ፥ አንተ የእግዚአብሔርን ጦርነት እየተዋጋህ ነው፤ በምትኖርበትም ዘመን ሁሉ ምንም ዐይነት ክፉ ነገር ማድረግን ስለማትፈልግ ስለ ፈጸምኩት በደል እባክህ ይቅር በለኝ፤ እግዚአብሔር አንተንና ዘሮችህን ለዘለዓለም ያነግሣል፤ ማንም ሰው በአንተ ላይ አደጋ ጥሎ ሊገድልህ ቢፈልግ አንድ ሰው ውድ የሆነ ሀብቱን እንደሚጠብቅ አምላክህ እግዚአብሔር አንተን በሰላም ይጠብቅሃል፤ ስለ ጠላቶችህም የሆነ እንደ ሆነ አንድ ሰው ድንጋዩን ከወንጭፍ እንደሚያስፈነጥር እግዚአብሔር ራሱ አሽቀንጥሮ ይጥላቸዋል። እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት፥ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ባደረገልህና በእስራኤልም ላይ በሚያነግሥህ ጊዜ፥ ምንም ዐይነት ጸጸት ወይም የኅሊና ወቀሳ አይደርስብህም። ጌታዬ ሆይ፥ ያለ ምክንያት ወይም የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ብለህ የገደልከው ሰው የለም፤ ስለዚህ ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር በሚባርክህ ጊዜ እኔንም አትርሳኝ።” ዳዊትም እንዲህ አላት፤ “ከእኔ ጋር እንድትገናኚ አንቺን ወደ እኔ የላከ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! በዛሬው ቀን ደም ከማፍሰስና በቀልንም ከመበቀል የጠበቀኝ መልካም አስተሳሰብሽ የተባረከ ይሁን፤ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። በአንቺ ላይ ጒዳት ከማድረስ እግዚአብሔር ጠብቆኛል፤ ፈጥነሽ ወደ እኔ ባትመጪ ኖሮ ግን፥ ከናባል ወንዶች አንድ እንኳ ሳላስተርፍ ከንጋት በፊት ሁሉንም ለመግደል በሕያው እግዚአብሔር ስም ምዬ ነበር።” ከዚያም በኋላ ዳዊት ያመጣችለትን ስጦታ ተቀብሎ “ወደ ቤትሽ በሰላም ተመልሰሽ ሂጂ፤ ልመናሽን ሰምቼአለሁ፤ የጠየቅሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አላት። አቢጌልም እንደ ቤተ መንግሥት ግብር ታላቅ ግብዣ በማድረግ ላይ ወደነበረው ወደ ናባል ተመልሳ ሄደች፤ እርሱም ሰክሮ በደስታ ይፈነድቅ ስለ ነበር እስከ ማግስቱ ጧት ድረስ ምንም ቃል አልነገረችውም፤ በማግስቱም ስካሩ ከበረደለት በኋላ ሁሉንም ነገር አስረዳችው፤ ልቡም በድንጋጤ ስለ ተመታ እንደ ድንጋይ ሆነ። ከዐሥር ቀኖች በኋላም እግዚአብሔር ስለ ቀሠፈው ናባል ሞተ።

1 ሳሙኤል 25:23-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ወዲያው ከአህያዋ ወርዳ፥ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ተደፍታ እጅ ነሣች። በእግሩም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በደሉ በእኔ ላይ ብቻ ይሁን፤ እባክህ አገልጋይህ ታናግርህ፤ የምትልህንም ስማ። ጌታዬ፥ ያን ባለጌ ሰው ናባልን ከቁምነገር አይቁጠረው፤ ስሙ ራሱ ሞኝ ማለት ስለሆነ፥ ሰውየውም ልክ እንደ ስሙ ነው፤ ሞኝነትም አብሮት የኖረ ነው። እኔ አገልጋይህ ግን ጌታዬ የላካቸውን ጐልማሶች አላየኋቸውም። ጌታዬ ሆይ፤ በሕያው ጌታ፥ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ደም ከማፍሰስና በገዛ እጅህ ከመበቀል የጠበቀህ ጌታ ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና ጌታዬን ሊጐዱ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ፤ አገልጋይህም ለጌታዬ ያመጣችው ይህ ስጦታ አንተን ለሚከተሉ ጐልማሶች ይሰጥ። ጌታዬ የጌታን ጦርነት ስለሚዋጋ ጌታም ለጌታዬ የታመነ ቤት በእርግጥ ለዘለዓለም የሚያጸናለት በመሆኑ፥ እባክህ የእኔን የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህ። ማንም ሰው ሕይወትህን ለማጥፋት ቢያሳድድህ እንኳ፥ የጌታዬ ሕይወት በሕያዋን አንድነት እስራት ውስጥ በአምላክህ በጌታ ዘንድ በሰላም ትጠበቃለች፤ የጠላቶችህን ሕይወት ግን፥ እንደ ወንጭፍ ድንጋይ ይወነጭፋል። ጌታም በሰጠህ ተስፋ መሠረት፥ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ባደረገልህና በእስራኤልም ላይ በሚያነግሥህ ጊዜ፥ ጌታዬ የምታዝንበት ምክንያት ወይም የኅሊና ጸጸት አይኖርብህም፤ ምክንያቱም በከንቱ ያፈሰስከው ደም ወይም በገዛ እጅህ የወሰድከው በቀል የለምና። ስለዚህ ጌታ ለጌታዬ በጎ ነገር ባደረገልህ ጊዜም፥ እኔንም አገልጋይህን አስበኝ።” ዳዊትም አቢጌልን እንዲህ አላት፤ “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፥ የእስራኤል አምላክ ጌታ የተመሰገነ ይሁን! ደም እንዳላፈስና በገዛ እጄ እንዳልበቀል ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። ጉዳት እንዳላደርስብሽ የጠበቀኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው ጌታን! እንዲህ በቶሎ መጥተሽ ባታገኚኝ ኖሮ፥ እስኪ ነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ እንኳ ባልተረፈ ነበር።” ከዚያም ዳዊት ያመጣችለትን ከእጇ ተቀብሎ፥ “በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፤ ቃልሽን ሰምቻለሁ፤ የጠየቅሽኝንም ተቀብያአለሁ” አላት። አቢጌልም ወደ ናባል በተመለሰች ጊዜ፥ እነሆ፤ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ትልቅ ግብዣ አድርጎ አገኘችው፤ ክፉኛም ሰክሮ ልቡ በደስታ ተሞልቶ ነበር። ስለዚህ እስኪ ነጋ ድረስ ምንም አልነገረችውም። ነግቶ የወይን ጠጁ ስካር ካለፈለት በኋላ የሆነውን ሁሉ ስትነግረው ልቡ ቀጥ አለ፤ ሰውነቱም እንደ ድንጋይ በድን ሆነ። ዐሥር ቀን ያህል ካለፈ በኋላ፥ ጌታ ናባልን ቀሠፈው፤ እርሱም ሞተ።