አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21
21
ዳዊት ከሳኦል ፊት ሸሽቶ መሄዱ
1ዳዊት በኖብ ወደሚገኘው ወደ ካህኑ አቤሜሌክ ዘንድ ሄደ፤ አቤሜሌክም በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ ሊቀበለው ወጥቶ “ማንም ሰው ሳይከተልህ ብቻህን ስለምን ወደዚህ መጣህ?” ሲል ጠየቀው። #ማቴ. 12፥3-4፤ ማር. 2፥25-26፤ ሉቃ. 6፥3።
2ዳዊትም ለካህኑ ለአቢሜሌክ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ እዚህ የመጣሁት የንጉሥ ሳኦልን ተልእኮ ለመፈጸም ነው፤ እኔ ወደዚህ የተላክሁበትን ጉዳይ ለማንም ሰው እንዳልገልጥ ንጉሡ አዞኛል፤ ተከታዮቼንም በአንድ ቦታ እንድንገናኝ አዝዣቸዋለሁ፤ 3ታዲያ አሁን ምን ምግብ ትሰጠኛለህ? አምስት እንጀራ ወይም ያለህን ሌላ ነገር ስጠኝ።”
4ካህኑም “ከተቀደሰው ኅብስት በቀር ሕዝብ የሚመገበው እንጀራ የለኝም፤ ተከታዮችህ በቅርቡ ከሴቶች ጋር ሳይገናኙ ተቈጥበው በንጽሕና የቈዩ ከሆኑ፥ ይህን ኅብስት መብላት ይችላሉ” ሲል መለሰለት።
5ዳዊትም ለካህኑ መልሶ “ከብላቴኖቼ ጋር ወደ ተልእኮ በምሄድበት ጊዜ ሁሉ ከሴቶች እንርቃለን፤ ተራ ተልእኮ እንኳ በምናደርግበት ጊዜ ብላቴኖቼ ንጽሕናቸውን ይጠብቃሉ። ዛሬማ ምንኛ የበለጠ ቅዱሳን መሆን ይገባቸዋል?”
6ስለዚህም ካህኑ የተቀደሰውን ኅብስት አንሥቶ ለዳዊት ሰጠው፤ ካህኑ ያለው ምግብ ለእግዚአብሔር መባ ሆኖ የቀረበው ኅብስት ብቻ ነበር፤ ይህም ኅብስት ከተቀደሰው ጠረጴዛ ላይ ተነሥቶ በሌላ አዲስ ኅብስት የተተካ ነበር። #ዘሌ. 24፥5-9።
7የሳኦል እረኞች አለቃ የሆነው ኤዶማዊው ዶይቅ በዚያኑ ቀን ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ለመፈጸም በዚያ ተገኝቶ ነበር።
8ዳዊትም አቤሜሌክን “የምትሰጠኝ ጦር ወይም ሰይፍ በአንተ ዘንድ ይገኛልን? የንጉሡ ትእዛዝ አስቸኳይ ስለ ሆነ ጦሬንም ሆነ ሌላውንም መሣሪያዬን ለመያዝ ጊዜ አላገኘሁም ነበር” አለው።
9አቤሜሌክም “በኤላ ሸለቆ የገደልከው የፍልስጥኤማዊው የጎልያድ ሰይፍ በእኔ ዘንድ አለ፤ እርሱም ከኤፉዱ በስተኋላ በጨርቅ ተጠቅሎ ተቀምጦአል፤ የምትፈልገው ከሆነ ውሰደው፤ በዚህ የሚገኝ የጦር መሣሪያ እርሱ ብቻ ነው” አለው። #1ሳሙ. 17፥51።
ዳዊትም “እርሱኑ ስጠኝ! ከእርሱ የተሻለ ሰይፍ የትም አይገኝም” አለው።
10ዳዊትም ከሳኦል በመሸሽ አኪሽ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ጋት ንጉሥ ሄደ፤ 11የንጉሡ ባለሟሎች የሆኑት ባለሥልጣኖች “ይህ በአገሩ የነገሠው ዳዊት አይደለምን? ‘ሳኦል ሺህ ገዳይ! ዳዊት ዐሥር ሺህ ገዳይ!’ እያሉ ሴቶች በጭፍራ የዘፈኑለት እርሱ አይደለምን?” ሲሉ አኪሽን ጠየቁት። #1ሳሙ. 18፥7፤ 29፥5።
12በእነርሱም አነጋገር የዳዊት ልብ በብርቱ ተነካ፤ ንጉሥ አኪሽንም በብርቱ ፈራ። #መዝ. 56። 13በፊታቸው ጠባዩን ለወጠ፤ ከእነርሱ ጋር እያለም ራሱን እብድ አስመሰለ፤ በበሩ መዝጊያ ላይ ቧጠጠ፤ ለሐጩንም በጺሙ ላይ እንዲዝረከረክ አደረገ። #መዝ. 34። 14አኪሽም ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖች “እነሆ! ይህ ሰው እብድ ነው! ታዲያ፥ ስለምን ወደ እኔ አመጣችሁት? 15በእኔ ዘንድ እንዲያብድ ወደ እኔ ይህን ሰው ያመጣችሁት፥ እኔ እብድ አጥቼ ነውን? ይህ ሰው ወደ ቤቴ መግባት አለበትን?” አላቸው።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997