2ኛ መጽሐፈ ነገሥት መግቢያ
መግቢያ
በሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት ውስጥ በኤልያስና በኤልሳዕ የተደረጉት ተአምራት፥ የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት ታሪክ፥ እንዲሁም የሕዝቡ መማረክ በዘገባና በትረካ ተጽፏል።
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት የተፈጸመውን የ 300 ዓመታት ታሪክ ይዟል። መጽሐፉ የአንደኛ መጽሐፈ ነገሥት ተከታይ ሲሆን ታሪኩን የሚጀምረው አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት ካቆመበት ነው። ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት ከሦስት ዋና ዋና ክፍሎች የተዋቀረ ነው። ከምዕራፍ አንድ እስከ ምዕራፍ ሰባት ያለው የመጀመሪያው ክፍል የነቢዩ የኤልያስን በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ ማረግና፥ የነቢዩ የኤልሳዕን የነቢይነት ዘመን፥ እንዲሁም በነቢዩ በኤልሳዕ የተደረጉ ተኣምራትን የያዘ ነው። ሁለተኛው ክፍል ከምዕራፍ ስምንት እስከ ምዕራፍ ዐሥራ ሰባት ያለው ሲሆን፥ የይሁዳንና የእስራኤልን መንግሥታት ታሪክ የሚዘረዝርና የእስራኤልን መንግሥት መውደቅ የሚተርክ ነው። ከምዕራፍ ዐሥራ ስምንት እስከ ምዕራፍ ሀያ አምስት ያለው ሦስተኛው የመጽሐፉ ክፍል ደግሞ፥ የይሁዳ መንግሥት ብቻውን ያደረገውን የጉዞ ሂደትና በመጨረሻም በናቡከደነፆር መሪነት የይሁዳ ሕዝብ ተማርኮ ወደ ባቢሎን መወሰዱን ይናገራል።
ይህ መጽሐፍ እግዚአብሔር ለሚገዙለትና ዘወትር ለሚያመልኩት ክብርን የሚሰጥ፥ ከትእዛዙ ፈቀቅ በሚሉ ላይ ደግሞ ታላቅ መከራን የሚያመጣ፥ በእውነት የሚፈርድ አምላክ መሆኑን ያስተምራል። እግዚአብሔር በሕጉና በትእዛዙ መሠረት እየሄዱ የሚያገለግሉትን ቅዱሳን ሰዎች በምድር ላይ ተሰሚነትንና ክብርን እንደሚሰጣቸው ማስተዋል ይቻላል። ከዚህም በላይ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ከተፈረደው የሞት ፍርድ አምልጠው በሕይወት መኖር እንዲችሉ የሚያደርግ አምላክ መሆኑን ኤልያስን በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ በማሳረግ አሳይቷል። ለነቢዩ ለኤልሳዕም ሕያዋን ጥፋተኞችን እንዲገድል፥ የሞተን እንዲያስነሣ፥ ሌሎች ታላላቅ ተአምራትን እንዲሠራ ኃይልን ሰጥቶታል። በአንጻሩ ደግሞ በተለያዩ ዘመናት የተነሡት አብዛኞቹ የእስራኤልም ሆኑ የይሁዳ ነገሥታት እግዚአብሔርን ማምለክ ትተው ሌሎች አማልክትን ማምለክ በመጀመራቸው በተለያዩ ጊዜያት በጠላቶቻቸው እንዲወረሩና በምርኮ ከአገራቸው ተወስደው በባዕዳን አገር በመጻተኛነት እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። ይህም እግዚአብሔር ለእርሱ የማይታዘዝን ሕዝብ እንዴት እንደሚቅጣ ያሳያል።
የመጽሐፉ አጠቃላይ ይዘት
የኤልያስና የኤልሳዕ ታሪክና ተአምራት (1፥1—8፥15)
የእስራኤልና የይሁዳ መንግሥታት፥ የሰማርያ አወዳደቅ (8፥16—17፥41)
የይሁዳ መንግሥት ከንጉሥ ሕዝቅያስ እስከ ባቢሎን ምርኮ (18፥1—25፥30)
ምዕራፍ
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ነገሥት መግቢያ: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ