1 ነገሥት 22:13-53
1 ነገሥት 22:13-53 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ፥ “እነሆ፥ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ” አለው። ሚክያስም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ” አለ። ወደ ንጉሡም ደረሰ። ንጉሡም፥ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር?” አለው። እርሱም፥ “ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም፥ “በእግዚአብሔር ስም እውነት ትነግረኝ ዘንድ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። እርሱም አለ፥ “እንዲህ አይደለም፤ እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም አለ፦ እግዚአብሔር የእነዚህ አምላክ አይደለምን? እያንዳንዱ በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ።” የእስራኤልም ንጉሥ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥን፥ “ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁምን?” አለው። ሚክያስም አለ፥ “እንዲህ አይደለም፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሰማሁት እኔ አይደለሁምን? እንዲህ አይደለም፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። እግዚአብሔርም፦ ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው? አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ ያለ ነገር ተናገረ። መንፈስም ወጣ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ፦ እኔ አስተዋለሁ አለ። እግዚአብሔርም፦ በምን ታስተዋለህ? አለው፤ እርሱም ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም፦ ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፤ ይሆንልሃልም፤ ውጣ፤ እንዲሁም አድርግ አለ። አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል።” የከሓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም ጕንጩን በጥፊ መታውና፥ “ምን ዓይነት የእግዚአብሔር መንፈስ ነው የተናገረህ?” አለው። ሚክያስም፥ “እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ ውስጠኛው እልፍኝህ በሄድህ ጊዜ ታያለህ” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ፥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማዪቱም ሹም ወደ አሞን ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ፦ ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉአቸው” አለ። ሚክያስም፥ “በሰላም ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም” አለ። ደግሞም አሕዛብ ሁሉ ሆይ! ስሙኝ” አለ። የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ዘመቱ። የእስራኤልም ንጉሥ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን የእኔን ልብስ ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ወደ ሰልፍ ገባ። የሶርያም ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሰረገሎች አለቆች፥ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፥ ታናሽ ቢሆን ወይም ታላቅ ከማናቸውም ጋር አትዋጉ” ብሎ አዝዞ ነበር። የሰረገሎች አለቆችም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፥ “በእውነት የእስራኤልን ንጉሥ ይመስላል፤” አሉ ይዋጉትም ዘንድ ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም ጮኸ። የሰረገሎች አለቆችም የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። አንድ ሰውም ቀስቱን ድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በሳንባውና በደረቱ መካከል ወጋው፤ ሰረገለኛውንም፥ “መልሰህ ንዳ፤ ተወግቻለሁና ከሰልፍ ውስጥ አውጣኝ” አለው። በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ ንጉሡም ከጥዋት እስከ ማታ በሶርያውያን ፊት በሰረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ የቍስሉም ደም በሰረገላው ውስጥ ፈሰሰ፤ ማታም ሞተ። ፀሐይም በገባች ጊዜ አዋጅ ነጋሪው ወጥቶ፥ “ንጉሡ ሞቶአልና እያንዳንዱ ወደ ከተማው፥ እያንዳንዱም ወደ ሀገሩ ይሂድ” ብሎ አዋጅ ነገረ። ወደ ሰማርያም መጡ፤ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት፤ ሰረገላውንም በሰማርያ ምንጭ አጠቡት። እግዚአብሔርም በነቢዩ አድሮ እንደ ተናገረ ውሾችና ጅቦች ደሙን ላሱት። አመንዝሮች ሴቶችም በደሙ ታጠቡበት። የቀረውም የአክዓብ ነገር፥ ያደረገውም ነገር ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የሠራው ቤት፥ የሠራቸውም ከተሞች ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አካዝያስ ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ። ኢዮሣፍጥም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ አምስት ዓመት ጎበዝ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ አምስት ዓመት ነገሠ። እናቱም ዓዙባ የተባለች የሴሜይ ልጅ ነበረች። በአባቱም በአሳ መንገድ ሁሉ ሄደ፤ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን አደረገ፤ ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉትን መስገጃዎችን አላራቀም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ታረቀ። የቀረውም የኢዮሣፍጥ ነገር፥ ኀይሉም፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። ከአባቱም ከአሳ ዘመን የቀረውን ርኩስ ሥራ ከምድር አጠፋ። በኤዶምያስም ንጉሥ አልነበረም፤ ሹሙም እንደ ንጉሥ ነበረ። ኢዮሣፍጥም ወደ ኦፌር ሄደው ወርቅ ያመጡ ዘንድ በተርሴስ መርከብን ሠራ፤ ነገር ግን መርከቢቱ በጋሴዎንጋቤር ተሰብራለችና አልሄደችም። የአክዓብም ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን፥ “አገልጋዮችህ ከአገልጋዮቼ ጋር በመርከብ ይሂዱ” አለው፤ ኢዮሣፍጥ ግን አልወደደም። ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮራም ነገሠ። በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመተ መንግሥት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ። በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ በአባቱ በአክዓብ፥ በእናቱም በኤልዛቤል መንገድ፥ እስራኤልንም ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሄደ። በዓሊምንም አመለከ፤ ሰገደላቸውም፤ ከእርሱም አስቀድሞ አባቶቹ እንዳደረጉት ሁሉ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣው።
1 ነገሥት 22:13-53 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ሚክያስን ሊጠራ የሄደው መልእክተኛ፣ “እነሆ፤ ሌሎቹ ነቢያት ንጉሡ ድል እንደሚያደርግ በአንድ ቃል ትንቢት እየተናገሩለት ነውና የአንተም ቃል ከእነርሱ ጋር አንድ እንዲሆን እባክህ መልካም ነገር ተናገር” አለው። ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ለእርሱ የምነግረው እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ ነው” አለ። እዚያም እንደ ደረሰ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፤ በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ እንዝመትባት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዘምተህ ድል አድርጋት” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም አንዳች ነገር እንዳትነግረኝ የማምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው። ከዚያም ሚክያስ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በየተራራው ላይ ተበትነው አየሁ፣ እግዚአብሔርም፣ ‘ይህ ሕዝብ ጌታ የለውም፤ እያንዳንዱ በሰላም ወደየቤቱ ይሂድ’ አለ።” የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው። ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይ ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት፣ አክዓብን ማን ያስተው?’ አለ። “ታዲያ አንዱ ይህን፣ ሌላውም ያን አለ፤ በመጨረሻም፣ አንድ መንፈስ ወጣ፤ ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ፣ ‘እኔ አስተዋለሁ’ አለ። “እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው። “እርሱም፣ ‘እኔ እወጣለሁ፤ በገዛ ነቢያቱም አፍ ሁሉ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። “እግዚአብሔርም፣ ‘በል እንግዲያው ውጣና አስተው፤ ይሳካልሃል’ አለው። “ስለዚህ እነሆ እግዚአብሔር በእነዚህ ሁሉ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ በአንተም ላይ መዓቱን እንደሚያመጣብህ ተናገረ።” ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚክያስን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ በየት በኩል ዐልፎ ነው አንተን መጥቶ ያናገረህ?” ሲል ጠየቀው። ሚክያስም፤ “ይህንማ ለመደበቅ ወደ አንዲት እልፍኝ በሄድህ ዕለት ታውቀዋለህ” አለው። ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “በሉ ሚክያስን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤ ከዚያም፣ ‘ንጉሡ፣ በደኅና እስክመለስ ድረስ፣ ይህን ሰው በእስር ቤት አቈዩት፤ ከደረቅ እንጀራና ከውሃ በስተቀር ሌላ እንዳትሰጡት’ ብሏል በሉት” አለ። ሚክያስም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስህ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረማ!” አለ፤ ከዚያም በመቀጠል፣ “በዚህ ያለኸው ሕዝብ ሁሉ ይህን ቃሌን ልብ ብለህ ያዘው፤” አለ። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ወደምትገኘው ሬማት ወጡ። የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እንዳልታወቅ እኔ ልብስ ለውጬና ሌላ ሰው መስዬ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ራሱን ደብቆ ወደ ጦርነቱ ገባ። በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሠረገላ አዛዦች፣ “ከራሱ ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽም ይሁን ትልቅ ከማንም ጋር እንዳትገጥሙ” ሲል አዝዟቸው ነበር፤ የሠረገላ አዛዦቹ ኢዮሣፍጥን ሲያዩት፣ “ያለ ጥርጥር ይህ የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፤ ስለዚህ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ሲጮህ ግን የሠረገላ አዛዦቹ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን ዐውቀው መከታተሉን ተዉት። ነገር ግን አንዱ ቀስቱን ሳያልም እንዲሁ ሲያስፈነጥር በጦር ልብሱ መጋጠሚያ ላይ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው፤ ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን፣ “ቈስያለሁና ወደ ኋላ አዙረህ ከጦሩ ሜዳ አውጣኝ” አለው። ጦርነቱም ቀኑን ሙሉ ተፋፍሞ ዋለ፤ በዚህ ጊዜም ንጉሡ በሶርያውያን ፊት ለፊት ሠረገላው ላይ ቀና ብሎ እንደ ተደገፈ ነበር፤ የቍስሉ ደም በሠረገላው ወለል ላይ ይወርድ ነበር፤ በዚያኑ ዕለት ማታም ንጉሡ ሞተ። ፀሓይ ስትጠልቅም በሰራዊቱ መካከል፣ “እያንዳንዱ ሰው ወደ ቤቱ፣ እያንዳንዱም ወደ ሀገሩ ይሂድ!” የሚል ጩኸት አስተጋባ። ንጉሡ ስለ ሞተም ወደ ሰማርያ አምጥተውት እዚያው ተቀበረ። ሠረገላውንም አመንዝሮች በታጠቡበት በሰማርያ ኵሬ ዐጠቡት፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ደሙን ውሾች ላሱት። ሌላው በአክዓብ ዘመነ መንግሥት የተፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ ቤተ መንግሥቱን መሥራቱና በዝኆን ጥርስ መለበጡ እንዲሁም የሠራቸው የምሽግ ከተሞች በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን? አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ አካዝያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ነገሠ። ኢዮሣፍጥ ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ አምስት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ሃያ አምስት ዓመት ገዛ። እናቱ ዓዙባ ትባላለች፤ እርሷም የሺልሒ ልጅ ነበረች። በአካሄዱም ሁሉ የአባቱን የአሳን መንገድ ተከተለ፤ ከዚያች ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን አደረገ፤ ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎች አላጠፋም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ይሠዋ፣ ዕጣንም ያጥን ነበር። እንዲሁም ኢዮሣፍጥ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር በሰላም ኖረ። ሌላውም ኢዮሣፍጥ በዘመነ መንግሥቱ የፈጸመው፣ ያከናወነውና ያደረገው ጦርነት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን? ከአባቱ ከአሳ ዘመን በኋላ እንኳ ተርፈው በጣዖት ማምለኪያ ቦታዎች የነበሩትን የወንደቃ ቅሬታዎች ከምድሪቱ አስወገደ። በዚያን ጊዜ ኤዶም ንጉሥ አልነበራትም፤ የሚገዛት እንደራሴ ነበር። ኢዮሣፍጥ ወርቅ ለማምጣት ወደ ኦፊር የሚሄዱ የንግድ መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ በዔጽዮንጋብር ስለ ተሰበሩ ከቶ ወደዚያ መሄድ አልቻሉም ነበር። በዚያን ጊዜም የአክዓብ ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን “ሰዎቼ ከሰዎችህ ጋር በመርከብ ይሂዱ” ሲል ጠይቆት ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን እሺ አላለውም። ኢዮሣፍጥ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበት በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮራምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በሰማርያ ነገሠ፤ እስራኤልንም ሁለት ዓመት ገዛ። እርሱም የአባቱንና የእናቱን፣ እንዲሁም እስራኤልን ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን መንገድ በመከተሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ሥራ ሠራ። አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በኣልን አመለከ፤ ሰገደለትም። በዚህም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ እንዲነሣሣ አደረገ።
1 ነገሥት 22:13-53 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ “እነሆ፥ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ፤” አለው። ሚክያስም “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ፤” አለ። ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር?” አለው፤ እርሱም “ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል፤” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም “ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። እርሱም “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም ‘ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ፤’ አለ፤” ብሎ ተናገረ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን “ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁህምን?” አለው። ሚክያስም አለ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። እግዚአብሔርም ‘ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው?’ አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ ያለ ነገር ተናገረ። መንፈስም ወጣ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ ‘እኔ አሳስተዋለሁ፤’ አለ። እግዚአብሔርም ‘በምን?’ አለው፤ እርሱም ‘ወጥቼ በነቢያቶቹ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ፤’ አለ። እግዚአብሔርም ‘ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፤ ይሆንልሃልም፤ ውጣ፤ እንዲሁም አድርግ፤’ አለ። አሁንም እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል።” የከንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም ጕንጩን በጥፊ መታውና “አንተን ሊናገር የእግዚአብሔር መንፈስ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ?” አለ። ሚክያስም “እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ በሄድህ ጊዜ ታያለህ፤” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማይቱም ሹም ወደ አሞን ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ ‘ንጉሡ እንዲህ ይላል “በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውሃ አጠጡት፤” በሉ’” አለ። ሚክያስም “በደኅና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም፤” አለ። ደግሞም “አሕዛብ ሁሉ ሆይ! ስሙኝ፤” አለ። የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን “ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ፤” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ወደ ሰልፍ ገባ። የሶርያም ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሠረገሎች አለቆች “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፥ ታናሽ ቢሆን ወይም ታላቅ ከማናቸውም ጋር አትግጠሙ፤” ብሎ አዝዞ ነበር። የሠረገሎች አለቆችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ “በእውነት የእስራኤል ንጉሥ ነው፤” አሉ፤ ይገጥሙትም ዘንድ ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም ጮኸ። የሠረገሎች አለቆችም የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። አንድ ሰውም ቀስቱን ድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ ልብስ መጋጠሚያ በኩል ወጋው፤ ሠረገለኛውንም “መልሰህ ንዳ፤ ተወግቻለሁና ከሰልፍ ውስጥ አውጣኝ፤” አለው። በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ ንጉሡም በሶርያውያን ፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ ማታም ሞተ፤ የቍስሉም ደም በሠረገላው ውስጥ ፈሰሰ። በሠራዊቱም መካከል ፀሐይ ስትገባ “ንጉሡ ሞቶአልና እያንዳንዱ ወደ ከተማው፥ እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሂድ!” የሚል ጩኸት ሆነ። ወደ ሰማርያም መጡ፤ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት። አመንዝሮች በታጠቡባት በሰማርያ ኩሬ ሠረገላውን አጠቡት፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ውሾች ደሙን ላሱት። የቀረውም የአክዓብ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የሠራው ቤት፥ የሠራቸውም ከተሞች ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አካዝያስ ነገሠ። አክዓብም በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ። ኢዮሣፍጥ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ አምስት ዓመት ጎበዝ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ አምስት ዓመት ነገሠ። እናቱም ዓዙባ የተባለች የሺልሒ ልጅ ነበረች። በአባቱም በአሳ መንገድ ሁሉ ሄደ፤ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን አደረገ፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ ሕዝቡ ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ታረቀ። የቀረውም የኢዮሣፍጥ ነገር፥ የሠራውም ጭከና፥ እንዴትም እንደ ተዋጋ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ከአባቱ ከአሳ ዘመን የተረፉትን ሰዶማውያን ከምድር አጠፋ። በኤዶምያስም ንጉሥ አልነበረም፤ ሹሙም እንደ ንጉሥ ነበረ። ኢዮሣፍጥም ወደ ኦፊር ሄደው ወርቅ ያመጡ ዘንድ የተርሴስን መርከቦች ሠራ፤ ነገር ግን መርከቦቹ በዔጽዮንጋብር ተሰበሩ እንጂ አልሄዱም። የአክዓብም ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን “ባሪያዎቼ ከባሪያዎችህ ጋር በመርከብ ይሂዱ፤” አለው፤ ኢዮሣፍጥ ግን አልወደደም። ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮራም ነገሠ። በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ። በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ በአባቱና በእናቱም መንገድ፥ እስራኤልንም ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሄደ። በኣልንም አመለከ፤ ሰገደለትም፤ አባቱም እንዳደረገ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣ።
1 ነገሥት 22:13-53 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሚክያስን ለመጥራት ሄዶ የነበረው መልእክተኛ በዚሁ ጊዜ ሚክያስን “ሌሎቹ ነቢያት በሙሉ ንጉሥ አክዓብ ድል የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ የትንቢት ቃል ተናግረዋል፤ ስለዚህም አንተም እንደእነርሱ ብታደርግ ይሻልሃል” አለው። ሚክያስ ግን “እግዚአብሔር የሚገልጥልኝን ቃል ብቻ እንደምናገር በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ!” ሲል መለሰለት። ሚክያስም ወደ ንጉሥ አክዓብ ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ንጉሥ ኢዮሣፍጥና እኔ ወደ ራሞት ሄደን ጦርነት እንክፈት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው። ሚክያስም “ዘምተህ አደጋ ጣልባት! በእርግጥም ታሸንፋለህ፤ እግዚአብሔርም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲል መለሰለት። አክዓብ ግን “አንተ በእግዚአብሔር ስም የትንቢትን ቃል ስትነግረኝ እውነቱን ግለጥ! ይህንንስ ስንት ጊዜ እነግርሃለሁ?” አለው። ሚክያስም “መላው የእስራኤል ሠራዊት ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በኮረብታዎች ላይ ተበታትነው አያለሁ፤ እግዚአብሔርም ‘እነዚህ ሰዎች መሪ የላቸውም፤ ስለዚህ ወደየቤታቸው በሰላም ይመለሱ ብሎአል’ ሲል መለሰለት።” አክዓብም ኢዮሣፍጥን “እርሱ ዘወትር ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም ብዬህ አልነበረምን?” አለው። ሚክያስም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለውን ስማ! እግዚአብሔር በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፥ መላእክቱም ሁሉ በቀኝና በግራው ቆመው አየሁ፤ እግዚአብሔርም ‘አክዓብ ወደ ራሞት ሄዶ በዚያ እንዲገደል ሊያሳስተው የሚችል ማነው?’ አለ፤ ከመላእክቱም መካከል አንዱ አንድ ነገር፥ ሌላው ሌላ ነገር በመግለጥ የተለያየ ሐሳብ ያቀርቡ ነበር፤ በመጨረሻ ግን አንድ መንፈስ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ‘እኔ ላሳስተው እችላለሁ’ አለ፤ እግዚአብሔርም ‘እንዴት አድርገህ ልታሳስተው ትችላለህ?’ አለው። መንፈሱም ‘ሄጄ የአክዓብ ነቢያት ሁሉ ሐሰት እንዲናገሩ አደርጋለሁ’ ሲል መለሰለት፤ እግዚአብሔርም ‘እንግዲያውስ ሄደህ አሳስተው፤ ይከናወንልሃል አለው።’ ” ሚክያስም “እንግዲህ የተወሰነው ይህ ነው፤ እነዚህን የአንተን ነቢያት የሐሰት ቃል እንዲነግሩህ ያደረጋቸው እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ በአንተ ላይ መዓት ሊያመጣብህ እግዚአብሔር ራሱ ወስኖአል!” ሲል ንግግሩን ደመደመ። ከዚህ በኋላ የከናዕና ልጅ ሴዴቅያስ ወደ ሚክያስ ቀረብ ብሎ በጥፊ በመምታት “ኧረ ከመቼ ወዲህ ነው የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ አልፎ አንተን ያነጋገረህ?” አለው። ሚክያስም “በስተ ጓሮ በኩል ወዳለው ክፍል ሄደህ በምትሸሸግበት ጊዜ ታገኘዋለህ” ሲል መለሰለት። በዚህን ጊዜ ንጉሥ አክዓብ ከጦር መኰንኖቹ አንዱን “ሚክያስን ያዘው፤ ወደ ከተማይቱ ገዢ ወደ አሞንና ወደ ልዑል ዮአሽ ውሰደው፤ እኔም በደኅና እስክመለስ ድረስ በእስር ቤት አስገብተው ደረቅ እንጀራና ውሃ ብቻ እየሰጡት እንዲቈይ ያደርጉ ዘንድ በእኔ ስም ንገራቸው” ሲል አዘዘው። ሚክያስም “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት አልተናገረም ማለት ነዋ!” አለው፤ ቀጥሎም ድምፁን ከፍ በማድረግ “በዚህ የምትገኙ ሕዝቦች ሁሉ እኔ የተናገርኩትን ሁሉ ልብ ብላችሁ አድምጡ!” አለ። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ምድር በምትገኘው በራሞት ከተማ ላይ አደጋ ለመጣል ዘመቱ። አክዓብም ኢዮሣፍጥን “ወደ ጦርነት ለመሄድ ስንነሣ እኔ ሌላ ሰው መስዬ ለመታየት ሌላ ልብስ እለብሳለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ሌላ ልብስ ለብሶ ማንነቱን በመሰወር ዘመተ። የሶርያ ንጉሥ “በንጉሡ ላይ እንጂ በሌላ በማንም ላይ አደጋ አትጣሉ” ሲል ለሠላሳ ሁለቱ የሠረገላ ጦር አዛዦች ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ስለዚህ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ስለ መሰላቸው በእርሱ ላይ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም በጮኸ ጊዜ፤ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በማረጋገጥ በእርሱ ላይ አደጋ ከመጣል ተገቱ፤ ይሁን እንጂ በአጋጣሚ አንድ የሶርያ ወታደር ፍላጻ በማስፈንጠር ንጉሥ አክዓብን በጦር ልብሱ መገናኛ ላይ መታው፤ ንጉሥ አክዓብም የሠረገላ ነጂውን “እኔ ቈስያለሁ! ስለዚህ ሠረገላውን መልሰህ ከጦር ሜዳው ውጣ!” ሲል አዘዘው። ጦርነቱም በተፋፋመ ጊዜ ንጉሥ አክዓብ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ ከቊስሉም የሚፈሰው ደም ብዛት ከስር በኩል ሠረገላውን በክሎት ነበር፤ በዚያውም ቀን ምሽት ሞተ፤ ፀሐይ ልትጠልቅ ጥቂት ሲቀራትም “እያንዳንዱ ሰው ወደየአገሩና ወደየከተማው ተመልሶ ይሂድ!” የሚል ትእዛዝ ከእስራኤል ጦር አዛዦች ተነገረ። ንጉሥ አክዓብ በዚህ ዐይነት ሞተ፤ ሬሳውም ወደ ሰማርያ ተወስዶ ተቀበረ፤ ሠረገላውም በሰማርያ ኲሬ ታጠበ፤ እግዚአብሔርም አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ደሙን ውሾች ላሱት፤ በዚያም ኲሬ ጋለሞታዎች ታጠቡበት። ንጉሥ አክዓብ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ፥ ቤተ መንግሥቱን በዝሆን ጥርስ እንዴት አስጊጦ እንደ ሰራውና የሠራቸውም ከተሞች ሁኔታ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ንጉሥ አክዓብም ስለ ሞተ በእርሱ እግር ተተክቶ ልጁ አካዝያስ ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ እርሱም በሠላሳ አምስት ዓመት ዕድሜው ነግሦ ኻያ አምስት ዓመት በኢየሩሳሌም ገዛ፤ እናቱም ዐዙባ ተብላ የምትጠራ የሺልሒ ልጅ ነበረች። ኢዮሣፍጥ ከእርሱ በፊት እንደ ነበረው እንደ አሳ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ሠራ፤ ይሁን እንጂ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን አልደመሰሰም ነበር፤ ስለዚህም ሕዝቡ በእነዚያ ቦታዎች መሥዋዕት ማቅረብና ዕጣን የማጠን ተግባሩን አልተወም ነበር፤ ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ሰላም መሥርቶ ይኖር ነበር። ኢዮሣፍጥ ያደረጋቸው ነገሮችና፥ በጦርነት ላይ ያሳየው ጀግንነትም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ከአባቱ ከአሳ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የተረፉትንና በአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎች ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ወንዶችና ሴቶች አመንዝራዎችን ሁሉ አስወገደ። በዚያን ዘመን የኤዶም ምድር የራስዋ ንጉሥ አልነበራትም፤ ከዚህም የተነሣ በይሁዳ ንጉሥ በሚሾመው እንደ ራሴ ትገዛ ነበር። ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ውቅያኖስን አቋርጠው ከኦፊር ወርቅ የሚያመጡለትን የተርሴስ ዐይነት መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ነገር ግን መርከቦቹ በኤጽዮንጋብር ወደብ ላይ ስለ ተሰበሩ መጓዝ አልቻሉም። ከዚያም በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ መርከበኞቹ ከኢዮሣፍጥ መርከበኞች ጋር በኅብረት እንዲሠሩ የውል ድርድር አቅርቦ ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን ሐሳቡን አልተቀበለም። ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮራም ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ። እርሱም የአባቱን የአክዓብን፥ የእናቱን የኤልዛቤልንና የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት የመራውን የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል በእግዚአብሔር ፊት በደል ሠራ። ከእርሱም በፊት እንደ ነበረው እንደ አባቱ ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ በመስገድና በማገልገል የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቊጣ አነሣሣ።
1 ነገሥት 22:13-53 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሚክያስን ለመጥራት ሄዶ የነበረው መልእክተኛ በዚሁ ጊዜ ሚክያስን “ሌሎቹ ነቢያት በሙሉ ንጉሥ አክዓብ ድል የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ የትንቢት ቃል ተናግረዋል፤ ስለዚህም አንተም እንደ እነርሱ ብታደርግ ይሻልሃል” አለው። ሚክያስ ግን “ጌታ የሚገልጥልኝን ቃል ብቻ እንደምናገር በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ!” ሲል መለሰለት። ሚክያስም ወደ ንጉሥ አክዓብ ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ንጉሥ ኢዮሣፍጥና እኔ ወደ ራሞት ሄደን ጦርነት እንክፈት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው። ሚክያስም “ዘምተህ አደጋ ጣልባት! በእርግጥም ታሸንፋለህ፤ ጌታም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲል መለሰለት። አክዓብ ግን “አንተ በጌታ ስም የትንቢትን ቃል ስትነግረኝ እውነቱን ግለጥ! ይህንንስ ስንት ጊዜ እነግርሃለሁ?” አለው። ሚክያስም “መላው የእስራኤል ሠራዊት ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በኮረብታዎች ላይ ተበታትነው አያለሁ፤ ጌታም ‘እነዚህ ሰዎች መሪ የላቸውም፤ ስለዚህ ወደየቤታቸው በሰላም ይመለሱ ብሏል’ ሲል መለሰለት።” አክዓብም ኢዮሣፍጥን “እርሱ ዘወትር ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም ብዬህ አልነበረምን?” አለው። ሚክያስም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ ጌታ የሚለውን ስማ! ጌታ በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፥ መላእክቱም ሁሉ በቀኝና በግራው ቆመው አየሁ፤ ጌታም ‘አክዓብ ወደ ራሞት ሄዶ በዚያ እንዲገደል ሊያሳስተው የሚችል ማነው?’ አለ፤ ከመላእክቱም መካከል አንዱ አንድ ነገር፥ ሌላው ሌላ ነገር በመግለጥ የተለያየ ሐሳብ ያቀርቡ ነበር። በመጨረሻ ግን አንድ መንፈስ ወደ ጌታ ፊት ቀርቦ ‘እኔ ላሳስተው እችላለሁ’ አለ። ጌታም ‘እንዴት አድርገህ ልታሳስተው ትችላለህ?’ አለው። መንፈሱም ‘ሄጄ የአክዓብ ነቢያት ሁሉ ሐሰት እንዲናገሩ አደርጋለሁ’ ሲል መለሰለት፤ እግዚአብሔርም ‘እንግዲያውስ ሄደህ አሳስተው፤ ይከናወንልሃል አለው።’” ሚክያስም “እንግዲህ የተወሰነው ይህ ነው፤ እነዚህን የአንተን ነቢያት የሐሰት ቃል እንዲነግሩህ ያደረጋቸው ጌታ ነው፤ ስለዚህ በአንተ ላይ መዓት ሊያመጣብህ ጌታ ራሱ ወስኖአል!” ሲል ንግግሩን ደመደመ። ከዚህ በኋላ የከናዕና ልጅ ሴዴቅያስ ወደ ሚክያስ ቀረብ ብሎ በጥፊ በመምታት “ኧረ ከመቼ ወዲህ ነው የጌታ መንፈስ ከእኔ አልፎ አንተን ያነጋገረህ?” አለው። ሚክያስም “በስተ ጓሮ በኩል ወዳለው ክፍል ሄደህ በምትሸሸግበት ጊዜ ታገኘዋለህ” ሲል መለሰለት። በዚህን ጊዜ ንጉሥ አክዓብ ከጦር መኰንኖቹ አንዱን “ሚክያስን ያዘው፤ ወደ ከተማይቱ ገዢ ወደ አሞንና ወደ ልዑል ዮአሽ ውሰደው፤ እኔም በደኅና እስክመለስ ድረስ በእስር ቤት አስገብተው ደረቅ እንጀራና ውሃ ብቻ እየሰጡት እንዲቆይ ያደርጉ ዘንድ በእኔ ስም ንገራቸው” ሲል አዘዘው። ሚክያስም “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት አልተናገረም ማለት ነዋ!” አለው፤ ቀጥሎም ድምፁን ከፍ በማድረግ “በዚህ የምትገኙ ሕዝቦች ሁሉ እኔ የተናገርኩትን ሁሉ ልብ ብላችሁ አድምጡ!” አለ። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ምድር በምትገኘው በራሞት ከተማ ላይ አደጋ ለመጣል ዘመቱ። አክዓብም ኢዮሣፍጥን “ወደ ጦርነት ለመሄድ ስንነሣ እኔ ሌላ ሰው መስዬ ለመታየት ሌላ ልብስ እለብሳለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ሌላ ልብስ ለብሶ ማንነቱን በመሰወር ዘመተ። የሶርያ ንጉሥ “በንጉሡ ላይ እንጂ በሌላ በማንም ላይ አደጋ አትጣሉ” ሲል ለሠላሳ ሁለቱ የሠረገላ ጦር አዛዦች ትእዛዝ አስተላለፈ። ስለዚህ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ስለ መሰላቸው በእርሱ ላይ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም በጮኸ ጊዜ፤ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በማረጋገጥ በእርሱ ላይ አደጋ ከመጣል ተገቱ። ይሁን እንጂ በአጋጣሚ አንድ የሶርያ ወታደር ፍላጻ በማስፈንጠር ንጉሥ አክዓብን በጦር ልብሱ መገናኛ ላይ መታው፤ ንጉሥ አክዓብም የሠረገላ ነጂውን “እኔ ቆስያለሁ! ስለዚህ ሠረገላውን መልሰህ ከጦር ሜዳው ውጣ!” ሲል አዘዘው። ጦርነቱም በተፋፋመ ጊዜ ንጉሥ አክዓብ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ ከቁስሉም የሚፈሰው ደም ብዛት ከስር በኩል ሠረገላውን በክሎት ነበር፤ በዚያውም ቀን ምሽት ሞተ። ፀሐይ ልትጠልቅ ጥቂት ሲቀራትም “እያንዳንዱ ሰው ወደየአገሩና ወደየከተማው ተመልሶ ይሂድ!” የሚል ትእዛዝ ከእስራኤል ጦር አዛዦች ተነገረ። ንጉሥ አክዓብ በዚህ ዓይነት ሞተ፤ ሬሳውም ወደ ሰማርያ ተወስዶ ተቀበረ፤ ሠረገላውም በሰማርያ ኲሬ ታጠበ፤ ጌታም አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ደሙን ውሾች ላሱት፤ በዚያም ኲሬ ጋለሞታዎች ታጠቡበት። ንጉሥ አክዓብ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ፥ ቤተ መንግሥቱን በዝሆን ጥርስ እንዴት አስጊጦ እንደ ሠራውና የሠራቸውም ከተሞች ሁኔታ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ንጉሥ አክዓብም ስለ ሞተ በእርሱ እግር ተተክቶ ልጁ አካዝያስ ነገሠ። የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። እርሱም በሠላሳ አምስት ዓመት ዕድሜው ነግሦ ኻያ አምስት ዓመት በኢየሩሳሌም ገዛ፤ እናቱም ዐዙባ ተብላ የምትጠራ የሺልሒ ልጅ ነበረች። ኢዮሣፍጥ ከእርሱ በፊት እንደነበረው እንደ አሳ በጌታ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ሠራ፤ ይሁን እንጂ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን አልደመሰሰም ነበር፤ ስለዚህም ሕዝቡ በእነዚያ ቦታዎች መሥዋዕት ማቅረብና ዕጣን የማጠን ተግባሩን አልተወም ነበር፤ ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ሰላም መሥርቶ ይኖር ነበር። ኢዮሣፍጥ ያደረጋቸው ነገሮችና፥ በጦርነት ላይ ያሳየው ጀግንነትም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ከአባቱ ከአሳ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የተረፉትንና በአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎች ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ወንዶችና ሴቶች አመንዝራዎችን ሁሉ አስወገደ። በዚያን ዘመን የኤዶም ምድር የራስዋ ንጉሥ አልነበራትም፤ ከዚህም የተነሣ በይሁዳ ንጉሥ በሚሾመው እንደ ራሴ ትገዛ ነበር። ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ውቅያኖስን አቋርጠው ከኦፊር ወርቅ የሚያመጡለትን የተርሴስን ዓይነት መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ነገር ግን መርከቦቹ በኤጽዮንጋብር ወደብ ላይ ስለ ተሰበሩ መጓዝ አልቻሉም። ከዚያም በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ መርከበኞቹ ከኢዮሣፍጥ መርከበኞች ጋር በኅብረት እንዲሠሩ የውል ድርድር አቅርቦ ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን ሐሳቡን አልተቀበለም። ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮራም ነገሠ። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ። እርሱም የአባቱን የአክዓብን፥ የእናቱን የኤልዛቤልንና የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት የመራውን የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል በጌታ ፊት በደል ሠራ።