የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 21

21
1የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር ጭፍራውን ሁሉ ሰበሰበ፤ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሁለት ነገሥት ነበሩ፥ ፈረሶችና ሰረገሎችም ነበሩ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበበ፥ ወጋትም። 2ወደ እስራኤልም ንጉሥ ወደ አክዓብ፦ 3ወልደ አዴር እንዲህ ይላል፦ ብርህና ወርቅህ ለእኔ ነው፤ ሴቶችህና መልካካሞቹም ልጆችህ ለእኔ ናቸው ብሎ ወደ ከተማይቱ መልእክተኞችን ላከ። 4የእስራኤል ንጉሥ መልሶ፦ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ አንተ እንዳልህ ነው፤ እኔ ለእኔም የሆነው ሁሉ የአንተ ነው አለ። 5ደግሞም መልእክተኞች ተመልሰው፦ ወልደ አዴር እንዲህ ይላል፦ ቀድሞ ብርህንና ወርቅህን ሴቶችህንና ልጆችህንም ትሰጠኛለህ ብዬ ልኬብህ ነበር፤ 6ነገም በዚህ ጊዜ ባሪያዎቼን እልክብሃለሁ፥ ቤትህንም የባሪያዎችህንም ቤቶች ይበረብራሉ፤ ደስ የሚያሰኛቸውንም ሁሉ በእጃቸው አድርገው ይወስዳሉ አሉ። 7የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፦ ተመልከቱ፥ ይህም ሰው ክፉ እንዲሻ እዩ፤ ስለ ሴቶቼ ስለ ልጆቼ ስለ ብሬና ወርቄም ላከብኝ፥ እንቢም አላልሁም አለ። 8ሽማግሌዎችም ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ፦ አትስማው፥ እሺም አትበለው አሉት። 9ለወልደ አዴርም መልአክተኞች፦ ለጌታዬ ለንጉሥ፦ ለእኔ ለባሪያህ በመጀመሪያ የላክህብኝ ሁሉ አደርጋለሁ፤ ይህ ግን አድርገው ዘንድ አይቻለኝም በሉት አላቸው። መልእክተኞችም ተመልሰው ይህን አወሩለት። 10ወልደ አዴርም፦ ለሚከተለኝ ሕዝብ የሰማርያ ትቢያ ጭብጥ ጭብጥ ይበቃው እንደ ሆነ፥ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ ይህንም ይጨምሩብኝ ብሎ ላከበት። 11የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ፦ በቃ፤ ለሰልፍ የሚታጠቅ ጋሻ ጦሩን እንደሚያወልቅ አይመካ አለው። 12ወልደ አዴርም ያን ነገር በሰማ ጊዜ ከነገሥታቱ ጋር በድንኳኑ ውስጥ ይጠጣ ነበር፤ ባሪያዎቹንም፦ ተሰለፉ አላቸው፤ እነርሱም በከተማይቱ ትይዩ ተሰለፉ። 13እነሆም፥ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ ቀርቦ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህን ብዙ ጭፍራ ሁሉ ታያለህን? እነሆ፥ ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ አለ። 14አክዓብም፦ በማን? አለ፤ እርሱም፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በአውራጆቹ አለቆች ጕልማሶች አለ፤ እርሱም፦ ሰልፉን ማን ይጀምራል? አለ፤ እርሱም፦ አንተ አለው። 15የአውራጆቹንም አለቆች ጕልማሶች ቈጠረ፥ ሁለት መቶም ሠላሳ ሁለት ነበሩ፤ ከእነርሱም በኋላ ሕዝቡን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ሁሉ፥ ቈጠረ፥ ሰባትም ሺህ ነበሩ። 16ቀትርም በሆነ ጊዜ ወጡ፤ ወልደ አዴር ረዳቶቹም ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት እየጠጡ በድንኳን ውስጥ ይሰክሩ ነበር። 17የአውራጆቹም አለቆች ጕልማሶች አስቀድመው ወጡ፤ ወልደ አዴርም መልእክተኞችን ላከ፥ እነርሱም፦ ሰዎች ከሰማርያ ወጥተዋል ብለው ነገሩት። 18እርሱም፦ ለዕርቅ ወይም ለሰልፍ መጥተው እንደ ሆነ በሕይወታቸው ያዙአቸው አለ። 19እነዚህም የአውራጆች አለቆች ጕልማሶች ከከተማይቱ ወጡ፥ ሠራዊትም ተከተላቸው። 20ሁሉም በእያንዳንዱ በፊቱ የነበረውን ሰው ገደለ፥ ሶርያውያንም ሸሹ፤ እስራኤልም አሳደዱአቸው፥ የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር በፈረሱ አመለጠ። 21የእስራኤል ንጉሥም ወጥቶ ፈረሶቹንና ሰረገሎቹን ያዘ፥ ሶርያውያንንም በታላቅ ውጊት ገደላቸው። 22ነቢዩም ወደ እስራኤል ንጉሥ ቀርቦ፦ የሶርያ ንጉሥ በሚመጣው ዓመት ይመጣብሃልና ሂድ፥ በርታ፥ የምታደርገውንም ተመልከትና እወቅ አለው። 23የሶርያም ንጉሥ ባሪያዎች እንዲህ አሉት፦ አምላካቸው የተራሮች አምላክ ነው፤ ስለዚህ በርትተውብን ነበር፤ ነገር ግን በሜዳ ላይ ከእነርሱ ጋር ብንዋጋ በእርግጥ እንበረታባቸዋለን። 24ይህንም አድርግ፤ ከጭፍሮችህ ነገሥታቱን አርቅ፥ በፋንታቸውም አለቆችን ሹም። 25አንተም ቀድሞ እንደ ጠፋብህ ሠራዊት፥ ፈረሱን በፈረስ ፋንታ፥ ሰረገላውንም በሰረገላ ፋንታ፥ ሠራዊትን ቍጠር፤ በሜዳም ላይ ከእነርሱ ጋር እንዋጋለን፥ በእርግጥም እንበረታባቸዋለን። ምክራቸውንም ሰማ፥ እንዲሁም አደረገ። ፕ 26በሚመጣውም ዓመት ወልደ አዴር ሶርያውያንን አሰለፈ፥ ከእስራኤልም ጋር ይዋጋ ዘንድ ወደ አፌቅ ወጣ። 27የእስራኤልም ልጆች ተሰለፉ፥ ሊገጥሙአቸውም ወጡ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ሁለት ትናንሾች የፍየል መንጋዎች ሆነው በፊታቸው ሰፈሩ፤ ሶርያውያን ግን ምድሩን ሞልተው ነበር። 28የእግዚአብሔርም ሰው ቀርቦ የእስራኤልን ንጉሥ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሶርያውያን፦ እግዚአብሔር የተራሮች አምላክ ነው እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ታላቅ ጭፍራ ሁሉ በእጅህ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ አለው። 29እነዚህም በእነዚያ ትይዩ ሰባት ቀን ያህል ሰፈሩ፤ በሰባተኛውም ቀን ተጋጠሙ፥ የእስራኤልም ልጆች ከሶርያውያን በአንድ ቀን መቶ ሺህ እግረኛ ገደሉ። 30የቀሩትም ወደ አፌቅ ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሸሹ፤ ቅጥሩም በቀሩት በሀያ ሰባት ሺህ ሰዎች ላይ ወደቀ። ወልደ አዴርም ሸሽቶ ወደ ከተማይቱ ወደ እልፍኙ ውስጥ ገባ። 31ባሪያዎቹም፦ እነሆ፥ የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሐሪዎች እንደ ሆኑ ሰምተናል፤ በወገባችን ማቅ እንታጠቅ፥ በራሳችንም ገመድ እንጠምጥም፥ ወደ እስራኤልም ንጉሥ እንውጣ፤ ምናልባት ነፍስህን ይምራታል አሉት። 32ወገባቸውንም በማቅ ታጠቁ፥ በራሳቸውም ገመድ ጠመጠሙ፥ ወደ እስራኤልም ንጉሥ መጥተው፦ ባሪያህ ወልደ አዴር፦ ነፍሴን ትምራት ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎአል አሉት። እርሱም፦ ገና በሕይወቱ አለን? ወንድሜ ነው አለ። 33ሰዎቹም የደግ ምልክት አደረጉትና ቃሉን ከአፉ ተቀብለው፦ ወንድምህ ወልደ አዴር አለ አሉት። እርሱም፦ ሂዱ፥ አምጡት አለ። ወልደ አዴርም ወደ እርሱ ወጣ፥ በሰረገላውም ላይ አስቀመጠው። 34ወልደ አዴርም፦ አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልስልሃለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገ አንተ በደማስቆ ገበያ ታደርጋለህ አለው። አክዓብም፦ እኔም በዚህ ቃል ኪዳን እሰድድሃለሁ አለ። ከእርሱም ጋር ቃል ኪዳን አድርጎ ሰደደው። 35ከነቢያትም ወገን አንድ ሰው በእግዚአብሔር ቃል ባልንጀራውን፦ ምታኝ አለው። ሰውዮውም ይመታው ዘንድ እንቢ አለ። 36እርሱም፦ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና እነሆ፥ ከእኔ በራቅህ ጊዜ አንበሳ ይገድልሃል አለው። ከእርሱም በራቀ ጊዜ አንበሳ አግኝቶ ገደለው። 37ደግሞም ሌላ ሰው አግኝቶ፦ ምታኝ አለው። ሰውዮውም መታው፥ በመምታቱም አቈሰለው። 38ነቢዩም ሄዶ በመንገድ አጠገብ ንጉሡን ቆየው፤ ዓይኖቹንም በቀጸላው ሸፍኖ ተሸሸገ። 39ንጉሡም ባለፈ ጊዜ ወደ እርሱ ጮኽ፦ ባሪያህ ወደ ሰልፍ መካከል ወጣ፤ እነሆም፥ አንድ ሰው ፈቀቅ ብሎ ወደ እኔ አንድ ሰው አመጣና፦ ይህን ሰው ጠብቅ፥ ቢኮበልልም ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ ትሆናለች፥ ወይም አንድ መክሊት ብር ትከፍላለህ አለኝ። 40ባሪያህም ወዲህና ወዲያ ሲመለከት ጠፋ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ፦ ፍርድህ እንዲሁ ይሆናል፤ አንተ ፈርድኸዋል አለው። 41ፈጥኖም ቀጸላውን ከዓይኑ አነሣ የእስራኤልም ንጉሥ ከነቢያት ወገን እንደ ሆነ አወቀው። 42እርሱም፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ እርም ያልሁትን ሰው ከእጅህ አውጥተሃልና ነፍስህ በነፍሱ ፋንታ ሕዝብህም በሕዝቡ ፋንታ ይሆናሉ አለው። 43የእስራኤልም ንጉሥ እየተቈጣና እየተናደደ ወደ ቤቱ ተመለሰ፥ ወደ ሰማርያም መጣ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ