1 ነገሥት 19:7-13
1 ነገሥት 19:7-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና፥ “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ” አለው። ተነሥቶም በላ፤ ጠጣም፤ በዚያም በበላው የምግብ ኀይል እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ። እዚያም ወዳለ ዋሻ ገባ፤ በዚያም አደረ፤ እነሆም፥ “ኤልያስ ሆይ! ምን አመጣህ?” የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። ኤልያስም፥ “ሁሉን ለሚገዛ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ” አለ። እርሱም አለ፥ “ነገ ውጣ፤ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም። እነሆም፥ እግዚአብሔር በዚያ አለፈ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፤ ዓለቶቹንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፤ እግዚአብሔርም በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ እንደ ፉጨት ያለ ቀጭን ድምፅ ሆነ፤ በዚያም እግዚአብሔር ነበረ። ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆም፥ “ኤልያስ ሆይ፥ ወደዚህ ለምን መጣህ?” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ።
1 ነገሥት 19:7-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና መጥቶ ነካ አደረገውና፣ “ሩቅ መንገድ ስለምትሄድ ተነሥና ብላ” አለው። ስለዚህም ተነሥቶ በላ፤ ጠጣም፤ በምግቡም ብርታት አግኝቶ ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ኮሬብ እስኪደርስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተጓዘ፤ በዚያም ወደ አንዲት ዋሻ ገብቶ ዐደረ። እግዚአብሔር የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እርሱ መጣ፤ “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አለው። እርሱም፣ “እኔ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ እስራኤላውያን ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና። የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አሁንም እኔን ለመግደል ይፈልጋሉ” አለ። እግዚአብሔርም፣ “እግዚአብሔር በዚያ ያልፋልና ወደ ተራራው ወጥተህ በእግዚአብሔር ፊት ቁም” አለው። ከዚያም ታላቅና ኀይለኛ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጣጠቀ፤ ዐለቶችንም በእግዚአብሔር ፊት ብትንትናቸውን አወጣ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ከነፋሱም ቀጥሎ የምድር መነዋወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መነዋወጡ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መነዋወጡም ቀጥሎ እሳት መጣ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም ቀጥሎ ለስለስ ያለ ድምፅ ተሰማ። ኤልያስም ይህን ሲሰማ፣ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፍኖ ወጣና በዋሻው ደጃፍ ቆመ። ከዚያም፣ “ኤልያስ ሆይ፤ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ።
1 ነገሥት 19:7-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ፤” አለው። ተነሥቶም በላ፤ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኀይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ። እዚያም ወዳለ ዋሻ መጣ፥ በዚያም አደረ። እነሆም “ኤልያስ ሆይ! በዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። እርሱም “ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋል፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ፤” አለ። እርሱም “ውጣ፤ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም፤” አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፤ ዐለቶቹንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ። ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጎናጸፊያው ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆ “ኤልያስ ሆይ! በዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።
1 ነገሥት 19:7-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእግዚአብሔርም መልአክ ተመልሶ መጥቶ “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ስለ ሆነ፥ ተነሥተህ ብላ!” ሲል ዳግመኛ ኤልያስን ቀሰቀሰው፤ ኤልያስም ተነሥቶ ምግቡን በላ፥ ውሃውንም ጠጣ፤ ከዚያም ምግብ ባገኘው ኀይል እስከ ተቀደሰው የሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ተጓዘ፤ እዚያም እንደ ደረሰ ወደ አንድ ዋሻ ገብቶ እዚያ ዐደረ። በድንገትም እግዚአብሔር “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትህንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔንም እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ!” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም ኤልያስን “ካለህበት ወጥተህ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም” አለው፤ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በአጠገቡ አለፈ፤ ብርቱ ነፋስም በፊቱ በመላክ ኰረቶችን ሰነጣጠቀ፤ አለቶችንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ነፋሱም ከቆመ በኋላ ምድሪቱ ተናወጠች፤ እግዚአብሔር ግን በምድሪቱ ነውጥ ውስጥ አልነበረም፤ ከምድሪቱም ነውጥ በኋላ እሳት መጣ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳት ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም በኋላ የሹክሹክታ ድምፅ ተሰማ። ኤልያስ የሹክሹክታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው መግቢያ በር አጠገብ ቆመ፤ አንድ ድምፅም “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው።
1 ነገሥት 19:7-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የጌታም መልአክ ተመልሶ መጥቶ “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ስለ ሆነ፥ ተነሥተህ ብላ!” ሲል ዳግመኛ ኤልያስን ቀሰቀሰው። ኤልያስም ተነሥቶ ምግቡን በላ፥ ውሃውንም ጠጣ፤ ከዚያም ምግብ ባገኘው ኃይል እስከ ተቀደሰው የሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ተጓዘ። እዚያም እንደ ደረሰ ወደ አንድ ዋሻ ገብቶ እዚያ ዐደረ። በድንገትም ጌታ “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትህንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔንም እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ!” ሲል መለሰ። ጌታም ኤልያስን “ካለህበት ወጥተህ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም” አለው፤ ከዚህ በኋላ ጌታ በአጠገቡ አለፈ፤ ብርቱ ነፋስም በፊቱ በመላክ ኰረብቶችን ሰነጣጠቀ፤ አለቶችንም ሰባበረ፤ ጌታ ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ነፋሱም ከቆመ በኋላ ምድሪቱ ተናወጠች፤ ጌታ ግን በምድሪቱ ነውጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድሪቱም ነውጥ በኋላ እሳት መጣ፤ ጌታ ግን በእሳት ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም በኋላ የሹክሹክታ ድምፅ ተሰማ። ኤልያስ የሹክሹክታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው መግቢያ በር አጠገብ ቆመ፤ አንድ ድምፅም “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው።