የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 22

22
ነቢዩ ሚክያስ አክዓብን እንዳስጠነቀቅ
(2ዜ.መ. 18፥2-27)
1ሶርያና እስራኤልም ሳይዋጉ ሦስት ዓመት ተቀመጡ። 2በሦስተኛውም ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወረደ። 3የእስራኤልም ንጉሥ ባሪያዎቹን “ሬማት ዘገለዓድ የእኛ እንደ ሆነች፥ እኛም ከሶርያ ንጉሥ እጅ ሳንወስዳት ዝም እንዳልን ታውቃላችሁን?” አላቸው። 4ኢዮሣፍጥንም “በሬማት ዘገለዓድ እንዋጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ትመጣለህን?” አለው። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ “እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው አለው።
5ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ “የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ፤” አለው። 6የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቶቹን አራት መቶ የሚያህሉትን ሰዎች ሰብስቦ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ፤” አሉት። 7ኢዮሣፍጥ ግን “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን?” አለ። 8የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን “እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የይምላ ልጅ ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ፤” አለው። ኢዮሣፍጥም “ንጉሥ እንዲህ አይበል፤” አለ። 9የእስራኤልም ንጉሥ አንዱን ጃንደረባ ጠርቶ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣ፤” አለው። 10የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቶቹም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። 11የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ሶርያውያንን ትወጋለህ፤’” አለ። 12ነቢያትም ሁሉ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን፤” እያሉ እንዲህ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
13ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ “እነሆ፥ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ፤” አለው። 14ሚክያስም “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ፤” አለ። 15ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር?” አለው፤ እርሱም “ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል፤” ብሎ መለሰለት። 16ንጉሡም “ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። 17እርሱም “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም ‘ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ፤’ አለ፤” ብሎ ተናገረ። 18የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን “ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁህምን?” አለው። 19ሚክያስም አለ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። 20እግዚአብሔርም ‘ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው?’ አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ ያለ ነገር ተናገረ። 21መንፈስም ወጣ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ ‘እኔ አሳስተዋለሁ፤’ አለ። 22እግዚአብሔርም ‘በምን?’ አለው፤ እርሱም ‘ወጥቼ በነቢያቶቹ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ፤’ አለ። እግዚአብሔርም ‘ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፤ ይሆንልሃልም፤ ውጣ፤ እንዲሁም አድርግ፤’ አለ። 23አሁንም እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል።”
24የከንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም ጕንጩን በጥፊ መታውና “አንተን ሊናገር የእግዚአብሔር መንፈስ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ?” አለ። 25ሚክያስም “እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ በሄድህ ጊዜ ታያለህ፤” አለ። 26የእስራኤልም ንጉሥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማይቱም ሹም ወደ አሞን ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ ‘ንጉሡ እንዲህ ይላል 27“በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውሃ አጠጡት፤” በሉ’” አለ። 28ሚክያስም “በደኅና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም፤” አለ። ደግሞም “አሕዛብ ሁሉ ሆይ! ስሙኝ፤” አለ።
የአክዓብ ሽንፈትና ሞት
29የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። 30የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን “ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ፤” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ወደ ሰልፍ ገባ። 31የሶርያም ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሠረገሎች አለቆች “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፥ ታናሽ ቢሆን ወይም ታላቅ ከማናቸውም ጋር አትግጠሙ፤” ብሎ አዝዞ ነበር። 32የሠረገሎች አለቆችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ “በእውነት የእስራኤል ንጉሥ ነው፤” አሉ፤ ይገጥሙትም ዘንድ ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም ጮኸ። 33የሠረገሎች አለቆችም የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። 34አንድ ሰውም ቀስቱን ድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ ልብስ መጋጠሚያ በኩል ወጋው፤ ሠረገለኛውንም “መልሰህ ንዳ፤ ተወግቻለሁና ከሰልፍ ውስጥ አውጣኝ፤” አለው። 35በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ ንጉሡም በሶርያውያን ፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ ማታም ሞተ፤ የቍስሉም ደም በሠረገላው ውስጥ ፈሰሰ። 36በሠራዊቱም መካከል ፀሐይ ስትገባ “ንጉሡ ሞቶአልና እያንዳንዱ ወደ ከተማው፥ እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሂድ!” የሚል ጩኸት ሆነ።
37ወደ ሰማርያም መጡ፤ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት። 38አመንዝሮች በታጠቡባት በሰማርያ ኩሬ ሠረገላውን አጠቡት፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ውሾች ደሙን ላሱት። 39የቀረውም የአክዓብ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የሠራው ቤት፥ የሠራቸውም ከተሞች ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 40አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
ኢዮሳፍጥ በይሁዳ እንደ ነገሠ
(2ዜ.መ. 20፥31—21፥1)
41አክዓብም በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ። 42ኢዮሣፍጥ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ አምስት ዓመት ጎበዝ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ አምስት ዓመት ነገሠ። እናቱም ዓዙባ የተባለች የሺልሒ ልጅ ነበረች። 43በአባቱም በአሳ መንገድ ሁሉ ሄደ፤ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን አደረገ፤ ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ ሕዝቡ ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። 44ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ታረቀ።
45የቀረውም የኢዮሣፍጥ ነገር፥ የሠራውም ጭከና፥ እንዴትም እንደ ተዋጋ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 46ከአባቱ ከአሳ ዘመን የተረፉትን ሰዶማውያን ከምድር አጠፋ። 47በኤዶምያስም ንጉሥ አልነበረም፤ ሹሙም እንደ ንጉሥ ነበረ። 48ኢዮሣፍጥም ወደ ኦፊር ሄደው ወርቅ ያመጡ ዘንድ የተርሴስን መርከቦች ሠራ፤ ነገር ግን መርከቦቹ በዔጽዮንጋብር ተሰበሩ እንጂ አልሄዱም። 49የአክዓብም ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን “ባሪያዎቼ ከባሪያዎችህ ጋር በመርከብ ይሂዱ፤” አለው፤ ኢዮሣፍጥ ግን አልወደደም። 50ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮራም ነገሠ።
አካዝያስ በእስራኤል እንደ ነገሠ
51በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ። 52በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ በአባቱና በእናቱም መንገድ፥ እስራኤልንም ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሄደ። 53በኣልንም አመለከ፤ ሰገደለትም፤ አባቱም እንዳደረገ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ