1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 19
19
ኤልያስ በሲና ተራራ
1ኤልያስ ያደረገውን ሁሉና የበዓልንም ነቢያት በሙሉ በሞት እንዴት እንደ ቀጣ ንጉሥ አክዓብ ለሚስቱ ለኤልዛቤል ነገራት። 2ስለዚህ እርሷ “በእነዚያ ነቢያት ላይ ያደረግኸውን እኔም ነገ ልክ በአሁኑ ሰዓት በአንተ ላይ ሳላደርግብህ ብቀር አማልክት በሞት ይቅሠፉኝ!” ስትል ወደ ኤልያስ የዛቻ መልእክት ላከች። 3ኤልያስም ስለ ፈራ ሕይወቱን ለማትረፍ ከአገልጋዩ ጋር በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህ ከተማ ሄደ።
አገልጋዩንም በዚያ ተወው። 4#ዮናስ 4፥3።ኤልያስ አንድ ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዘ፤ ከዚህ በኋላ ጉዞውን ቆም አድርጎ፥ በአንድ የክትክታ ዛፍ ጥላ ሥር ተቀመጠ፤ ሞቱንም በመመኘት “ጌታ ሆይ! አሁንስ ይብቃኝ፤ ከቀድሞ አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ!” ሲል ጸለየ።
5ከዚህ በኋላ በዛፉ ሥር ጋደም እንዳለ እንቅልፍ ወሰደው፤ በድንገትም አንድ መልአክ መጥቶ በመዳሰስ ቀሰቀሰውና “ተነሥ ብላ!” አለው፤ 6ኤልያስም ተነሥቶ ዙሪያውን በተመለከተ ጊዜ በድንጋይ ሙቀት የበሰለ የዳቦ ሙልሙልና አንድ ገንቦ ውሃ በራስጌው ተቀምጦ አየ፤ ከበላና ከጠጣም በኋላ ተመልሶ ተኛ። 7የጌታም መልአክ ተመልሶ መጥቶ “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ስለ ሆነ፥ ተነሥተህ ብላ!” ሲል ዳግመኛ ኤልያስን ቀሰቀሰው። 8ኤልያስም ተነሥቶ ምግቡን በላ፥ ውሃውንም ጠጣ፤ ከዚያም ምግብ ባገኘው ኃይል እስከ ተቀደሰው የሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ተጓዘ። 9እዚያም እንደ ደረሰ ወደ አንድ ዋሻ ገብቶ እዚያ ዐደረ።
በድንገትም ጌታ “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው።
10 #
ሮሜ 11፥3። ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትህንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔንም እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ!” ሲል መለሰ።
11ጌታም ኤልያስን “ካለህበት ወጥተህ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም” አለው፤ ከዚህ በኋላ ጌታ በአጠገቡ አለፈ፤ ብርቱ ነፋስም በፊቱ በመላክ ኰረብቶችን ሰነጣጠቀ፤ አለቶችንም ሰባበረ፤ ጌታ ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ነፋሱም ከቆመ በኋላ ምድሪቱ ተናወጠች፤ ጌታ ግን በምድሪቱ ነውጥ ውስጥ አልነበረም። 12ከምድሪቱም ነውጥ በኋላ እሳት መጣ፤ ጌታ ግን በእሳት ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም በኋላ የሹክሹክታ ድምፅ ተሰማ።
13ኤልያስ የሹክሹክታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው መግቢያ በር አጠገብ ቆመ፤ አንድ ድምፅም “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው።
14ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔን እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ” ሲል መለሰ።
15 #
2ነገ. 8፥7-13። ጌታም እንዲህ አለው፤ “በደማስቆ ከተማ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓ ተመልሰህ ሂድ፤ እዚያም በደረስህ ጊዜ አዛሄልን ቀብተህ በሶርያ ላይ አንግሠው። 16#2ነገ. 9፥1-6።የኒምሺን ልጅ ኢዩንም ቀብተህ በእስራኤል ላይ አንግሠው፤ የአቤል መሖላ ተወላጅ የሆነውን የዮሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕንም ቀብተህ በአንተ እግር ነቢይ እንዲሆን አድርገው። 17ከአዛሄል እጅ ከመገደል ተርፎ የሚያመልጠውን ማንኛውንም ሰው ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩ እጅ የሚያመልጠውንም ኤልሳዕ ይገድለዋል። 18#ሮሜ 11፥4።ይሁን እንጂ ለእኔ ታማኞች የሆኑ፥ ለባዓል ያልሰገዱና ምስሉንም ያልተሳለሙ ሰባት ሺህ ሰዎችን በእስራኤል ምድር በሕይወት እንዲተርፉ አደርጋለሁ።”
የኤልሳዕ መጠራት
19ኤልያስ ከዚያ ከሄደ በኋላ የዮሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ሁለት በሬዎች ጠምዶ ሲያርስ አገኘው፤ ከእርሱም ጋር በፊቱ በዐሥራ አንድ ጥማድ በሬዎች የሚያርሱ ደቦኞች ነበሩ፤ ኤልሳዕም በመጨረሻው ዐሥራ ሁለተኛ ጥማድ ያርስ ነበር፤ ኤልያስም መጐናጸፊያውን አውልቆ በኤልሳዕ ላይ ደረበለት። 20በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ በሬዎቹን ትቶ ወደ ኤልያስ በመሮጥ “አባትና እናቴን ስሜ እንድሰናበት ፍቀድልኝ ከዚያም በኋላ እከተልሃለሁ” አለው።
ኤልያስም “እሺ፥ ተመልሰህ ሂድ፤ እኔ አልከለክልህም!” ሲል መለሰለት።
21ከዚህ በኋላ ኤልሳዕ ወደ ጥማድ በሬዎቹ ተመልሶ ዐረዳቸው፤ የተጠመዱበትንም ቀንበር በማንደድ ሥጋቸውን ቀቅሎ ለሰዎቹ አቀረበላቸው፤ እነርሱም በሉ፤ ከዚህ በኋላ ኤልያስን ተከትሎ በመሄድ ረዳቱ ሆነ።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 19: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ