አቤግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ከአህያዋ ላይ ፈጥና ወረደች፤ በዳዊትም ፊት በግንባርዋ ወደቀች፤ ምድርም ነክታ ሰገደችለት። በእግሩም ላይ ወደቀች፤ እንዲህም አለች፥ “ጌታዬ ሆይ! ይህ ኀጢኣት በእኔ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያህ በጆሮህ ልናገር፥ የባሪያህንም ቃል አድምጥ። በዚህ ክፉ ሰው በናባል ላይ ጌታዬ ልቡን እንዳይጥል እለምናለሁ፤ እንደ ስሙ እንዲሁ እርሱ ነው፤ ስሙ ናባል ነው፤ ስንፍናም አድሮበታል፤ እኔ ባሪያህ ግን አንተ የላክሃቸውን ብላቴኖችህን አላየሁም። አሁንም ጌታዬ ሆይ! ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ወደ ንጹሕ ደም እንዳትገባና፥ እጅህን እንድታድን የከለከለህ እግዚአብሔር ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና በጌታዬ ላይ ክፉ የሚሹ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ። አሁንም ባሪያህ ወደ ጌታዬ ያመጣችውን ይህን መተያያ ተቀበል፤ በጌታዬም ዘንድ ለሚቆሙ ሰዎች ስጣቸው። እግዚአብሔር ለጌታዬ የታመነ ቤትን ይሠራለታልና፥ የጌታዬንም ጦርነት እግዚአብሔር ይዋጋለታልና የእኔን የባሪያህን ኀጢኣት፥ እባክህ፥ ይቅር በል፤ በዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህም። የሚያሳድድህና ነፍስህን የሚሻ ሰው ቢነሣ፥ የጌታዬ ነፍስ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ በሕይወት ማሰሪያ የታሰረች ትሆናለች፤ የጠላቶችህ ነፍስ ግን በወንጭፍ እንደሚወነጨፍ ትሁን። እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር ለጌታዬ የተናገረውን ቸርነት ሁሉ ያደርግልሃል፤ በእስራኤልም ላይ አለቃ አድርጎ ይሾምሃል፤ ይህ ርኵሰትና የልብ በደል፥ በከንቱ ንጹሕ ደም ማፍሰስም ለጌታዬ አይሁኑበት፤ የጌታዬም እጁ ትዳን፤ እግዚአብሔርም ለጌታዬ በጎ ያድርግለት፤ በጎም ታደርግላት ዘንድ ባሪያህን አስብ።” ዳዊትም አቤግያን አላት፥ “ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የላከ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። ጠባይሽ የተባረከ ነው። ወደ ደም እንዳልገባ፥ እጄንም እንዳድን ዛሬ የከለከልሽኝ አንቺም የተባረክሽ ነሽ። ነገር ግን ክፉ እንዳላደርግብሽ የከለከለኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔን ለመገናኘት ፈጥነሽ ባልመጣሽ ኖሮ፥ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አጥር ተጠግቶ የሚሸን አንድ ስንኳ ባልቀረውም ብዬ ነበር።” ዳዊትም ያመጣችውን ከእጅዋ ተቀብሎ፥ “በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፥ ቃልሽን እንደ ሰማሁ፥ ፊትሽንም እንዳከበርሁ ተመልከቺ” አላት። አቤግያም ወደ ናባል መጣች፤ እነሆም፥ በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ ያደርግ ነበር፤ ናባልም እጅግ ሰክሮ ነበርና ልቡ ደስ ብሎት ነበር፤ ስለዚህም እስኪነጋ ድረስ ታናሽ ነገር ወይም ታላቅ ነገር አልነገረችውም ነበር። በነጋውም የወይኑ ስካር ከናባል ባለፈ ጊዜ ሚስቱ ይህን ነገር ነገረችው፤ ልቡም በውስጡ ሞተ፤ እንደ ድንጋይም ሆነ፤ ከዐሥር ቀንም በኋላ እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፤ እርሱም ሞተ።
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 25 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 25:23-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos