አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 20
20
የናቡቴ የወይን ተክል ቦታ
1ለኢይዝራኤላዊውም ለናቡቴ በሰማርያ ንጉሥ በአክዓብ ቤት አጠገብ የወይን ቦታ ነበረው። 2አክዓብም ናቡቴን “በቤቴ አቅራቢያ ነውና የአትክልት ቦታ አደርገው ዘንድ የወይን ቦታህን ስጠኝ፤ ስለ እርሱም ከእርሱ የተሻለ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ወይም ብትወድድ ግምቱን ገንዘብ እሰጥሃለሁ፤” ብሎ ተናገረው። 3ናቡቴም አክዓብን “የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር ያርቅልኝ፤” አለው። 4ኢይዝራኤላዊውም ናቡቴ “የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም፤” ብሎ ስለ ተናገረው አክዓብ ተቆጥቶና ተናድዶ ወደ ቤቱ ገባ። በአልጋውም ላይ ተጋድሞ ፊቱን ተሸፋፈነ፤ እንጀራም አልበላም።
5ሚስቱም ኤልዛቤል ወደ እርሱ መጥታ “ልብህ የሚያዝን እንጀራስ የማትበላ ስለምንድር ነው?” አለችው። 6እርሱም “ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን ‘የወይንህን ቦታ በገንዘብ ስጠኝ፤ ወይም ብትወድድ በፋንታው ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤’ ብዬ ተናገርሁት፤ እርሱ ግን ‘የወይን ቦታዬን አልሰጥህም፤’ ብሎ ስለ መለሰልኝ ነው፤” አላት። 7ሚስቱም ኤልዛቤል “አንተ አሁን የእስራኤልን መንግሥት ትገዛለህን? ተነሣ፤ እንጀራም ብላ፤ ልብህም ደስ ይበላት፤ የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤” አለችው። 8በአክዓብም ስም ደብዳቤ ጻፈች፤ በማኅተሙም አተመችው፤ በከተማው ወደ ነበሩትና ከናቡቴም ጋር ወደ ተቀመጡት ሽማግሌዎችና ከበርቴዎች ደብዳቤውን ላከች። 9በደብዳቤውም “ስለ ጾም አዋጅ ንገሩ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀምጡት፤ 10ሁለትም ምናምንቴ ሰዎች በፊቱ አስቀምጡና ‘እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል፤’ ብለው ይመስክሩበት፤ አውጥታችሁም እስኪሞት ድረስ ውገሩት፤” ብላ ጻፈች።
11በከተማውም የተቀመጡት የከተማው ሰዎችና ሽማግሌዎች ከበርቴዎችም ኤልዛቤል እንዳዘዘቻቸውና ወደ እነርሱ በተላከው ደብዳቤ እንደ ተጻፈ እንዲሁ አደረጉ። 12የጾም አዋጅ ነገሩ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀመጡት። 13ሁለቱም ምናምንቴ ሰዎች ገብተው በፊቱ ተቀመጡ፤ ምናምንቴዎቹ ሰዎችም በሕዝቡ ፊት “ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል፤” ብለው በናቡቴ ላይ መሰከሩ። የዚያን ጊዜም ከከተማ አውጥተው እስኪሞት ድረስ ወገሩት። 14ወደ ኤልዛቤልም “ናቡቴ ተወግሮ ሞተ፤” ብለው ላኩ። 15ኤልዛቤልም ናቡቴ ተወግሮ እንደ ሞተ በሰማች ጊዜ ኤልዛቤል አክዓብን “ናቡቴ ሞቶአል፤ በሕይወትም አይደለምና በገንዘብ ይሰጥህ ዘንድ እንቢ ያለውን የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ ተነሥተህ ውረስ፤” አለችው። 16አክዓብም ናቡቴ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ ይወርሰው ዘንድ ወደ ኢይዝራኤላዊው ወደ ናቡቴ ወይን ቦታ ሊወርድ ተነሣ።
ኤልያስ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንደ ተናገረ
17የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 18“ተነሥተህ በሰማርያ የሚኖረውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ እነሆ፥ ይወርሰው ዘንድ በወረደበት በናቡቴ የወይን ቦታ ውስጥ አለ። 19አንተም ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ገድለህ ወረስኸውን?’ ብለህ ንገረው። ‘ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተንም ደም ደግሞ ውሾች ይልሱታል፤’ ብለህ ንገረው።” 20አክዓብም ኤልያስን “ጠላቴ ሆይ! አገኘኸኝን?” አለው። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት “አግኝቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ለማድረግ ራስህን ሽጥሃልና። 21እነሆ፥ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፤ ፈጽሞም እጠርግሃለሁ፤ ከአክዓብም በእስራኤል ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ አጠፋለሁ፤ 22በሥራህም አስቆጥተኸኛልና፥ እስራኤልንም አስተሃልና ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ። 23ደግሞ እግዚአብሔር ስለ ኤልዛቤል ‘በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ኤልዛቤልን ውሾች ይበሉአታል፤’ ብሎ ተናገረ። 24ከአክዓብም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል።” 25በእግዚአብሔር ፊት ክፋት ለመሥራት ራሱን እንደ ሸጠ፥ ሚስቱም ኤልዛቤል እንደ ነዳችው፥ እንደ አክዓብ ያለ ሰው አልነበረም። 26እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ያጠፋቸው አሞራዊያን እንደ ሠሩት ሁሉ፥ ጣዖታትን በመከተል እጅግ ርኩስ ነገር ሠራ።
27አክዓብም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ ገላውን ማቅ አለበሰ፤ ጾመም፤ በማቅ ላይም ተኛ፤ ቅስስ ብሎም ሄደ። 28-29ደግሞም “አክዓብ በፊቴ እንደ ተዋረደ አየህን? በፊቴ የተዋረደ ስለ ሆነ በልጁ ዘመን በቤቱ ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ እንጂ፥ በእርሱ ዘመን ክፉ ነገር አላመጣም፤” የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ መጣ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 20: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ