1 ሳሙኤል 21:10-15
1 ሳሙኤል 21:10-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዳዊትም ተነሣ በዚያም ቀን ከሳኦል ፊት ሸሸ፤ ወደ ጌትም ንጉሥ ወደ አንኩስ መጣ። የአንኩስ ብላቴኖችም፥ “ይህ ዳዊት የሀገሩ ንጉሥ አይደለምን? ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም ዐሥር ሺህ ገደለ ብለው ሴቶች በዘፈን የዘመሩለት እርሱ አይደለምን?” አሉት። ዳዊትም ይህን ቃል በልቡ አኖረ፤ የጌትንም ንጉሥ አንኩስን እጅግ ፈራ። በፊቱም መልኩን ለወጠ፤ በዚያችም ቀን አመለጠ። በከተማውም በር ከበሮ ይዞ በእጁ መታ፤ በበሩም መድረክ ላይ ተንፈራፈረ፤ ልጋጉም በጢሙ ላይ ይወርድ ነበር። አንኩስም ብላቴኖቹን፥ “እነሆ፥ ይህ ሰው እብድ እንደ ሆነ አይታችኋል፤ ለምን ወደ እኔ አመጣችሁት? በፊቴ ያብድ ዘንድ ይህን ያመጣችሁት እኔ የእብዶች አለቃ ነኝን? እንዲህ ያለውስ ወደ ቤቴ ይገባልን?” አላቸው።
1 ሳሙኤል 21:10-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያች ዕለት ዳዊት ከሳኦል ሸሽቶ ወደ ጌት ንጉሥ ወደ አንኩስ ሄደ። የአንኩስ አገልጋዮችም፣ “የምድሪቱ ንጉሥ ዳዊት ይህ አይደለምን? ደግሞስ፣ “ ‘ሳኦል ሺሕ ገደለ፤ ዳዊት ግን ዐሥር ሺሕ ገደለ’ ብለው በጭፈራቸው የዘፈኑለትስ እርሱ አይደለምን?” አሉት። ዳዊት ነገሩን በልቡ አኖረ፤ የጌትን ንጉሥ አንኩስንም እጅግ ፈራው። ስለዚህ በፊታቸው አእምሮውን እንደ ሳተ ሰው ሆነ፤ በያዙትም ጊዜ የከተማዪቱን ቅጥሮች እየቦጫጨረ፣ ልጋጉንም በጢሙ ላይ እያዝረበረበ እንደ እብድ ሆነ። አንኩስም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ “ሰውየውን እስቲ ተመልከቱት፤ እብድ እኮ ነው! ታዲያ ወደ እኔ ያመጣችሁት ለምንድን ነው? በፊቴ እንዲህ ይሆን ዘንድ ይህን ሰው እዚህ ያመጣችሁት እብድ ዐጥቼ ነውን? እንዲህ ያለውስ ሰው ወደ ቤቴ መግባት ይገባዋልን?”
1 ሳሙኤል 21:10-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳዊትም ተነሣ በዚያም ቀን ሳኦልን ፈርቶ ሸሸ፥ ወደ ጌትም ንጉሥ ወደ አንኩስ ሄደ። የአንኩስ ባሪያዎችም፦ ይህ ዳዊት የአገሩ ንጉሥ አይደለምን? ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ ብለው ሴቶች በዘፈን የዘመሩለት እርሱ አይደለምን? አሉት። ዳዊትም ይህን ቃል በልቡ አኖረ፥ የጌትንም ንጉሥ አንኩስን እጅግ ፈራ። በፊታቸውም አእምሮውን ለወጠ፥ በያዙትም ጊዜ እንደ እብድ ሆነ፥ በበሩም መድረክ ላይ ተንፈራፈረ፥ ልጋጉም በጢሙ ላይ ይወርድ ነበር። አንኩስም ባሪያዎቹን፦ እነሆ፥ ይህ ሰው እብድ እንደ ሆነ አይታችኋል፥ ለምን ወደ እኔ አመጣችሁት? በፊቴ ያብድ ዘንድ ይህን ያመጣችሁት እብድ ጠፍቶብኝ ነውን? እንዲህ ያለውስ ወደ ቤቴ ይገባልን? አላቸው።
1 ሳሙኤል 21:10-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዳዊትም ከሳኦል በመሸሽ አኪሽ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ጋት ንጉሥ ሄደ፤ የንጉሡ ባለሟሎች የሆኑት ባለሥልጣኖች “ይህ በአገሩ የነገሠው ዳዊት አይደለምን? ‘ሳኦል ሺህ ገዳይ! ዳዊት ዐሥር ሺህ ገዳይ!’ እያሉ ሴቶች በጭፍራ የዘፈኑለት እርሱ አይደለምን?” ሲሉ አኪሽን ጠየቁት። በእነርሱም አነጋገር የዳዊት ልብ በብርቱ ተነካ፤ ንጉሥ አኪሽንም በብርቱ ፈራ። በፊታቸው ጠባዩን ለወጠ፤ ከእነርሱ ጋር እያለም ራሱን እብድ አስመሰለ፤ በበሩ መዝጊያ ላይ ቧጠጠ፤ ለሐጩንም በጺሙ ላይ እንዲዝረከረክ አደረገ። አኪሽም ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖች “እነሆ! ይህ ሰው እብድ ነው! ታዲያ፥ ስለምን ወደ እኔ አመጣችሁት? በእኔ ዘንድ እንዲያብድ ወደ እኔ ይህን ሰው ያመጣችሁት፥ እኔ እብድ አጥቼ ነውን? ይህ ሰው ወደ ቤቴ መግባት አለበትን?” አላቸው።
1 ሳሙኤል 21:10-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያች ዕለት ዳዊት ከሳኦል ሸሽቶ ወደ ጋት ንጉሥ ወደ አኪሽ ሄደ። የአኪሽ አገልጋዮችም፥ “የምድሪቱ ንጉሥ ዳዊት ይህ አይደለምን? ደግሞስ ‘ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊት ዐሥር ሺህ ገደለ’ ብለው በጭፈራቸው የዘፈኑለትስ እርሱ አይደለምን?” አሉት። ዳዊት ነገሩን በልቡ አኖረ፤ የጋትን ንጉሥ አኪሽንም እጅግ ፈራው። ስለዚህ በፊታቸው አእምሮውን እንደሳተ ሰው ሆነ፤ በያዙትም ጊዜ የከተማዪቱን ቅጥሮች እየቦጫጨረ፥ ለሐጩንም በጢሙ ላይ እያዝረከረከ እንደ እብድ ሆነ። አኪሽም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ “ሰውየውን እስቲ ተመልከቱት፤ እብድ እኮ ነው! ታዲያ ወደ እኔ ያመጣችሁት ለምንድን ነው? በፊቴ እንዲህ ይሆን ዘንድ ይህን ሰው እዚህ ያመጣችሁት እብድ አጥቼ ነውን? እንዲህ ያለውስ ሰው ወደ ቤቴ መግባት ይገባዋልን?”