የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ሳሙኤል 18:8-30

1 ሳሙኤል 18:8-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሳኦል እጅግ ተቈጣ፤ ይህም ነገር አላስደሰተውም። እርሱም፣ “ለዳዊት ዐሥር ሺሕ አሉለት፤ ለእኔ ግን ሺሕ ብቻ! እንግዲህ መንግሥት እንጂ ሌላ ምን ቀረው” አለ። ከዚያች ዕለት አንሥቶ ሳኦል ዳዊትን በቅናት ዐይን ይመለከተው ጀመር። በማግስቱም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በኀይል መጣበት፣ በዚህ ጊዜ ዳዊት ወትሮ እንደሚያደርገው ሁሉ በገና ሲደረድር፣ ሳኦል በቤቱ ሆኖ ትንቢት ይናገር ነበር። ሳኦል በእጁ ጦር ይዞ ነበር፤ እርሱም፣ “ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ” ብሎ በማሰብ ጦሩን ወረወረበት፤ ዳዊት ግን ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። እግዚአብሔር ከእርሱ ተለይቶ ከዳዊት ጋር ስለሆነ፣ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። ስለዚህ ዳዊትን ከአጠገቡ በማራቅ የሺሕ አለቃ አደረገው። ዳዊትም ሰራዊቱን እየመራ በፊታቸው ይወጣና ይገባ ነበር። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር። ሳኦልም፣ ዳዊት እንደ ተሳካለት ባየ ጊዜ ፈራው፤ መላው እስራኤልና ይሁዳ ግን ዳዊትን ወደዱት፤ በፊታቸው እየወጣና እየገባ የሚመራቸው እርሱ ነበርና። ሳኦል ዳዊትን፣ “ታላቋ ልጄ ሜሮብ እነኋት፤ እርሷን እድርልሃለሁ፤ አንተ ግን በጀግንነት አገልግለኝ፤ የእግዚአብሔርንም ጦርነቶች ተዋጋ” አለው፤ ሳኦል በልቡ፣ “ፍልስጥኤማውያን እጃቸውን ያንሡበት እንጂ እኔ በእርሱ ላይ እጄን አላነሣም” ብሎ ነበርና። ዳዊት ግን ሳኦልን፣ “የንጉሥ ዐማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ቤተ ሰቤም ሆነ የአባቴ ጐሣስ በእስራኤል ዘንድ ምንድን ነው?” አለው። ይሁን እንጂ የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤስድሪኤል ተዳረች። በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደችው፤ ሳኦልም ይህን ሲሰማ ደስ አለው። ሳኦልም በልቡ፣ “ወጥመድ እንድትሆነው፣ በፍልስጥኤማውያንም እጅ እንዲጠፋ እርሷን እድርለታለሁ” ሲል ዐሰበ። ስለዚህ ሳኦል ዳዊትን፣ “እነሆ፤ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ዐማቼ ትሆናለህ” አለው። ከዚያም ሳኦል ባለሟሎቹን፣ “ለዳዊት፣ ‘እነሆ፤ ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፤ ባለሟሎቹም ሁሉ ይወዱሃል፤ ስለዚህ ዐማቹ ሁንለት’ ብላችሁ በምስጢር ንገሩት” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም ይህንኑ ለዳዊት ደግመው ነገሩት፤ ዳዊት ግን “ለመሆኑ የንጉሥ አማች መሆንን እስከዚህ ትንሽ ነገር አድርጋችሁ ትቈጥራላችሁን? እኔ አንድ ምስኪን ድኻና እምብዛም የማልታወቅ ሰው ነኝ” አላቸው። የሳኦል ባለሟሎችም ዳዊት ያላቸውን በነገሩት ጊዜ፣ ሳኦል፣ “ዳዊትን፣ ‘ንጉሡስ ለልጂቱ ካንተ የሚፈልገው ጥሎሽ ጠላቶቹን ለመበቀል የመቶ ፍልስጥኤማውያንን ሸለፈት እንጂ ሌላ አይደለም ብላችሁ ንገሩት’ ” አላቸው። ሳኦል ይህን ያቀደው ዳዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲወድቅ ነበር። ባለሟሎቹ ይህን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ የንጉሥ ዐማች መሆኑ ደስ አሰኘው። ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ ከማለፉ በፊት፣ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎቹ ሄደው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤ ለንጉሡ ዐማች ይሆን ዘንድ፣ ሸለፈታቸውን አምጥቶ በቍጥራቸው ልክ ለንጉሡ አቀረበ፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ለዳዊት ዳረለት። ሳኦል እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደ ሆነና ልጁ ሜልኮልም እንደ ወደደችው በተረዳ ጊዜ፣ ሳኦል ከቀድሞው ይልቅ ፈራው፤ እስከ ዕድሜውም ፍጻሜ ድረስ ጠላቱ ሆነ። የፍልስጥኤማውያን ጦር አዛዦች እንደ ወትሮው ሁሉ፣ ለጦርነት ይወጡ ነበር፤ ዳዊትም ከቀሩት የሳኦል መኳንንት የበለጠ ድል አገኘ፤ ስሙም የታወቀ ሆነ።

1 ሳሙኤል 18:8-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሳኦ​ልም እጅግ ተቈጣ፤ ይህም ነገር ሳኦ​ልን አስ​ከ​ፋው፤ እር​ሱም፥ “ለዳ​ዊት ዐሥር ሺህ ሰጡት፤ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፤ ከመ​ን​ግ​ሥት በቀር ምን ቀረ​በት?” አለ። ከዚ​ያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊ​ትን ሁል​ጊዜ ይጠ​ባ​በ​ቀው ነበር። እን​ዲ​ህም ሆነ፤ በነ​ጋው ሳኦ​ልን ክፉ መን​ፈስ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ያዘው፤ በቤ​ቱም ውስጥ ትን​ቢት ተና​ገረ። ዳዊ​ትም በየ​ቀኑ ያደ​ርግ እንደ ነበረ በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦ​ልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። ሳኦ​ልም፥ “ዳዊ​ትን ከግ​ንቡ ጋር አጣ​ብቄ እመ​ታ​ዋ​ለሁ” ብሎ ጦሩን ወረ​ወረ። ዳዊ​ትም ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ከእ​ርሱ ጋር ስለ ነበረ፥ ከሳ​ኦ​ልም ስለ ተለየ ሳኦል ከዳ​ዊት ፊት የተ​ነሣ ፈራ። ስለ​ዚ​ህም ሳኦል ከእ​ርሱ አራ​ቀው፤ የሺህ አለ​ቃም አድ​ርጎ ሾመው፤ በሕ​ዝ​ቡም ፊት ይወ​ጣና ይገባ ነበር። ዳዊ​ትም በአ​ካ​ሄዱ ሁሉ ብል​ህና ዐዋቂ ነበር፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ከእ​ርሱ ጋር ነበረ። ሳኦ​ልም እጅግ ብልህ እንደ ሆነ አይቶ እጅግ ፈራው። ነገር ግን በፊ​ታ​ቸው ይወ​ጣና ይገባ ስለ​ነ​በረ እስ​ራ​ኤ​ልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊ​ትን ወደዱ። ሳኦ​ልም ዳዊ​ትን፥ “ታላ​ቂቱ ልጄ ሜሮብ እነ​ኋት፤ እር​ስ​ዋን እድ​ር​ል​ሃ​ለሁ፤ ብቻ ጀግና ልጅ ሁን​ልኝ፤ ስለ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ጦር​ነት ተጋ​ደል” አለው። ሳኦ​ልም፥ “የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን እጅ በእ​ርሱ ላይ ትሁን እንጂ የእኔ እጅ በእ​ርሱ ላይ አት​ሁን” ይል ነበር። ዳዊ​ትም ሳኦ​ልን፥ “ለን​ጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰው​ነ​ቴስ ምን​ድን ናት? የአ​ባ​ቴስ ወገን በእ​ስ​ራ​ኤል ዘንድ ምን​ድን ነው?” አለው። ነገር ግን የሳ​ኦል ልጅ ሜሮብ ዳዊ​ትን የም​ታ​ገ​ባ​በት ጊዜ ሲደ​ርስ ለሚ​ሆ​ላ​ዊው ለአ​ድ​ር​ኤል ተዳ​ረች። የሳ​ኦ​ልም ልጅ ሜል​ኮል ዳዊ​ትን ወደ​ደች፤ ይህም ወሬ ለሳ​ኦል ደረ​ሰ​ለት፤ ነገ​ሩም ደስ አሰ​ኘው። ሳኦ​ልም፥ “እር​ስ​ዋን እሰ​ጠ​ዋ​ለሁ፤ እር​ስ​ዋም እን​ቅ​ፋት ትሆ​ን​በ​ታ​ለች” አለ። እነ​ሆም፥ የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን እጅ በሳ​ኦል ላይ ነበ​ረች። ሳኦ​ልም ብላ​ቴ​ኖ​ቹን፥ “እነሆ፥ ንጉሥ እጅግ ወድ​ዶ​ሃል፤ ቤተ ሰቡም ሁሉ ወድ​ደ​ው​ሃል፤ አሁ​ንም ለን​ጉሥ አማች ሁን ብላ​ችሁ በስ​ውር ለዳ​ዊት ንገ​ሩት” ብሎ አዘ​ዛ​ቸው። የሳ​ኦ​ልም ብላ​ቴ​ኖች ይህን ቃል በዳ​ዊት ጆሮ ተና​ገሩ፤ ዳዊ​ትም፥ “እኔ የተ​ዋ​ረ​ድ​ሁና ክብር የሌ​ለኝ ሰው ስሆን ለን​ጉሥ አማች እሆን ዘንድ ለእ​ና​ንተ ትንሽ ነገር ይመ​ስ​ላ​ች​ኋ​ልን?” አለ። የሳ​ኦ​ልም ብላ​ቴ​ኖች፦ ዳዊት እን​ዲህ ብሎ ተና​ገረ ብለው ነገ​ሩት። ሳኦ​ልም አላ​ቸው፥ “የን​ጉ​ሥን ጠላ​ቶች ይበ​ቀል ዘንድ ከመቶ ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን ሸለ​ፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይ​ሻም ብላ​ችሁ ለዳ​ዊት ንገ​ሩት” አላ​ቸው። ሳኦል ግን ይህን ማለቱ በፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን እጅ ይጥ​ለው ዘንድ አስቦ ነው። የሳ​ኦ​ልም ብላ​ቴ​ኖች ይህን ቃል ለዳ​ዊት ነገ​ሩት፤ ለን​ጉ​ሥም አማች ይሆን ዘንድ ዳዊ​ትን ደስ አሰ​ኘው። ዳዊ​ትና ሰዎ​ቹም ተነ​ሥ​ተው ሄዱ፤ ከፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም ሁለት መቶ ሰዎ​ችን ገደሉ፤ ዳዊ​ትም ለን​ጉሥ አማች ይሆን ዘንድ ሰለ​ባ​ቸ​ውን አም​ጥቶ በቍ​ጥ​ራ​ቸው ልክ ለን​ጉሡ ሰጠ። ሳኦ​ልም ልጁን ሜል​ኮ​ልን ዳረ​ለት። ሳኦ​ልም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከዳ​ዊት ጋር እንደ ሆነ አየ፤ እስ​ራ​ኤ​ልም ሁሉ ወደ​ዱት። ሳኦ​ልም ዳዊ​ትን አጥ​ብቆ ፈራው፤ ሳኦ​ልም ዕድ​ሜ​ውን ሁሉ ለዳ​ዊት ጠላት ሆነ። የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያ​ንም አለ​ቆች ይወጡ ነበር፤ በወ​ጡም ጊዜ ሁሉ ከሳ​ኦል አገ​ል​ጋ​ዮች ሁሉ ይልቅ ዳዊት አስ​ተ​ውሎ ያደ​ርግ ነበ​ርና ስሙ እጅግ ተጠ​ርቶ ነበር።

1 ሳሙኤል 18:8-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሳኦልም እጅግ ተቆጣ፥ ይህም ነገር አስከፋው፥ እርሱም፦ ለዳዊት እልፍ ሰጡት፥ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፥ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረበት? አለ። ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ተመቅኝቶ ተመለከተው። በነጋውም ሳኦልን ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው፥ በቤቱም ውስጥ ትንቢት ተናገረ። ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ እንደ ነበረ በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። ሳኦልም፦ ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ ብሎ ጦሩን ወረወረ። ዳዊትም ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። ስለዚህም ሳኦል ከእርሱ አራቀው፥ የሺህ አለቃም አደረገው፥ በሕዝቡም ፊት ይወጣና ይገባ ነበር። ዳዊትም በአካሄዱ ሁሉ አስተውሎ ያደርግ ነበር፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ። ሳኦልም እጅግ ብልህ እንደ ሆነ አይቶ እጅግ ፈራው። ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለ ነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱ። ሳኦልም ዳዊትን፦ ታላቂቱ ልጄ ሜሮብ እነኋት፥ እርስዋን እድርልሃለሁ፥ ብቻ ቀልጣፋ ልጅ ሁንልኝ፥ ስለ እግዚአብሔርም ጦርነት ተጋደል አለው። ሳኦልም፦ የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ ትሁን እንጂ የእኔ እጅ በእርሱ ላይ አትሁን ይል ነበር። ዳዊትም ሳኦልን፦ ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ ምንድር ናት? የአባቴስ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድር ነው? አለው። ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜሮብ ዳዊትን የምታገባበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤስድሪኤል ተዳረች። የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደች፥ ይህም ወሬ ለሳኦል ደረሰለት፥ ነገሩም ደስ አሰኘው። ሳኦልም፦ ወጥመድ ትሆነው ዘንድ፥ የፍልስጥኤማውያንም እጅ በእርሱ ላይ ትሆን ዘንድ እርስዋን እድርለታለሁ አለ፥ ሳኦልም ዳዊትን፦ ዛሬ ሁለተኛ አማች ትሆነኛለህ አለው። ሳኦልም ባሪያዎቹን፦ እነሆ ንጉሥ እጅግ ወድዶሃል፥ ባሪያዎቹም ሁሉ ወድደውሃል፥ አሁንም ለንጉሥ አማች ሁን ብላችሁ በስውር ለዳዊት ንገሩት ብሎ አዘዛቸው። የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል በዳዊት ጆሮ ተናገሩ፥ ዳዊትም፦ እኔ ድሀ የተጠቃሁም ሰው ስሆን ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ ለእናንተ ትንሽ ነገር ይመስላችኋልን? አለ። የሳኦልም ባሪያዎች፦ ዳዊት እንዲህ ብሎ ተናገረ ብለው ነገሩት። ሳኦልም ዳዊትን በፍልስጥኤማውያን እጅ ይጥለው ዘንድ አስቦ፦ የንጉሥን ጠላቶች ይበቀል ዘንድ ከመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይሻም ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት አላቸው። የሳኦልም ባሪያዎች ይህን ቃል ለዳዊት ነገሩት፥ ለንጉሥም አማች ይሆን ዘንድ ዳዊትን ደስ አሰኘው። ዳዊትና ሰዎቹም ተነሥተው ሄዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም መቶ ሰዎች ገደሉ፥ ዳዊትም ለንጉሥ አማች ይሆን ዘንድ ሰለባቸውን አምጥቶ በቁጥራቸው ልክ ለንጉሡ ሰጠ። ሳኦልም ልጁን ሜልኮልን ዳረለት። ሳኦልም እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደ ሆነ አየ፥ እስራኤልም ሁሉ ወደዱት። ሳኦልም ዳዊትን አጥብቆ ፈራው፥ ሳኦልም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ። የፍልስጥኤማውያንም አለቆች ይወጡ ነበር፥ በወጡም ጊዜ ሁሉ ከሳኦል ባሪያዎች ሁሉ ይልቅ ዳዊት አስተውሎ ያደርግ ነበርና ስሙ እጅግ ተጠርቶ ነበር።

1 ሳሙኤል 18:8-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሳኦል ይህ አባባል ደስ ስላላሰኘው በጣም ተቈጥቶ “ለዳዊት ዐሥር ሺህ፥ ለእኔ ግን አንድ ሺህ ብቻ ሰጡ፤ እንግዲህ ከመንገሥ በቀር ምን ቀረው!” አለ። ከዚህም የተነሣ ከዚያን ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ ቅናትና ጥርጣሬ አደረበት። በማግስቱም በድንገት ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ሳኦልን ተቈራኘው፤ በቤቱም ውስጥ እንደ እብድ ይለፈልፍ ነበር፤ ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ በነበረው ዐይነት ለሳኦል በገና ይደረድርለት ነበር፤ ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። “መትቼ ከግድግዳ ጋር አጣብቀዋለሁ!” ብሎ በልቡ አሰበ፤ ከዚህም በኋላ ጦሩን በዳዊት ላይ ሁለት ጊዜ ወረወረ፤ ዳዊት ግን ሁለቴም ዞር እያለ አመለጠ። እግዚአብሔር እርሱን ትቶ ከዳዊት ጋር ስለ ነበረ ሳኦል ዳዊትን ፈራው፤ ከዚህም የተነሣ ሳኦል ዳዊትን ከፊቱ ለማራቅ የሺህ ወታደሮች አዛዥ አድርጎ ላከው፤ ዳዊትም ወታደሮቹን ወደ ጦርነት መራ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር። ሳኦልም የዳዊትን ተልእኮ መሳካት እየተመለከተ በይበልጥ ይፈራው ጀመር፤ ነገር ግን ተልእኮው የሚሳካለት መሪ በመሆኑ በእስራኤልም ሆነ በይሁዳ የሚገኝ ሕዝብ ሁሉ ዳዊትን ይወድ ነበር፤ ከዚህ በኋላ ሳኦል ዳዊትን እንዲህ አለው፥ “የእግዚአብሔርን ጦርነት በጀግንነት ብትዋጋ ታላቅዋን ልጄን ሜራብን እድርልሃለሁ፤” ሳኦል ይህን ያለበት ምክንያት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲሞት እንጂ እርሱ ዳዊትን ለመግደል ስላልፈለገ ነው። ዳዊትም “የንጉሥ ዐማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ቤተሰቤስ በእስራኤል መካከል እምን ቊጥር ይገባል?” ሲል መለሰለት። ነገር ግን ሜራብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ከመሖላ ለመጣውና ዓድሪኤል ተብሎ ለሚጠራ ለአንድ ሌላ ሰው ተዳረች። ይሁን እንጂ ሜልኮል ተብላ የምትጠራው የሳኦል ልጅ ዳዊትን ወደደች፤ ሳኦልም ይህን በሰማ ጊዜ ደስ አለው፤ በልቡም “ሜልኮልን ለዳዊት እሰጣለሁ፤ እርስዋም ዳዊትን እንድታጠምድልኝ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ በፍልስጥኤማውያን እጅ ይገደላል” ሲል አሰበ። ስለዚህም ሳኦል ለሁለተኛ ጊዜ ዳዊትን ጠርቶ “አሁን የእኔ ዐማች ትሆናለህ” አለው። ባለሟሎቹንም ጠርቶ “ንጉሡ በአንተ ተደስቶአል፤ የእርሱ ባለሟሎች የሆኑት ባለሥልጣኖቹም ይወዱሃል፤ ስለዚህ የእርሱን ልጅ ታገባ ዘንድ አሁን ጥሩ ጊዜ ገጥሞሃል” ብለው ለዳዊት በግል እንዲነግሩት አዘዘ። ስለዚህ የሳኦል ባለሟሎች ይህን ጉዳይ ለዳዊት በምሥጢር ነገሩት፤ እርሱም፦ “እንደእኔ ላለ ዝቅተኛ ድኻ ሰው የንጉሥ ዐማች መሆን ቀላል ይመስላችኋልን?” አላቸው። ባለሟሎቹም ከዳዊት ያገኙትን መልስ ለሳኦል ነገሩት፤ ሳኦልም እንደ ገና “ንጉሡ ስለ ልጁ ከአንተ የሚፈልገው ጥሎሽ ጠላቶቹን መበቀል እንዲችል አንድ መቶ ፍልስጥኤማውያን ገድለህ ሸለፈታቸውን እንድታመጣለት ብቻ ነው” ብላችሁ ንገሩት ሲል ባለሟሎቹን አዘዘ። ሳኦል ይህን ያደረገበት ምክንያት ዳዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲገደልለት በማቀድ ነበር። የሳኦል ባለሟሎችም ይህንኑ ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም የንጉሡ ዐማች እንዲሆን በመታሰቡ ደስ አለው። የሠርጉም ቀን ከመድረሱ በፊት፥ ዳዊትና ወታደሮቹ ዘምተው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤ ዳዊትም የንጉሥ ዐማች መሆን ይችል ዘንድ ሸለፈታቸውን ወደ ንጉሡ በመውሰድ ቈጥሮ አስረከበ። ስለዚህም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ለዳዊት ዳረለት። ሳኦል እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር መሆኑንና ልጁም ሜልኮል እርሱን እንደ ወደደችው አረጋገጠ። ስለዚህም ሳኦል ዳዊትን ይበልጥ ከመፍራቱ የተነሣ በኖረበት ዘመን ሁሉ የዳዊት ጠላት ሆነ። የፍልስጥኤማውያን ወታደሮች በየጊዜው እየመጡ ጦርነት ያደርጉ ነበር፤ ይሁን እንጂ በማናቸውም ጦርነት ሁሉ ከሳኦል የጦር መኰንኖች ይበልጥ ድል የሚሳካለት ለዳዊት ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ዳዊት እጅግ ዝነኛ ሆነ።

1 ሳሙኤል 18:8-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሳኦል እጅግ ተቆጣ፤ ይህም ነገር አላስደሰተውም። እርሱም፥ “ለዳዊት ዐሥር ሺህ አሉለት፤ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ! እንግዲህ መንግሥት እንጂ ሌላ ምን ቀረው!” አለ። ከዚያች ዕለት አንሥቶ ሳኦል ዳዊትን በቅናት ዐይን ይመለከተው ጀመር። በማግስቱም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ክፉ መንፈስ ሳኦልን ተቆራኘው፥ ሳኦል በቤቱ ሆኖ እንደ እብድ ይለፈልፍ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ዳዊት በየእለቱ እንደሚያደርገው ሁሉ በገና ሲደረድር ነበር። ሳኦል በእጁ ጦር ይዞ ነበር። እርሱም፥ “ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ” ብሎ በማሰብ ጦሩን ወረወረበት፤ ዳዊት ግን ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። ጌታ ከእርሱ ተለይቶ ከዳዊት ጋር ስለሆነ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። ስለዚህ ዳዊትን ከአጠገቡ በማራቅ የሺህ አለቃ አደረገው። ዳዊትም ሠራዊቱን እየመራ በፊታቸው ይወጣና ይገባ ነበር። ጌታም ከእርሱ ጋር ስለ ነበር የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር። ሳኦልም፥ ዳዊት እንደ ተሳካለት ባየ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈራው፤ መላው እስራኤልና ይሁዳ ግን በፊታቸው እየወጣና እየገባ የሚመራቸው እርሱ ነበርና ዳዊትን ወደዱት። ሳኦል ዳዊትን፥ “ታላቋ ልጄ ሜራብ እነኋት፤ እርሷን እድርልሃለሁ፤ አንተ ግን በጀግንነት አገልግለኝ፤ የጌታንም ጦርነቶች ተዋጋልኝ” አለው፤ ሳኦል በልቡ፥ “ፍልስጥኤማውያን እጃቸውን ያንሡበት እንጂ እኔ በእርሱ ላይ እጄን አላነሣም” ብሎ ነበር። ዳዊት ግን ሳኦልን፥ “የንጉሥ ዐማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ቤተሰቤም ሆነ የአባቴ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድነው?” አለው። ይሁን እንጂ የሳኦል ልጅ ሜራብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤድሪኤል ተዳረች። በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደችው፤ ሳኦልም ይህን ሲሰማ ደስ አለው። ሳኦልም በልቡ፥ “ወጥመድ እንድትሆነው፥ በፍልስጥኤማውያንም እጅ እንዲጠፋ እርሷን እድርለታለሁ” ሲል አሰበ። ስለዚህ ሳኦል ለሁለተኛ ጊዜ ዳዊትን፥ “እነሆ፤ ዛሬ ዐማቼ ትሆናለህ” አለው። ከዚያም ሳኦል ባለሟሎቹን፥ “ለዳዊት፥ ‘እነሆ፤ ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፤ ባለሟሎቹም ሁሉ ይወዱሃል፤ ስለዚህ ዐማቹ ሁንለት’ ብላችሁ በምስጢር ንገሩት” ብሎ አዘዛቸው። እነርሱም ይህንኑ ለዳዊት ደግመው ነገሩት፤ ዳዊት ግን “ለመሆኑ የንጉሥ ዐማች መሆንን እስከዚህ ትንሽ ነገር አድርጋችሁ ትቆጥራላችሁን? እኔ አንድ ምስኪን ድኻና እውቅና የሌለኝ መሆኔን አጣችሁትን?” አላቸው። የሳኦል ባለሟሎችም ዳዊት ያላቸውን ነገሩት። ሳኦልም፥ “ዳዊትን፥ ‘ንጉሡም ለልጅቱ ካንተ የሚፈልገው ጥሎሽ ጠላቶቹን ለመበቀል የመቶ ፍልስጥኤማውያንን ሸለፈት እንጂ ሌላ አይደለም ብላችሁ ንገሩት’ ” አላቸው። ሳኦል ይህን ያቀደው ዳዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲወድቅ ነበር። ባለሟሎቹ ይህን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ የንጉሥ ዐማች መሆኑ ደስ አሰኘው። ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ ከማለፉ በፊት፥ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎቹ ሄደው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤ ለንጉሡ ዐማች ይሆን ዘንድ፥ ሸለፈታቸውን አምጥቶ በቁጥራቸው ልክ ለንጉሡ አቀረበ፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ለዳዊት ዳረለት። ሳኦል፥ ጌታ ከዳዊት ጋር እንደ ሆነና ልጁ ሜልኮልም እንደወደደችው በተረዳ ጊዜ፥ ሳኦል ከቀድሞው ይልቅ ዳዊትን ፈራው፤ እስከ ዕድሜ ልኩም ጠላቱ ሆነ። የፍልስጥኤማውያን ጦር አዛዦች እንደ ወትሮው ሁሉ ለጦርነት ይወጡ ነበር፤ ዳዊትም ከቀሩት የሳኦል መኳንንት የበለጠ ድል አገኘ፤ ስሙም እጅግ የታወቀ ሆነ።