የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 22

22
ነቢዩ ሚክያስ ንጉሥ አክዓብን ማስጠንቀቁ
(2ዜ.መ. 18፥2-27)
1ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ሦስት ዓመቶች ውስጥ በእስራኤልና በሶርያ መካከል ጦርነት ተወግዶ ሰላም ሰፍኖ ነበር። 2ይሁን እንጂ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ለመጐብኘት ወረደ። 3አክዓብ ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለ ሥልጣኖች “በገለዓድ የምትገኘውን ራሞትን ከሶርያ ንጉሥ ለማስመለስ ምንም ዓይነት እርምጃ ያልወሰድነው ስለምንድን ነው? ራሞት እኮ የእኛ ይዞታ ናት!” አላቸው። 4ኢዮሣፍጥንም “በራሞት ላይ አደጋ ለመጣል ከእኔ ጋር ለመዝመት ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢዮሣፍጥም፥ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ አንተ ሕዝብ ነው፤ ፈረሶቼም እንደ አንተ ፈረሶች ናቸው” አለው።
5“ነገር ግን መጀመሪያ የጌታን ፈቃድ ጠይቅ” ሲል መለሰለት።
6ስለዚህ አክዓብ አራት መቶ የሚሆኑትን ነቢያቱን ጠርቶ “ወደ ራሞት ሄጄ አደጋ ልጣልባት ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው።
እነርሱም “ሄደህ አደጋ ጣልባት፤ ጌታም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲሉ መለሱለት።
7ኢዮሣፍጥ ግን “የጌታን ፈቃድ የምንጠይቅበት ሌላስ ነቢይ የለምን?” ሲል ጠየቀ።
8አክዓብም “የይምላ ልጅ የሆነ ሚክያስ የተባለ ሌላ ነቢይም አለ፤ ነገር ግን እኔ እርሱን አልወደውም፤ እርሱ ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም!” ሲል መለሰለት።
ኢዮሣፍጥም “ይህን ማለት አይገባህም!” አለው።
9ከዚህ በኋላ አክዓብ ከቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች አንዱን ጠርቶ “ሚክያስን ፈልገህ በማግኘት በፍጥነት እንዲመጣ አድርግ” ሲል አዘዘው።
10በዚህም ጊዜ ሁለቱ ነገሥታት ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው በሰማርያ የቅጽር በር አጠገብ በሚገኘው አውድማ በየዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቱም ሁሉ በነገሥታቱ ፊት ቀርበው ትንቢት ይናገሩ ነበር። 11ከእነርሱም አንዱ ሴዴቅያስ ተብሎ የሚጠራው የከናዕና ልጅ ከብረት የተሠሩ ቀንዶችን ይዞ አክዓብን “ጌታ እንዲህ ይላል፤ ‘ከብረት በተሠሩ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ወግተህ ፍጹም የሆነ ድልን ትቀዳጃለህ’” አለው። 12ሌሎቹም ነቢያት ይህንኑ ቃል በመደገፍ “በራሞት ላይ ዝመት፤ ታሸንፋለህ፤ ጌታም ድልን ይሰጥሃል” አሉት።
13ሚክያስን ለመጥራት ሄዶ የነበረው መልእክተኛ በዚሁ ጊዜ ሚክያስን “ሌሎቹ ነቢያት በሙሉ ንጉሥ አክዓብ ድል የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ የትንቢት ቃል ተናግረዋል፤ ስለዚህም አንተም እንደ እነርሱ ብታደርግ ይሻልሃል” አለው።
14ሚክያስ ግን “ጌታ የሚገልጥልኝን ቃል ብቻ እንደምናገር በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ!” ሲል መለሰለት።
15ሚክያስም ወደ ንጉሥ አክዓብ ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ንጉሥ ኢዮሣፍጥና እኔ ወደ ራሞት ሄደን ጦርነት እንክፈት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው።
ሚክያስም “ዘምተህ አደጋ ጣልባት! በእርግጥም ታሸንፋለህ፤ ጌታም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲል መለሰለት።
16አክዓብ ግን “አንተ በጌታ ስም የትንቢትን ቃል ስትነግረኝ እውነቱን ግለጥ! ይህንንስ ስንት ጊዜ እነግርሃለሁ?” አለው።
17 # ዘኍ. 27፥17፤ ማቴ. 9፥36፤ ማር. 6፥34። ሚክያስም “መላው የእስራኤል ሠራዊት ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በኮረብታዎች ላይ ተበታትነው አያለሁ፤ ጌታም ‘እነዚህ ሰዎች መሪ የላቸውም፤ ስለዚህ ወደየቤታቸው በሰላም ይመለሱ ብሏል’ ሲል መለሰለት።”
18አክዓብም ኢዮሣፍጥን “እርሱ ዘወትር ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም ብዬህ አልነበረምን?” አለው።
19 # ኢዮብ 1፥6፤ ኢሳ. 6፥1። ሚክያስም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ ጌታ የሚለውን ስማ! ጌታ በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፥ መላእክቱም ሁሉ በቀኝና በግራው ቆመው አየሁ፤ 20ጌታም ‘አክዓብ ወደ ራሞት ሄዶ በዚያ እንዲገደል ሊያሳስተው የሚችል ማነው?’ አለ፤ ከመላእክቱም መካከል አንዱ አንድ ነገር፥ ሌላው ሌላ ነገር በመግለጥ የተለያየ ሐሳብ ያቀርቡ ነበር። 21በመጨረሻ ግን አንድ መንፈስ ወደ ጌታ ፊት ቀርቦ ‘እኔ ላሳስተው እችላለሁ’ አለ። 22ጌታም ‘እንዴት አድርገህ ልታሳስተው ትችላለህ?’ አለው። መንፈሱም ‘ሄጄ የአክዓብ ነቢያት ሁሉ ሐሰት እንዲናገሩ አደርጋለሁ’ ሲል መለሰለት፤ እግዚአብሔርም ‘እንግዲያውስ ሄደህ አሳስተው፤ ይከናወንልሃል አለው።’”
23ሚክያስም “እንግዲህ የተወሰነው ይህ ነው፤ እነዚህን የአንተን ነቢያት የሐሰት ቃል እንዲነግሩህ ያደረጋቸው ጌታ ነው፤ ስለዚህ በአንተ ላይ መዓት ሊያመጣብህ ጌታ ራሱ ወስኖአል!” ሲል ንግግሩን ደመደመ።
24ከዚህ በኋላ የከናዕና ልጅ ሴዴቅያስ ወደ ሚክያስ ቀረብ ብሎ በጥፊ በመምታት “ኧረ ከመቼ ወዲህ ነው የጌታ መንፈስ ከእኔ አልፎ አንተን ያነጋገረህ?” አለው።
25ሚክያስም “በስተ ጓሮ በኩል ወዳለው ክፍል ሄደህ በምትሸሸግበት ጊዜ ታገኘዋለህ” ሲል መለሰለት።
26በዚህን ጊዜ ንጉሥ አክዓብ ከጦር መኰንኖቹ አንዱን “ሚክያስን ያዘው፤ ወደ ከተማይቱ ገዢ ወደ አሞንና ወደ ልዑል ዮአሽ ውሰደው፤ 27እኔም በደኅና እስክመለስ ድረስ በእስር ቤት አስገብተው ደረቅ እንጀራና ውሃ ብቻ እየሰጡት እንዲቆይ ያደርጉ ዘንድ በእኔ ስም ንገራቸው” ሲል አዘዘው።
28ሚክያስም “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት አልተናገረም ማለት ነዋ!” አለው፤ ቀጥሎም ድምፁን ከፍ በማድረግ “በዚህ የምትገኙ ሕዝቦች ሁሉ እኔ የተናገርኩትን ሁሉ ልብ ብላችሁ አድምጡ!” አለ።
የአክዓብ መሞት
(2ዜ.መ. 18፥28-34)
29ከዚህ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ምድር በምትገኘው በራሞት ከተማ ላይ አደጋ ለመጣል ዘመቱ። 30አክዓብም ኢዮሣፍጥን “ወደ ጦርነት ለመሄድ ስንነሣ እኔ ሌላ ሰው መስዬ ለመታየት ሌላ ልብስ እለብሳለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ሌላ ልብስ ለብሶ ማንነቱን በመሰወር ዘመተ።
31የሶርያ ንጉሥ “በንጉሡ ላይ እንጂ በሌላ በማንም ላይ አደጋ አትጣሉ” ሲል ለሠላሳ ሁለቱ የሠረገላ ጦር አዛዦች ትእዛዝ አስተላለፈ። 32ስለዚህ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ስለ መሰላቸው በእርሱ ላይ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም በጮኸ ጊዜ፤ 33እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በማረጋገጥ በእርሱ ላይ አደጋ ከመጣል ተገቱ። 34ይሁን እንጂ በአጋጣሚ አንድ የሶርያ ወታደር ፍላጻ በማስፈንጠር ንጉሥ አክዓብን በጦር ልብሱ መገናኛ ላይ መታው፤ ንጉሥ አክዓብም የሠረገላ ነጂውን “እኔ ቆስያለሁ! ስለዚህ ሠረገላውን መልሰህ ከጦር ሜዳው ውጣ!” ሲል አዘዘው።
35ጦርነቱም በተፋፋመ ጊዜ ንጉሥ አክዓብ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ ከቁስሉም የሚፈሰው ደም ብዛት ከስር በኩል ሠረገላውን በክሎት ነበር፤ በዚያውም ቀን ምሽት ሞተ። 36ፀሐይ ልትጠልቅ ጥቂት ሲቀራትም “እያንዳንዱ ሰው ወደየአገሩና ወደየከተማው ተመልሶ ይሂድ!” የሚል ትእዛዝ ከእስራኤል ጦር አዛዦች ተነገረ።
37ንጉሥ አክዓብ በዚህ ዓይነት ሞተ፤ ሬሳውም ወደ ሰማርያ ተወስዶ ተቀበረ፤ 38ሠረገላውም በሰማርያ ኲሬ ታጠበ፤ ጌታም አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ደሙን ውሾች ላሱት፤ በዚያም ኲሬ ጋለሞታዎች ታጠቡበት።
39ንጉሥ አክዓብ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ፥ ቤተ መንግሥቱን በዝሆን ጥርስ እንዴት አስጊጦ እንደ ሠራውና የሠራቸውም ከተሞች ሁኔታ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። 40ንጉሥ አክዓብም ስለ ሞተ በእርሱ እግር ተተክቶ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ
(2ዜ.መ. 20፥31—21፥1)
41የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። 42እርሱም በሠላሳ አምስት ዓመት ዕድሜው ነግሦ ኻያ አምስት ዓመት በኢየሩሳሌም ገዛ፤ እናቱም ዐዙባ ተብላ የምትጠራ የሺልሒ ልጅ ነበረች። 43ኢዮሣፍጥ ከእርሱ በፊት እንደነበረው እንደ አሳ በጌታ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ሠራ፤ ይሁን እንጂ የአሕዛብ ማምለኪያ ስፍራዎችን አልደመሰሰም ነበር፤ 44ስለዚህም ሕዝቡ በእነዚያ ቦታዎች መሥዋዕት ማቅረብና ዕጣን የማጠን ተግባሩን አልተወም ነበር፤ 45ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ሰላም መሥርቶ ይኖር ነበር።
46ኢዮሣፍጥ ያደረጋቸው ነገሮችና፥ በጦርነት ላይ ያሳየው ጀግንነትም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፤ 47ከአባቱ ከአሳ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የተረፉትንና በአሕዛብ የማምለኪያ ቦታዎች ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ወንዶችና ሴቶች አመንዝራዎችን ሁሉ አስወገደ።
48በዚያን ዘመን የኤዶም ምድር የራስዋ ንጉሥ አልነበራትም፤ ከዚህም የተነሣ በይሁዳ ንጉሥ በሚሾመው እንደ ራሴ ትገዛ ነበር።
49ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ውቅያኖስን አቋርጠው ከኦፊር ወርቅ የሚያመጡለትን የተርሴስን ዓይነት መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ነገር ግን መርከቦቹ በኤጽዮንጋብር ወደብ ላይ ስለ ተሰበሩ መጓዝ አልቻሉም። 50ከዚያም በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ መርከበኞቹ ከኢዮሣፍጥ መርከበኞች ጋር በኅብረት እንዲሠሩ የውል ድርድር አቅርቦ ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን ሐሳቡን አልተቀበለም።
51ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮራም ነገሠ።
የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ
52የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ። 53እርሱም የአባቱን የአክዓብን፥ የእናቱን የኤልዛቤልንና የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ኃጢአት የመራውን የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል በጌታ ፊት በደል ሠራ። 54ከእርሱም በፊት እንደነበረው እንደ አባቱ በዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ በመስገድና በማገልገል የእስራኤልን አምላክ የጌታን ቁጣ አነሣሣ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ