1 ነገሥት 22:1-40
1 ነገሥት 22:1-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሰማርያም ሦስት ዓመት ተቀመጠ፤ በሶርያና በእስራኤልም መካከል ጦርነት አልነበረም። ከዚህም በኋላ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወረደ። የእስራኤልም ንጉሥ አገልጋዮቹን፥ “ሬማት ዘገለዓድ የእኛ እንደ ሆነች፥ እኛም ከሶርያ ንጉሥ እጅ ሳንወስዳት ዝም እንዳልን ታውቃላችሁን?” አላቸው። የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን፥ “በሬማት ዘገለዓድ እንዋጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ትዘምታለህን?” አለው። ኢዮሣፍጥም ለእስራእል ንጉሥ፥ “እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለው። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፥ “ወደ እግዚአብሔር ዛሬ ጠይቁልን” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቱን አራት መቶ የሚያህሉትን ሰዎች ሰበሰበ፤ የእስራኤል ንጉሥም፥ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም፥ “እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት። ኢዮሳፍጥም፥ “የእስራኤልን ንጉሥ የእግዚአብሔርን ቃል እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን?” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የይምላ ልጅ ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ክፉ እንጂ መልካም አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ” አለው። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም፥ “ንጉሥ እንዲህ አይበል” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ አንዱን ጃንደረባ ጠርቶ፥ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ ጥራው” አለው። የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም ከጦር መሣሪያቸው ጋር በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቱም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ተናገሩ። የከሓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ትወጋቸዋለህ” አለ። ነቢያትም ሁሉ እንዲህ ብለው ትንቢት ተናገሩ፥ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ዝመት፤ እግዚአብሔርም ይረዳሃል። ሶርያውያንንና ንጉሣቸውንም በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል።” ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ፥ “እነሆ፥ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ” አለው። ሚክያስም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ” አለ። ወደ ንጉሡም ደረሰ። ንጉሡም፥ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር?” አለው። እርሱም፥ “ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም፥ “በእግዚአብሔር ስም እውነት ትነግረኝ ዘንድ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። እርሱም አለ፥ “እንዲህ አይደለም፤ እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም አለ፦ እግዚአብሔር የእነዚህ አምላክ አይደለምን? እያንዳንዱ በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ።” የእስራኤልም ንጉሥ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥን፥ “ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁምን?” አለው። ሚክያስም አለ፥ “እንዲህ አይደለም፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሰማሁት እኔ አይደለሁምን? እንዲህ አይደለም፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። እግዚአብሔርም፦ ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው? አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ ያለ ነገር ተናገረ። መንፈስም ወጣ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ፦ እኔ አስተዋለሁ አለ። እግዚአብሔርም፦ በምን ታስተዋለህ? አለው፤ እርሱም ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም፦ ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፤ ይሆንልሃልም፤ ውጣ፤ እንዲሁም አድርግ አለ። አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል።” የከሓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም ጕንጩን በጥፊ መታውና፥ “ምን ዓይነት የእግዚአብሔር መንፈስ ነው የተናገረህ?” አለው። ሚክያስም፥ “እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ ውስጠኛው እልፍኝህ በሄድህ ጊዜ ታያለህ” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ፥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማዪቱም ሹም ወደ አሞን ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ፦ ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉአቸው” አለ። ሚክያስም፥ “በሰላም ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም” አለ። ደግሞም አሕዛብ ሁሉ ሆይ! ስሙኝ” አለ። የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ዘመቱ። የእስራኤልም ንጉሥ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን የእኔን ልብስ ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ወደ ሰልፍ ገባ። የሶርያም ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሰረገሎች አለቆች፥ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፥ ታናሽ ቢሆን ወይም ታላቅ ከማናቸውም ጋር አትዋጉ” ብሎ አዝዞ ነበር። የሰረገሎች አለቆችም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፥ “በእውነት የእስራኤልን ንጉሥ ይመስላል፤” አሉ ይዋጉትም ዘንድ ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም ጮኸ። የሰረገሎች አለቆችም የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። አንድ ሰውም ቀስቱን ድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በሳንባውና በደረቱ መካከል ወጋው፤ ሰረገለኛውንም፥ “መልሰህ ንዳ፤ ተወግቻለሁና ከሰልፍ ውስጥ አውጣኝ” አለው። በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ ንጉሡም ከጥዋት እስከ ማታ በሶርያውያን ፊት በሰረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ የቍስሉም ደም በሰረገላው ውስጥ ፈሰሰ፤ ማታም ሞተ። ፀሐይም በገባች ጊዜ አዋጅ ነጋሪው ወጥቶ፥ “ንጉሡ ሞቶአልና እያንዳንዱ ወደ ከተማው፥ እያንዳንዱም ወደ ሀገሩ ይሂድ” ብሎ አዋጅ ነገረ። ወደ ሰማርያም መጡ፤ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት፤ ሰረገላውንም በሰማርያ ምንጭ አጠቡት። እግዚአብሔርም በነቢዩ አድሮ እንደ ተናገረ ውሾችና ጅቦች ደሙን ላሱት። አመንዝሮች ሴቶችም በደሙ ታጠቡበት። የቀረውም የአክዓብ ነገር፥ ያደረገውም ነገር ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የሠራው ቤት፥ የሠራቸውም ከተሞች ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
1 ነገሥት 22:1-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሶርያና በእስራኤል መካከል ለሦስት ዓመት ጦርነት አልነበረም። በሦስተኛው ዓመት ግን የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ ለመጐብኘት ወረደ። የእስራኤልም ንጉሥ ሹማምቱን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ራሞት የእኛ ሆና ሳለች፣ ከሶርያው ንጉሥ እጅ ለመመለስ ምንም እንዳላደረግን አታውቁምን?” አላቸው። ስለዚህ ኢዮሣፍጥን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ራሞት ላይ ለመዝመት ዐብረኸኝ ለመሄድ ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፣ “እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፣ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለው። ደግሞም ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ፣ “በመጀመሪያ ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ጠይቅ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ልዝመት ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት። ኢዮሣፍጥ ግን፣ “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቀው አንድ ነቢይ አሁንም አለ፤ ነገር ግን ስለ እኔ ክፉ እንጂ ምን ጊዜም መልካም ትንቢት ተናግሮ ስለማያውቅ እጠላዋለሁ፤ ይህም ሰው የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለ። ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሡ እንዲህ ማለት አይገባውም” ሲል መለሰ። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ፣ “የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው” አለው። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ አልባሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ መግቢያ በር አጠገብ ባለው ዐውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። በዚህ ጊዜ፣ የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ የብረት ቀንዶች ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’ ” አለ። የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፣ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዝመትባት” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር። ሚክያስን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ለንጉሡ መልካምን ነገር እየተነበዩ ነው፤ እባክህ የአንተም ቃል እንደ ቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሠኘውን ተናገር” አለው። ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ እነግረዋለሁ” አለ። ወደ ንጉሡ በመጣ ጊዜ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፤ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ እንዝመት ወይስ እንቅር?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “ሂዱና ድል አድርጉ እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር ምንም ነገር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ የማምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው። ከዚያም ሚክያስ፣ “እስራኤል ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘እነዚህ ሰዎች ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደየቤቱ ይመለስ’ ብሏል” ሲል መለሰ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ፣ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው። ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። እግዚአብሔርም፣ ‘የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት ማን ያሳስተው?’ አለ። “አንዱ አንድ ሐሳብ፣ ሌላውም ሌላ ሐሳብ አቀረበ። ከዚያም አንድ መንፈስ መጥቶ፣ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም፣ ‘እኔ አሳስተዋለሁ’ አለ። “እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው። “እርሱም፣ ‘እኔ እወጣና፤ በገዛ ነቢያቱ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። “እግዚአብሔርም፣ ‘ታሳስተዋለህ፤ ይሳካልሃልም፤ እንግዲህ ውጣና አድርግ’ አለው። “ስለዚህ እነሆ እግዚአብሔር በእነዚህ ሁሉ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ እግዚአብሔርም ጥፋት እንደሚያመጣብህ ተናግሯል።” ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚክያስን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በየት በኩል ዐልፎኝ ነው አንተን ያናገረህ?” አለው። ሚክያስም፣ “ለመሸሸግ ወደ እልፍኝህ በምትሄድበት በዚያ ዕለት ታገኘዋለህ” አለው። ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ሚክያስን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤ ከዚያም፣ ‘ንጉሡ፣ ይህን ሰው እስር ቤት አስገቡት፤ በደኅና እስክመለስም ድረስ፣ ከደረቅ እንጀራና ከውሃ በቀር ሌላ እንዳትሰጡት’ ብሏል በሏቸው” አለ። ሚክያስም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ራሞት ገለዓድ ወጡ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ሌላ ሰው መስሎ ወደ ጦርነቱ ገባ። በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሠረገላ አዛዦች፣ “ከራሱ ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽም ሆነ ትልቅ ከሌላ ከማንም ጋራ እንዳትዋጉ” ብሎ አዝዟቸው ነበር፤ የሠረገላው አዛዦችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፣ “የእስራኤል ንጉሥ ይህ ነው” ብለው አሰቡ፤ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ የሠረገላ አዛዦቹ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን ዐውቀው መከታተሉን ተዉት። ይሁን እንጂ አንዱ ቀስቱን በነሲብ ቢያስፈነጥረው፣ በጥሩሩ መጋጠሚያዎች መካከል ዐልፎ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው። ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን “ተመለስና ከጦርነቱ አውጣኝ፤ ቈስያለሁና” አለው። ጦርነቱም ቀኑን ሙሉ ተፋፍሞ ዋለ፤ በዚህ ጊዜ ንጉሡ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ቀና ብሎ እንደ ተደገፈ ነበር፤ የቍስሉ ደም በሠረገላው ወለል ላይ ይወርድ ነበር፤ በዚያ ዕለት ማታም ንጉሡ ሞተ። ፀሓይ ስትጠልቅም በሰራዊቱ መካከል፣ “እያንዳንዱ ሰው ወደ ቤቱ፣ እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሂድ!” የሚል ጩኸት አስተጋባ። ንጉሡ ስለ ሞተም ወደ ሰማርያ አምጥተውት እዚያው ተቀበረ። ሠረገላውንም አመንዝሮች በታጠቡበት በሰማርያ ኵሬ ዐጠቡት፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ደሙን ውሾች ላሱት። ሌላው በአክዓብ ዘመነ መንግሥት የተፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ ቤተ መንግሥቱን መሥራቱና በዝኆን ጥርስ መለበጡ እንዲሁም የሠራቸው የምሽግ ከተሞች በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን? አክዓብም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ ልጁ አካዝያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
1 ነገሥት 22:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሶርያና እስራኤልም ሳይዋጉ ሦስት ዓመት ተቀመጡ። በሦስተኛውም ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወረደ። የእስራኤልም ንጉሥ ባሪያዎቹን “ሬማት ዘገለዓድ የእኛ እንደ ሆነች፥ እኛም ከሶርያ ንጉሥ እጅ ሳንወስዳት ዝም እንዳልን ታውቃላችሁን?” አላቸው። ኢዮሣፍጥንም “በሬማት ዘገለዓድ እንዋጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ትመጣለህን?” አለው። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ “እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው አለው። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ “የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ፤” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቶቹን አራት መቶ የሚያህሉትን ሰዎች ሰብስቦ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ፤” አሉት። ኢዮሣፍጥ ግን “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን?” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን “እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የይምላ ልጅ ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ፤” አለው። ኢዮሣፍጥም “ንጉሥ እንዲህ አይበል፤” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ አንዱን ጃንደረባ ጠርቶ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣ፤” አለው። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቶቹም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ሶርያውያንን ትወጋለህ፤’” አለ። ነቢያትም ሁሉ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን፤” እያሉ እንዲህ ትንቢት ይናገሩ ነበር። ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ “እነሆ፥ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ፤” አለው። ሚክያስም “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ፤” አለ። ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር?” አለው፤ እርሱም “ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል፤” ብሎ መለሰለት። ንጉሡም “ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። እርሱም “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም ‘ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ፤’ አለ፤” ብሎ ተናገረ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን “ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁህምን?” አለው። ሚክያስም አለ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። እግዚአብሔርም ‘ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው?’ አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ ያለ ነገር ተናገረ። መንፈስም ወጣ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ ‘እኔ አሳስተዋለሁ፤’ አለ። እግዚአብሔርም ‘በምን?’ አለው፤ እርሱም ‘ወጥቼ በነቢያቶቹ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ፤’ አለ። እግዚአብሔርም ‘ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፤ ይሆንልሃልም፤ ውጣ፤ እንዲሁም አድርግ፤’ አለ። አሁንም እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል።” የከንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም ጕንጩን በጥፊ መታውና “አንተን ሊናገር የእግዚአብሔር መንፈስ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ?” አለ። ሚክያስም “እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ በሄድህ ጊዜ ታያለህ፤” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማይቱም ሹም ወደ አሞን ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ ‘ንጉሡ እንዲህ ይላል “በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውሃ አጠጡት፤” በሉ’” አለ። ሚክያስም “በደኅና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም፤” አለ። ደግሞም “አሕዛብ ሁሉ ሆይ! ስሙኝ፤” አለ። የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን “ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ፤” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ወደ ሰልፍ ገባ። የሶርያም ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሠረገሎች አለቆች “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፥ ታናሽ ቢሆን ወይም ታላቅ ከማናቸውም ጋር አትግጠሙ፤” ብሎ አዝዞ ነበር። የሠረገሎች አለቆችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ “በእውነት የእስራኤል ንጉሥ ነው፤” አሉ፤ ይገጥሙትም ዘንድ ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም ጮኸ። የሠረገሎች አለቆችም የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። አንድ ሰውም ቀስቱን ድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ ልብስ መጋጠሚያ በኩል ወጋው፤ ሠረገለኛውንም “መልሰህ ንዳ፤ ተወግቻለሁና ከሰልፍ ውስጥ አውጣኝ፤” አለው። በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ ንጉሡም በሶርያውያን ፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ ማታም ሞተ፤ የቍስሉም ደም በሠረገላው ውስጥ ፈሰሰ። በሠራዊቱም መካከል ፀሐይ ስትገባ “ንጉሡ ሞቶአልና እያንዳንዱ ወደ ከተማው፥ እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሂድ!” የሚል ጩኸት ሆነ። ወደ ሰማርያም መጡ፤ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት። አመንዝሮች በታጠቡባት በሰማርያ ኩሬ ሠረገላውን አጠቡት፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ውሾች ደሙን ላሱት። የቀረውም የአክዓብ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የሠራው ቤት፥ የሠራቸውም ከተሞች ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
1 ነገሥት 22:1-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ሦስት ዓመቶች ውስጥ በእስራኤልና በሶርያ መካከል ጦርነት ተወግዶ ሰላም ሰፍኖ ነበር፤ ይሁን እንጂ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ለመጐብኘት ወረደ፤ አክዓብ ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖች “በገለዓድ የምትገኘውን ራሞትን ከሶርያ ንጉሥ ለማስመለስ ምንም ዐይነት እርምጃ ያልወሰድነው ስለምንድን ነው? ራሞት እኮ የእኛ ይዞታ ናት!” አላቸው፤ ኢዮሣፍጥንም “በራሞት ላይ አደጋ ለመጣል ከእኔ ጋር ለመዝመት ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም፥ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ አንተ ሕዝብ ነው፤ ፈረሶቼም እንደ አንተ ፈረሶች ናቸው” አለው። “ነገር ግን መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቅ” ሲል መለሰለት። ስለዚህ አክዓብ አራት መቶ የሚሆኑትን ነቢያቱን ጠርቶ “ወደ ራሞት ሄጄ አደጋ ልጣልባት ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሄደህ አደጋ ጣልባት፤ ጌታም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲሉ መለሱለት። ኢዮሣፍጥ ግን “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቅበት ሌላስ ነቢይ የለምን?” ሲል ጠየቀ። አክዓብም “የይምላ ልጅ የሆነ ሚክያስ የተባለ ሌላ ነቢይም አለ፤ ነገር ግን እኔ እርሱን አልወደውም፤ እርሱ ምን ጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም!” ሲል መለሰለት። ኢዮሣፍጥም “ይህን ማለት አይገባህም!” አለው። ከዚህ በኋላ አክዓብ ከቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች አንዱን ጠርቶ “ሚክያስን ፈልገህ በማግኘት በፍጥነት እንዲመጣ አድርግ” ሲል አዘዘው። በዚህም ጊዜ ሁለቱ ነገሥታት ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው በሰማርያ የቅጽር በር አጠገብ በሚገኘው አውድማ በየዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቱም ሁሉ በነገሥታቱ ፊት ቀርበው ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ከእነርሱም አንዱ ሴዴቅያስ ተብሎ የሚጠራው የከናዕና ልጅ ከብረት የተሠሩ ቀንዶችን ይዞ አክዓብን “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከብረት በተሠሩ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ወግተህ ፍጹም የሆነ ድልን ትቀዳጃለህ’ ” አለው። ሌሎቹም ነቢያት ይህንኑ ቃል በመደገፍ “በራሞት ላይ ዝመት፤ ታሸንፋለህ፤ እግዚአብሔርም ድልን ይሰጥሃል” አሉት። ሚክያስን ለመጥራት ሄዶ የነበረው መልእክተኛ በዚሁ ጊዜ ሚክያስን “ሌሎቹ ነቢያት በሙሉ ንጉሥ አክዓብ ድል የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ የትንቢት ቃል ተናግረዋል፤ ስለዚህም አንተም እንደእነርሱ ብታደርግ ይሻልሃል” አለው። ሚክያስ ግን “እግዚአብሔር የሚገልጥልኝን ቃል ብቻ እንደምናገር በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ!” ሲል መለሰለት። ሚክያስም ወደ ንጉሥ አክዓብ ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ንጉሥ ኢዮሣፍጥና እኔ ወደ ራሞት ሄደን ጦርነት እንክፈት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው። ሚክያስም “ዘምተህ አደጋ ጣልባት! በእርግጥም ታሸንፋለህ፤ እግዚአብሔርም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲል መለሰለት። አክዓብ ግን “አንተ በእግዚአብሔር ስም የትንቢትን ቃል ስትነግረኝ እውነቱን ግለጥ! ይህንንስ ስንት ጊዜ እነግርሃለሁ?” አለው። ሚክያስም “መላው የእስራኤል ሠራዊት ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በኮረብታዎች ላይ ተበታትነው አያለሁ፤ እግዚአብሔርም ‘እነዚህ ሰዎች መሪ የላቸውም፤ ስለዚህ ወደየቤታቸው በሰላም ይመለሱ ብሎአል’ ሲል መለሰለት።” አክዓብም ኢዮሣፍጥን “እርሱ ዘወትር ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም ብዬህ አልነበረምን?” አለው። ሚክያስም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለውን ስማ! እግዚአብሔር በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፥ መላእክቱም ሁሉ በቀኝና በግራው ቆመው አየሁ፤ እግዚአብሔርም ‘አክዓብ ወደ ራሞት ሄዶ በዚያ እንዲገደል ሊያሳስተው የሚችል ማነው?’ አለ፤ ከመላእክቱም መካከል አንዱ አንድ ነገር፥ ሌላው ሌላ ነገር በመግለጥ የተለያየ ሐሳብ ያቀርቡ ነበር፤ በመጨረሻ ግን አንድ መንፈስ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ‘እኔ ላሳስተው እችላለሁ’ አለ፤ እግዚአብሔርም ‘እንዴት አድርገህ ልታሳስተው ትችላለህ?’ አለው። መንፈሱም ‘ሄጄ የአክዓብ ነቢያት ሁሉ ሐሰት እንዲናገሩ አደርጋለሁ’ ሲል መለሰለት፤ እግዚአብሔርም ‘እንግዲያውስ ሄደህ አሳስተው፤ ይከናወንልሃል አለው።’ ” ሚክያስም “እንግዲህ የተወሰነው ይህ ነው፤ እነዚህን የአንተን ነቢያት የሐሰት ቃል እንዲነግሩህ ያደረጋቸው እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ በአንተ ላይ መዓት ሊያመጣብህ እግዚአብሔር ራሱ ወስኖአል!” ሲል ንግግሩን ደመደመ። ከዚህ በኋላ የከናዕና ልጅ ሴዴቅያስ ወደ ሚክያስ ቀረብ ብሎ በጥፊ በመምታት “ኧረ ከመቼ ወዲህ ነው የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ አልፎ አንተን ያነጋገረህ?” አለው። ሚክያስም “በስተ ጓሮ በኩል ወዳለው ክፍል ሄደህ በምትሸሸግበት ጊዜ ታገኘዋለህ” ሲል መለሰለት። በዚህን ጊዜ ንጉሥ አክዓብ ከጦር መኰንኖቹ አንዱን “ሚክያስን ያዘው፤ ወደ ከተማይቱ ገዢ ወደ አሞንና ወደ ልዑል ዮአሽ ውሰደው፤ እኔም በደኅና እስክመለስ ድረስ በእስር ቤት አስገብተው ደረቅ እንጀራና ውሃ ብቻ እየሰጡት እንዲቈይ ያደርጉ ዘንድ በእኔ ስም ንገራቸው” ሲል አዘዘው። ሚክያስም “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት አልተናገረም ማለት ነዋ!” አለው፤ ቀጥሎም ድምፁን ከፍ በማድረግ “በዚህ የምትገኙ ሕዝቦች ሁሉ እኔ የተናገርኩትን ሁሉ ልብ ብላችሁ አድምጡ!” አለ። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ምድር በምትገኘው በራሞት ከተማ ላይ አደጋ ለመጣል ዘመቱ። አክዓብም ኢዮሣፍጥን “ወደ ጦርነት ለመሄድ ስንነሣ እኔ ሌላ ሰው መስዬ ለመታየት ሌላ ልብስ እለብሳለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ሌላ ልብስ ለብሶ ማንነቱን በመሰወር ዘመተ። የሶርያ ንጉሥ “በንጉሡ ላይ እንጂ በሌላ በማንም ላይ አደጋ አትጣሉ” ሲል ለሠላሳ ሁለቱ የሠረገላ ጦር አዛዦች ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ስለዚህ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ስለ መሰላቸው በእርሱ ላይ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም በጮኸ ጊዜ፤ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በማረጋገጥ በእርሱ ላይ አደጋ ከመጣል ተገቱ፤ ይሁን እንጂ በአጋጣሚ አንድ የሶርያ ወታደር ፍላጻ በማስፈንጠር ንጉሥ አክዓብን በጦር ልብሱ መገናኛ ላይ መታው፤ ንጉሥ አክዓብም የሠረገላ ነጂውን “እኔ ቈስያለሁ! ስለዚህ ሠረገላውን መልሰህ ከጦር ሜዳው ውጣ!” ሲል አዘዘው። ጦርነቱም በተፋፋመ ጊዜ ንጉሥ አክዓብ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ ከቊስሉም የሚፈሰው ደም ብዛት ከስር በኩል ሠረገላውን በክሎት ነበር፤ በዚያውም ቀን ምሽት ሞተ፤ ፀሐይ ልትጠልቅ ጥቂት ሲቀራትም “እያንዳንዱ ሰው ወደየአገሩና ወደየከተማው ተመልሶ ይሂድ!” የሚል ትእዛዝ ከእስራኤል ጦር አዛዦች ተነገረ። ንጉሥ አክዓብ በዚህ ዐይነት ሞተ፤ ሬሳውም ወደ ሰማርያ ተወስዶ ተቀበረ፤ ሠረገላውም በሰማርያ ኲሬ ታጠበ፤ እግዚአብሔርም አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ደሙን ውሾች ላሱት፤ በዚያም ኲሬ ጋለሞታዎች ታጠቡበት። ንጉሥ አክዓብ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ፥ ቤተ መንግሥቱን በዝሆን ጥርስ እንዴት አስጊጦ እንደ ሰራውና የሠራቸውም ከተሞች ሁኔታ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ንጉሥ አክዓብም ስለ ሞተ በእርሱ እግር ተተክቶ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
1 ነገሥት 22:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ሦስት ዓመቶች ውስጥ በእስራኤልና በሶርያ መካከል ጦርነት ተወግዶ ሰላም ሰፍኖ ነበር። ይሁን እንጂ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ለመጐብኘት ወረደ። አክዓብ ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለ ሥልጣኖች “በገለዓድ የምትገኘውን ራሞትን ከሶርያ ንጉሥ ለማስመለስ ምንም ዓይነት እርምጃ ያልወሰድነው ስለምንድን ነው? ራሞት እኮ የእኛ ይዞታ ናት!” አላቸው። ኢዮሣፍጥንም “በራሞት ላይ አደጋ ለመጣል ከእኔ ጋር ለመዝመት ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢዮሣፍጥም፥ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ አንተ ሕዝብ ነው፤ ፈረሶቼም እንደ አንተ ፈረሶች ናቸው” አለው። “ነገር ግን መጀመሪያ የጌታን ፈቃድ ጠይቅ” ሲል መለሰለት። ስለዚህ አክዓብ አራት መቶ የሚሆኑትን ነቢያቱን ጠርቶ “ወደ ራሞት ሄጄ አደጋ ልጣልባት ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሄደህ አደጋ ጣልባት፤ ጌታም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲሉ መለሱለት። ኢዮሣፍጥ ግን “የጌታን ፈቃድ የምንጠይቅበት ሌላስ ነቢይ የለምን?” ሲል ጠየቀ። አክዓብም “የይምላ ልጅ የሆነ ሚክያስ የተባለ ሌላ ነቢይም አለ፤ ነገር ግን እኔ እርሱን አልወደውም፤ እርሱ ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም!” ሲል መለሰለት። ኢዮሣፍጥም “ይህን ማለት አይገባህም!” አለው። ከዚህ በኋላ አክዓብ ከቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች አንዱን ጠርቶ “ሚክያስን ፈልገህ በማግኘት በፍጥነት እንዲመጣ አድርግ” ሲል አዘዘው። በዚህም ጊዜ ሁለቱ ነገሥታት ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው በሰማርያ የቅጽር በር አጠገብ በሚገኘው አውድማ በየዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቱም ሁሉ በነገሥታቱ ፊት ቀርበው ትንቢት ይናገሩ ነበር። ከእነርሱም አንዱ ሴዴቅያስ ተብሎ የሚጠራው የከናዕና ልጅ ከብረት የተሠሩ ቀንዶችን ይዞ አክዓብን “ጌታ እንዲህ ይላል፤ ‘ከብረት በተሠሩ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ወግተህ ፍጹም የሆነ ድልን ትቀዳጃለህ’” አለው። ሌሎቹም ነቢያት ይህንኑ ቃል በመደገፍ “በራሞት ላይ ዝመት፤ ታሸንፋለህ፤ ጌታም ድልን ይሰጥሃል” አሉት። ሚክያስን ለመጥራት ሄዶ የነበረው መልእክተኛ በዚሁ ጊዜ ሚክያስን “ሌሎቹ ነቢያት በሙሉ ንጉሥ አክዓብ ድል የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ የትንቢት ቃል ተናግረዋል፤ ስለዚህም አንተም እንደ እነርሱ ብታደርግ ይሻልሃል” አለው። ሚክያስ ግን “ጌታ የሚገልጥልኝን ቃል ብቻ እንደምናገር በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ!” ሲል መለሰለት። ሚክያስም ወደ ንጉሥ አክዓብ ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ንጉሥ ኢዮሣፍጥና እኔ ወደ ራሞት ሄደን ጦርነት እንክፈት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው። ሚክያስም “ዘምተህ አደጋ ጣልባት! በእርግጥም ታሸንፋለህ፤ ጌታም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲል መለሰለት። አክዓብ ግን “አንተ በጌታ ስም የትንቢትን ቃል ስትነግረኝ እውነቱን ግለጥ! ይህንንስ ስንት ጊዜ እነግርሃለሁ?” አለው። ሚክያስም “መላው የእስራኤል ሠራዊት ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በኮረብታዎች ላይ ተበታትነው አያለሁ፤ ጌታም ‘እነዚህ ሰዎች መሪ የላቸውም፤ ስለዚህ ወደየቤታቸው በሰላም ይመለሱ ብሏል’ ሲል መለሰለት።” አክዓብም ኢዮሣፍጥን “እርሱ ዘወትር ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም ብዬህ አልነበረምን?” አለው። ሚክያስም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ ጌታ የሚለውን ስማ! ጌታ በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፥ መላእክቱም ሁሉ በቀኝና በግራው ቆመው አየሁ፤ ጌታም ‘አክዓብ ወደ ራሞት ሄዶ በዚያ እንዲገደል ሊያሳስተው የሚችል ማነው?’ አለ፤ ከመላእክቱም መካከል አንዱ አንድ ነገር፥ ሌላው ሌላ ነገር በመግለጥ የተለያየ ሐሳብ ያቀርቡ ነበር። በመጨረሻ ግን አንድ መንፈስ ወደ ጌታ ፊት ቀርቦ ‘እኔ ላሳስተው እችላለሁ’ አለ። ጌታም ‘እንዴት አድርገህ ልታሳስተው ትችላለህ?’ አለው። መንፈሱም ‘ሄጄ የአክዓብ ነቢያት ሁሉ ሐሰት እንዲናገሩ አደርጋለሁ’ ሲል መለሰለት፤ እግዚአብሔርም ‘እንግዲያውስ ሄደህ አሳስተው፤ ይከናወንልሃል አለው።’” ሚክያስም “እንግዲህ የተወሰነው ይህ ነው፤ እነዚህን የአንተን ነቢያት የሐሰት ቃል እንዲነግሩህ ያደረጋቸው ጌታ ነው፤ ስለዚህ በአንተ ላይ መዓት ሊያመጣብህ ጌታ ራሱ ወስኖአል!” ሲል ንግግሩን ደመደመ። ከዚህ በኋላ የከናዕና ልጅ ሴዴቅያስ ወደ ሚክያስ ቀረብ ብሎ በጥፊ በመምታት “ኧረ ከመቼ ወዲህ ነው የጌታ መንፈስ ከእኔ አልፎ አንተን ያነጋገረህ?” አለው። ሚክያስም “በስተ ጓሮ በኩል ወዳለው ክፍል ሄደህ በምትሸሸግበት ጊዜ ታገኘዋለህ” ሲል መለሰለት። በዚህን ጊዜ ንጉሥ አክዓብ ከጦር መኰንኖቹ አንዱን “ሚክያስን ያዘው፤ ወደ ከተማይቱ ገዢ ወደ አሞንና ወደ ልዑል ዮአሽ ውሰደው፤ እኔም በደኅና እስክመለስ ድረስ በእስር ቤት አስገብተው ደረቅ እንጀራና ውሃ ብቻ እየሰጡት እንዲቆይ ያደርጉ ዘንድ በእኔ ስም ንገራቸው” ሲል አዘዘው። ሚክያስም “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት አልተናገረም ማለት ነዋ!” አለው፤ ቀጥሎም ድምፁን ከፍ በማድረግ “በዚህ የምትገኙ ሕዝቦች ሁሉ እኔ የተናገርኩትን ሁሉ ልብ ብላችሁ አድምጡ!” አለ። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ምድር በምትገኘው በራሞት ከተማ ላይ አደጋ ለመጣል ዘመቱ። አክዓብም ኢዮሣፍጥን “ወደ ጦርነት ለመሄድ ስንነሣ እኔ ሌላ ሰው መስዬ ለመታየት ሌላ ልብስ እለብሳለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ሌላ ልብስ ለብሶ ማንነቱን በመሰወር ዘመተ። የሶርያ ንጉሥ “በንጉሡ ላይ እንጂ በሌላ በማንም ላይ አደጋ አትጣሉ” ሲል ለሠላሳ ሁለቱ የሠረገላ ጦር አዛዦች ትእዛዝ አስተላለፈ። ስለዚህ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ስለ መሰላቸው በእርሱ ላይ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም በጮኸ ጊዜ፤ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በማረጋገጥ በእርሱ ላይ አደጋ ከመጣል ተገቱ። ይሁን እንጂ በአጋጣሚ አንድ የሶርያ ወታደር ፍላጻ በማስፈንጠር ንጉሥ አክዓብን በጦር ልብሱ መገናኛ ላይ መታው፤ ንጉሥ አክዓብም የሠረገላ ነጂውን “እኔ ቆስያለሁ! ስለዚህ ሠረገላውን መልሰህ ከጦር ሜዳው ውጣ!” ሲል አዘዘው። ጦርነቱም በተፋፋመ ጊዜ ንጉሥ አክዓብ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ ከቁስሉም የሚፈሰው ደም ብዛት ከስር በኩል ሠረገላውን በክሎት ነበር፤ በዚያውም ቀን ምሽት ሞተ። ፀሐይ ልትጠልቅ ጥቂት ሲቀራትም “እያንዳንዱ ሰው ወደየአገሩና ወደየከተማው ተመልሶ ይሂድ!” የሚል ትእዛዝ ከእስራኤል ጦር አዛዦች ተነገረ። ንጉሥ አክዓብ በዚህ ዓይነት ሞተ፤ ሬሳውም ወደ ሰማርያ ተወስዶ ተቀበረ፤ ሠረገላውም በሰማርያ ኲሬ ታጠበ፤ ጌታም አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ደሙን ውሾች ላሱት፤ በዚያም ኲሬ ጋለሞታዎች ታጠቡበት። ንጉሥ አክዓብ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ፥ ቤተ መንግሥቱን በዝሆን ጥርስ እንዴት አስጊጦ እንደ ሠራውና የሠራቸውም ከተሞች ሁኔታ ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ንጉሥ አክዓብም ስለ ሞተ በእርሱ እግር ተተክቶ ልጁ አካዝያስ ነገሠ።