ሳኦልም እጅግ ተቈጣ፤ ይህም ነገር ሳኦልን አስከፋው፤ እርሱም፥ “ለዳዊት ዐሥር ሺህ ሰጡት፤ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፤ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረበት?” አለ። ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ሁልጊዜ ይጠባበቀው ነበር። እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሳኦልን ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው፤ በቤቱም ውስጥ ትንቢት ተናገረ። ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ እንደ ነበረ በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። ሳኦልም፥ “ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ” ብሎ ጦሩን ወረወረ። ዳዊትም ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ፥ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ከዳዊት ፊት የተነሣ ፈራ። ስለዚህም ሳኦል ከእርሱ አራቀው፤ የሺህ አለቃም አድርጎ ሾመው፤ በሕዝቡም ፊት ይወጣና ይገባ ነበር። ዳዊትም በአካሄዱ ሁሉ ብልህና ዐዋቂ ነበር፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ። ሳኦልም እጅግ ብልህ እንደ ሆነ አይቶ እጅግ ፈራው። ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱ። ሳኦልም ዳዊትን፥ “ታላቂቱ ልጄ ሜሮብ እነኋት፤ እርስዋን እድርልሃለሁ፤ ብቻ ጀግና ልጅ ሁንልኝ፤ ስለ እግዚአብሔርም ጦርነት ተጋደል” አለው። ሳኦልም፥ “የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ ትሁን እንጂ የእኔ እጅ በእርሱ ላይ አትሁን” ይል ነበር። ዳዊትም ሳኦልን፥ “ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ ምንድን ናት? የአባቴስ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድን ነው?” አለው። ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜሮብ ዳዊትን የምታገባበት ጊዜ ሲደርስ ለሚሆላዊው ለአድርኤል ተዳረች። የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደች፤ ይህም ወሬ ለሳኦል ደረሰለት፤ ነገሩም ደስ አሰኘው። ሳኦልም፥ “እርስዋን እሰጠዋለሁ፤ እርስዋም እንቅፋት ትሆንበታለች” አለ። እነሆም፥ የፍልስጥኤማውያን እጅ በሳኦል ላይ ነበረች። ሳኦልም ብላቴኖቹን፥ “እነሆ፥ ንጉሥ እጅግ ወድዶሃል፤ ቤተ ሰቡም ሁሉ ወድደውሃል፤ አሁንም ለንጉሥ አማች ሁን ብላችሁ በስውር ለዳዊት ንገሩት” ብሎ አዘዛቸው። የሳኦልም ብላቴኖች ይህን ቃል በዳዊት ጆሮ ተናገሩ፤ ዳዊትም፥ “እኔ የተዋረድሁና ክብር የሌለኝ ሰው ስሆን ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ ለእናንተ ትንሽ ነገር ይመስላችኋልን?” አለ። የሳኦልም ብላቴኖች፦ ዳዊት እንዲህ ብሎ ተናገረ ብለው ነገሩት። ሳኦልም አላቸው፥ “የንጉሥን ጠላቶች ይበቀል ዘንድ ከመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይሻም ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት” አላቸው። ሳኦል ግን ይህን ማለቱ በፍልስጥኤማውያን እጅ ይጥለው ዘንድ አስቦ ነው። የሳኦልም ብላቴኖች ይህን ቃል ለዳዊት ነገሩት፤ ለንጉሥም አማች ይሆን ዘንድ ዳዊትን ደስ አሰኘው። ዳዊትና ሰዎቹም ተነሥተው ሄዱ፤ ከፍልስጥኤማውያንም ሁለት መቶ ሰዎችን ገደሉ፤ ዳዊትም ለንጉሥ አማች ይሆን ዘንድ ሰለባቸውን አምጥቶ በቍጥራቸው ልክ ለንጉሡ ሰጠ። ሳኦልም ልጁን ሜልኮልን ዳረለት። ሳኦልም እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደ ሆነ አየ፤ እስራኤልም ሁሉ ወደዱት። ሳኦልም ዳዊትን አጥብቆ ፈራው፤ ሳኦልም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ። የፍልስጥኤማውያንም አለቆች ይወጡ ነበር፤ በወጡም ጊዜ ሁሉ ከሳኦል አገልጋዮች ሁሉ ይልቅ ዳዊት አስተውሎ ያደርግ ነበርና ስሙ እጅግ ተጠርቶ ነበር።
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 18 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 18:8-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos